Tuesday, December 24, 2013

የአማራ ክልሉ “ዱላ ቅብብሎሽ” ግራ አጋባኝ እኮ!

“የመተካካት ሂደት የዱላ ቅብብሎሽ ነው”
አቶ አያሌው ጐበዜ “ዱላውን” ለማነው ያቀበሉት?

እናንተ … የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነኝ የሚለው “CPJ” እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነኝ ባዩ “ሂዩማን ራይትስዎች” ከላያችን ላይ አንወርድም አሉን አይደል? (ከኢህአዴግና ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት ላይ ማለቴ እኮ ነው!) እኔማ ባለፈው የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ሲካሄድ… ሦስቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት፤ በጋራ የሰጡትን “ዱላቀረሽ” መግለጫ መስማታቸው ስለማይቀር አርፈው ይቀመጣሉ ብዬ ነበር፡፡ ችግሩ ግን “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…” የሚለውን ተረት አያውቁትም!፡፡ አያችሁ … የመብት ተሟጋቾች እኮ ችኮ ናቸው፤ ነገር ከያዙ አይለቁም፡፡ መቼም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት ሶስቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት “የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ የለም” ማለታቸውን የመብት ተሟጋቾቹ መስማታቸው አይቀርም፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ሰሞኑን CPJ ባወጣው ሪፖርት፤ ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያን ከ10 የዓለም አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧል (ገፅታ ለማበላሸት እኮ ነው!)
ድሮም ኒዮሊበራሊስቶች ለጦቢያ ተኝተው አያውቁም! እኔ ግን ሳስበው… እንዲህ ካሉት “ጃይንት” ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ “ፒስ” ማውረድ ነው ተመራጩ፡፡  (“አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው” አለ መሐሙድ!)
ይኸውላችሁ…ኢህአዴግን ልማት ወጥሮ ይዞት ነው እንጂ CPJ ን ማሳመን አያቅተውም ነበር፡፡ ትዝ ይላችኋል …እነ IMF እና እና ዎርልድ ባንክ በባለሁለት ዲጂቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከመንግስት ጋር ሲወዛገቡ! ኢህአዴግ ነፍሴ ምን አደረገ? 10 ዓመት ቢፈጅበትም አሳመናቸው! አሁን የኢህአዴግን ዕድገት እኮ  አምነዋል፡፡ ከጋዜጠኞች ተሟጋቾቹም ሆነ ከሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ጋር ያለውንም ውዝግብ፤ ኢህአዴግ በውይይት ቢሞከረው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
እኔ የምለው…በመብራት፣ በውሃና በስልክ አገልግሎቶች አዲስ የተቆረቆርን አገር መሰልን አይደል? (ደቡብ ሱዳን እኮ ተሻለች!) ሰሞኑን በኢቴቪ የሰማሁት የውሃ ችግር ግን “የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ” የሚያሰኝ ነው፡፡ “ሰሜናዊቷ ኮከብ” እየተባለች በምትሞካሸው መቀሌ ከተማ 3 ወር ሙሉ ውሃ አልነበረም ተባለ፡፡ (አሁንስ የታለ?) የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢቴቪ ቅሬታቸውን ሲናገሩ፤ በውሃ እጦት ክፉኛ መሰቃየታቸውን ገልፀዋል፡፡ (ግን እንደኛ ሳይማረሩ!) እኔማ… የመቀሌ ውሃና ፍሳሽ መ/ቤት፤ ተዘግቶ ነው ብዬ ተወራርጄ ነበር፡፡ አስበሉኝ!  ወዲያው የመ/ቤቱ ሃላፊ በኢቴቪ ከች አሉ (አለማፈራቸው!) እናም “የውሃ እጥረቱ የተከሰተው ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ ነው” ብለው በቀላሉ ተገላገሉት (ይሄማ የተበላ ዕቁብ ነው!)
“ስኳር ለምን ጠፋ?”
“ገበሬው ስኳር መጠቀም ስለጀመረ!”
“መብራት ለምን ይቆራረጣል?”
“የኢንዱስትሪ ዘርፉ ስላደገ!” እነዚህ ሁሉ ሰበቦች አሁን ፋሽናቸው አልፏል፡፡ (ሃላፊው አልሰሙማ!)
እንዴ… እነ መብራት ሃይልና የውሃና ፍሳሽ መ/ቤት ከተማውና ኢንዱስትሪው ሲያድግ የማንን ጐፈሬ እያበጠሩ ነበር? (አብረው አያድጉም እንዴ?) ወይስ የአገሪቱን ዕድገት እየተነበየ፣ ዕቅድ የሚያወጣ አዲስ መ/ቤት ማቋቋም ሊያስፈልግ ነው? (አሁንም እቅጯን ይናገሩ!)
እኔ ግን አንድ ሃሳብ አለኝ…ሦስቱ ትላልቅ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ውሃና ፍሳሽ፣ መብራት ሃይል፣ ኢትዮ - ቴሌኮም) የኢኮኖሚ ዕድገቱና የከተሞች መስፋፋት ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው፣ ትንሽ የዕድገቱ ግስጋሴ በረድ…ቀዝቀዝ … ቢልላቸው ጥሩ ነው (ሌላው ለጥጦ ያቅዳል እነሱ …) ይሄ እንግዲህ በቀና ልቦና ሲተነተን ነው፡፡ ግን ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፤ የSabotage (አሻጥር) ነገር ሊኖርበትም ይችላል፡፡ ምናልባትም የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞች ሰርገው ገብተው ይሆናል፡፡ (መረጃ ውድ በሆነበት አገር ሃሜትና ጥርጣሬ ቢነግስ አይገርምም!)
እኔ የምለው ግን…አፄ ምኒልክ ድንገት ቀና ብለው ይሄን ሁሉ “ምስቅልቅል” ቢመለከቱ “የት አገር ነው የነቃሁት” ብለው ግር የሚላቸው አይመስላችሁም? ከአንድ ክ/ዘመን በኋላ ጦቢያን እንደ አውሮፓ ሆና አገኛታለሁ ሲሉ፣ ከጥንቱም ብሳ ሦስት ወር ውሃ የሚጠፋባት አጃኢብ አገር ሆናላቸዋለች (እንዴት እንደሚያፍሩብን!)
በነገራችሁ ላይ…ካዛንቺስ አካባቢ ባለገመዱ ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ድፍን ወር ሞላው፡፡ ምኒልክ ቢኖሩ … “ማርያምን አልምርህም!” ይሉን ነበር፡፡ እናላችሁ…ኢትዮ ቴሌኮም በተደጋጋሚ ደውለን (በሞባይላችን ማለቴ ነው!) ስንጠይቅ የተሰጠን ምላሽ ምን መሰላችሁ? “አገልግሎቱ የተቋረጠው ከመንገድ ሥራው ጋር በተያያዘ ስለሆነ ትንሽ ታገሱ” የሚል ነው (ኧረ ተመስገን ነው! መዘለፍም አለ እኮ!) እኔ የምለው ግን… “ትንሽ ታገሱ” ሲባል ምን ማለት ነው? 1 ወር? (ወርማ ሊያልፈን ነው!) 2 ወር? 1 ዓመት? 5 ዓመት? (አልነገሩንማ!) ለጊዜው ግን እኛም የመንገድ ሥራ ማለት “ልማት” እንደሆነ ስለምናውቅ፣ የመንግስት ልማት ከሚስተጓጐል የእኛ ልማት አፈር ድሜ ይብላ ብለን ልንታገስ ተስማማን (ምርጫ የለንማ!) ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የዛሬ ዓመት ገደማ የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ ሃላፊ፤ ከኔትዎርክ ችግር ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የመንገዱን መቆፋፈር እንደምክንያት ሊያቀርቡ አሰቡና፣ የፓርቲያቸውን ግምገማ ፈሩ መሰለኝ፣ እንዲህ በብልሃት ተናገሩ:- “ከተማዋ ምስቅልቅል ላይ ናት…ግን የዕድገት ምስቅልቅል ነው!” (ከማንኛውም ምስቅልቅል ያውጣን!)
እኔ የምለው ግን … ይሄ ለሁሉ ነገር እንደ ፍቱን መድሃኒት የሚታዘዘው የ1ለ5 አደረጃጀት (በቤት ስሙ “ጥርነፋ!”) በቴሌ፣ በውሃና ፍሳሽ፣ እንዲሁም በመብራት ሃይል አልተሞከረም እንዴ? (1ለ5 ያልገባበት የለም ብዬ እኮ ነው!) በቅርቡ እንደውም ይሄ አደረጃጀት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መግባቱን የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩና የመድረክ ፓርቲ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ተናግረዋል (የአካዳሚ ነፃነት ውሃ በላው እንዴ?) ግን እኮ እዚህ እንደውም ዘግይቷል፡፡ በየክልሉ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች፣ የ1ለ5 አደረጃጀት ሥራ ላይ ተተግብሮ አመርቲ ውጤት እንዳመጣ፣ በኢቴቪ መስኮት ብቅ የሚሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እየመሰከሩ ነው (ካድሬ ናቸው እንዳትሉኝ!) ዝም ብዬ ሳስበው (መረጃ የለማ!) 1ለ5 ለተማሪዎች እንኳን ሳይበጅ አይቀርም (ለፖለቲካ ቅስቀሳ ሳይሆን ለጥናት!) ችግር የሚመጣው አንድ ፕሮፌሰር ከአምስት ዶክተር ጋር ይጠርነፍ ሲባል ነው (እዚህ አገር ፍሬን የለማ!) እናም በዚያው ከቀጠለ… አንድ ከፍተኛ ባለሃብት ከአምስት መካከለኛ ባለሃብቶች ጋር ይጠርነፍ መባሉ አይቀርም (ቀይ መስመር ማለፍ ተለምዶ የለ!)
ይሄን ፖለቲካዊ ወግ እየከተብኩ ሳለ፤ “ኢቴቪ ወዳጄ” … አንድ ሰበር ዜና ሹክ አለኝ፡፡ ለስምንት ዓመት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉት አቶ አያሌው ጐበዜ ባቀረቡት “የመተካካት ጥያቄ” መሰረት፣ አስቸኳይ ጉባኤ ተጠርቶ ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው አስረከቡ አለኝ-ኢቴቪ! አይገርምም ፍጥነትና ቅልጥፍናቸው! የህዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮችም አስቸኳይ ጉባኤ እየተጠራ እንዲህ አስቸኳይ እልባት ቢሰጣቸው አልኩ-በሃሳቤ፡፡ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ኢቴቪ ሌላ መረጃ አቀበለኝ፡፡ “የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሙሉ አምባሳደርነት ሹመት ተሰጣቸው” የሚል፡፡ ሌላ ፍጥነት! ሌላ ቅልጥፍና! አትሉም (ከሮቦት ብቻ የሚጠበቅ!) “የመተካካት ሂደት የዱላ ቅብብሎሽ ነው” ያሉት አቶ አያሌው ጐበዜ፤ “ዱላውን ለሚቀጥሉት ወጣት አመራሮች አስረክቤአለሁ” ብለዋል፡፡
እኔን ያልገባኝ ምን መሰላችሁ? የዱላ ቅብብሉ ዓይነት! (ወደ ጐን  የዱላ ቅብብሎሽ አለ እንዴ?) ሌላም ያልገባኝ ነገር አለ፡፡ ወጣቱ ትውልድ ወይም New blood የሚባለው የትኛው ነው? አቶ አያሌው ጐበዜን የተኩት (የቀድሞው ምክትላቸውን ማለቴ ነው!) የአዲሱ ትውልድ አባል ናቸው እንዴ? (“ለሚቀጥሉት ወጣት አመራሮች አስረክቤአለሁ” ስለተባለ እኮ ነው!) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ New blood የሚለው በስንት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን እንደሆነ ግልፅልፅ አድርጐ ቢነግረን ከ“ብዥታ” እንወጣለን፡፡ ወይም ደግሞ የዱላ ቅብብሎሽ ወደ ጐንም ይቻላል ብሎ እቅጩን ይንገረን፡፡ ያኔ አፋችንን ዘግተን እንቀመጣለን (እኔ New blood እንዳልሆንኩ ይታወቅልኝ!)
በመጨረሻ … አንድ ጥያቄ አለኝ፡ አቶ አያሌው ጐበዜ ስልጣናቸውን የለቀቁበትን ምክንያት በፌስ ቡክ ላይ ይፃፉልን!! (“ኢህአዴግ ፌስቡክ መጠቀም ያበረታታል” ሲባል ሰምቼ እኮ ነው!!)

 http://addisadmassnews.com

Tuesday, December 17, 2013

ጉቦ በመቀበል እስረኞችን የለቀቁ ታሰሩ!


ከ11 በላይ ታራሚዎችን በዚህ ሀሰተኛ ሰነድ ከእስር እንዲለቀቁ አድርገዋል
cuffs
ከ300 እስከ 500 ሺህ ብር እየተቀበሉ በሀሰተኛ ሰነድ ታራሚዎችን ከማረሚያ እንዲወጡ አስደርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሶስት የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የስራ ሀላፊዎችና አምስት ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተጠርጣሪዎቹ ኦፊሰር ገብረመድህን አረጋ፣ ረዳት ኦፊሰር ኢሳያስ ከበደና ዋርደር ኢብራሂም መሀመድ ሲሆኑ፥ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የእስረኞች አስተዳደር የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው።
ከእነዚህ የስራ ሃላፊዎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የተቀሩት ግለሰቦች ደግሞ ፥ በንግድ ስራ ይተዳደር የነበረው አቶ ሰለሞን ገለታ፣ አቶ ብሩክ ሀይሌ፣ ወይዘሪት ሳባ ገብረሚካኤል፣ አቶ ናታን ዘላለምና አቶ ቴዎድሮስ ግደይ ናቸው።
የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን  መርማሪ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻ ላይ እንደተመለከተው፥ ከሳባ ገብረሚካኤል ውጪ እነዚህ በንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩ ግለሰቦች ቀደም ሲል በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸውና በማረሚያ ቤት የእስራት ጊዜያቸውን ጨርሰው የወጡ ናቸው።
እንደ መርማሪው ማመልከቻ ሳባ ገብረሚካኤል በኮምፒውተር ፅሁፍ እያገዘቻቸው፥ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ግለሰቦችም ከፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታራሚዎች ከእስር የሚፈቱበትን ትዕዛዝ በሀሰተኛ መንገድ በማዘጋጀት እንዲሁም በሀሰተኛ ፊርማ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ማህተም በማስመሰል አዘጋጅተዋል።
በማረሚያ ቤት የሚገኙና ቅጣታቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆነ 300 ሺህ ብር ከዚያ በላይ ከሆነ ደግሞ 500 ሺህ ብር እየተቀበሉ ፥ ከ11 በላይ ታራሚዎችን በዚህ ሀሰተኛ ሰነድ ከእስር እንዲለቀቁ አድርገዋል ይላል።
የሚያገኙትንም ገንዘብ ለኦፊሰር ገብረመድህን አረጋ፣ ረዳት ኦፊሰር ኢሳያስ ከበደና ዋርደር ኢብራሂም መሀመድ ለተባሉት የማረሚያ ቤቱ የስራ ሀላፊዎች በመስጠታቸው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
በመርማሪው ማመልከቻ መሰረት እነዚህ የስራ ሃላፊዎች የነበሩ ተጠርጣሪዎች የእስር መፍቻ ደብዳቤው በሀሰተኛ መንገድ የተዘጋጀ እንደሆነ እያወቁ ታራሚዎች እንዲፈቱ በማድረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከሶስቱ የስራ ሀላፊዎች ውስጥ ኦፊሰር ገብረመድህን አረጋ ሀሰተኛ የእስር መፍቻ ካቀረበ አንድ ታራሚ 40 ሺህ ብር መቀበሉ ተመልክቷል።
የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻውን የተቀበለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ቢለቀቁ መረጃ ያጠፋሉ የሚለውን የመርማሪውን ተቃውሞ በመቀበል ፥ ጉዳያቸውን ማረሚያ ሆነው ይከታተሉ ብሏል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)

የማንዴላ ሌላኛው ገፅታ!


በአይሁዶች ሚሽናህ ውስጥ “በእድሜ ዘመኑ የሰዎችን ልብ ደስ ለሚያሰኝ መልካም ስራ የተጋ፣ እነሆ የሌሎችን ቀንበር የተሸከመ፣ ከእርሱም ታላላቆችና ታናናሾች ለሆኑ ለወንዶችም ለሴቶችም ጠዋት በሆነ ጊዜ እንደሚገኝ ብርሃን የሆነ፣ እርሱ በሞቱም እንኳ ቢሆን በአምላክና በሰዎች ዘንድ እጅግ ይከብራል፣ ወደ ላይም ከፍ ከፍ ይላል፡፡” የሚል ቃል ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ይህ ቅዱስ ቃል በኔልሰን ማንዴላ ተፈጽሞ እነሆ በዘመናችን ለማየት በቅተናል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ መላ ደቡብ አፍሪካውያን ከፍ ባለ አክብሮትና ፍቅር “ማዲባ” እያሉ የሚጠሯቸው ኔልሰን ማንዴላ፤ በረጅሙ የትግል ህይወታቸው የፈፀሙት ስራ በመላእክት እንጂ በስጋ ለባሽ ሰው የሚፈፀም አይመስልም። የዘር መድልዎና የጭቆና አገዛዝ ቀንበር ተሸክመው፣ ወደር የሌለው ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉበት ያ ረጅሙና እጅግ አስቸጋሪው ጉዞአቸው ለዘመናት ሲገፋ ለኖረው ሰፊው ህዝባቸው፤ ከማለዳ ጀንበር በብዙ እጥፍ የደመቀ የነፃነትና የእኩልነት ብርሃን አብርቶላቸዋል፡፡
“የማይናወጥ ጽኑ እምነት ያለው ተራሮችን ማንቀሳቀስ ይችላል” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው፣ ለእኩልነትና ለአንድነት የነበራቸው መቼም የማይናወጥ ጽኑ እምነት፣ ቀናቶች ሁሉ እስኪያልቁ ድረስ ይገረሰስ የማይመስለው የአፓርታይድ የዘር መድልዎና የጭቆና አገዛዝ፣ እግራቸው ስር አይሆኑ ሆኖ እንዲፈረካከስ አድርጐታል፡፡
ከመላእክት እንጂ ከሰው ልጆች መቸም ቢሆን እንዲህ እንደዋዛ በማይገኘው እፁብ ድንቅ ርህራሄአቸውና ፍፁም ይቅር ባይነታቸው፣ ከዚህ በፊት የትም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ የህዝባቸውን የደቡብ አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን ድፍን የአለማችንን ህዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ በከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት መማረክ ችሏል፡፡ እነሆ በሞታቸውም ጊዜ ቢሆን በአምላካቸው ፊት በእጅጉ ተከብረው፣ በሰው ልጆች ዘንድም  አቻ በሌለው ከፍተኛ ፍቅርና ክብር እንደ ንስር ወደ ላይ፣ ወደ ሰማይ ከፍ፣ እጅግ ከፍ ብለዋል፡፡ ለዘጠና አምስት አመታት ያህል የዘለቀው የኔልሰን ማንዴላ ረጅም የትግል ህይወት፤ በችግርና በፈተና፣ በጽናትና በአይበገሬነት፣ በውድቀትና በድል ታሪኮች የተሞላ ነው ብሎ በቀላሉ መናገር ምናልባት የአንባቢን ንቃተ ህሊና አሳንሶ እንደመገመት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእሳቸው የህይወት ታሪክ እንደነዚህ ባሉ ታሪኮች የተሞላ መሆኑን ድፍን አለሙ በሚገባ ያውቀዋልና፡፡
ኔልሰን ማንዴላ፤ በአፓርታይድ አገዛዝ የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸው ሮቢን ደሴት በሚገኘው ጥብቅ ወህኒ ቤት ውስጥ ለሀያ ሰባት አመታት በእስር የማቀቁት የቀለም ትምህርት አሊያም የሙያ ክህሎት ስልጠና በመውሰድ ሳይሆን የኖራ ማዕድን በመቆፈር ነበር፡፡ ይህም ለተለያዩ የእፎይታና የመተንፈሻ አካላት በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ አጋልጧቸዋል፡፡ ከሀያ ሰባት አመታት አስከፊ የእስር ቅጣት በሁዋላ ተፈተው፣ የሮቢን ደሴት ወህኒ ቤትን ለቀው ሲወጡ፣ ሳምባቸው በኖራ ብናኝ ክፉኛ ተጎድቶ በከፍተኛ የመተንፈስ ችግር እየተሰቃዩ ነበር፡፡ ይህም ብቻ አልነበረም፡፡ እስር ቤት ከገቡ ከአስራ አራተኛው አመት ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ የእንባ አመንጪ እጢያቸው በኖራና በአስቤስቶስ ብናኝ ሙሉ በሙሉ በመጎዳቱ፣  ስሜታቸውን እንባ አውጥተው በማልቀስ መግለጽ አይችሉም ነበር፡፡
የቀድሞው የኬጂቢ ኮሎኔል፣ የዛሬው የራሺያ ቆፍጣና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ስለ ራግቢ ጨዋታ የፈለገውን ያህል ቢያወሯቸው ጨርሶ አይሞቃቸውም አይበርዳቸውም። የጂዶ ጨዋታን ነገር ካነሱላቸው ግን መላ ስሜታቸው የሚነቃውና ሰውነታቸውን የሚነዝራቸው ከመቅጽበት ነው።
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜም የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ነፍሳቸው ነው፡፡ አደባባይ ወጥተው ሲጫወቱ አይታዩ እንጂ የእረፍት ጊዜአቸውን በአብዛኛው የሚያሳልፉት ከመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ ከልጃቸው ጋር ነጭ ላብ እስኪያልባቸው  ድረስ የቅርጫት ኳስ በማልፋት ነው፡፡ እርግጥ ነው ማዲባ እንደ ቭላድሚር ፑቲን ጂዶ ሲታገሉ ወይንም እንደ ፖል ካጋሜ በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር የቅርጫት ኳስ ሲጫወቱ ታይተው አያውቁም፡፡ ልጫወት ቢሉም የማያወላዳው ጤናቸው፣ ከተጫጫናቸው እርጅና ጋር ተዳምሮ ይህን መሰሉን እድል እንዳልሰጣቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ ሀገራቸው የአፍሪካና የአለም የእግር ኳስ ዋንጫ እንዲሁም የራግቢ የአለም ዋንጫ ውድድሮችን እንድታዘጋጅ ያደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ፣ አዘጋጅ ከሆነች በኋላም የሀገራቸውን ብሔራዊ የእግር ኳስና የራግቢ ቡድን ማሊያ ለብሰው ውድድሩ በሚካሄድበት ስታዲየም በመገኘት የሰጡት የሞቀ ድጋፍ፣ ብዙዎች ማንዴላ የእግር ኳስና የራግቢ ስፖርት ቅልጥ ያለ ደጋፊ ናቸው ብለው እንዲገምቷቸው አድርጓል፡፡
እውነቱ ግን ይህ አይደለም፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የእግር ኳስም ሆነ የራግቢ ጨዋታ አድናቂ አልነበሩም፡፡ እርሳቸው የሚወዱትና የሚያደንቁት የስፖርት አይነት ቦክስና የረዥም ርቀት የሩጫ ውድድሮችን ብቻ ነበር፡፡ ሀያ ሠባት አመታትን ባሳለፉበት የሮቢን ደሴት ወህኒ ቤት ውስጥ ኖራና አስቤስቶስ ለመቆፈር ዶማና አካፋቸውን ይዘው ከመውጣታቸው በፊት ዘወትር ጧት ጧት የቦክስ ልምምድ ያደርጉ ነበር፡፡
“ረዥሙ የነፃነት ጉዞ” በሚል ርዕስ ባሳተሙትና የህይወት ታሪካቸውን በተረኩበት መጽሀፍ ውስጥ የቦክስ ስፖርትን ሲገልፁ “የቦክስ ስፖርት ሳይንሱ እንጂ ድብድቡ አዝናንቶኝ አያውቅም፡፡ አንዱ ራሱን ለመከላከል እንዴት ሰውነቱን እንደሚያንቀሳቅስ፣ ሌላው ደግሞ ለማጥቃትና ለመከላከል እንዴት ያለ ስትራተጂ እንደሚጠቀም፣ አንዱ ሌላኛውን እንዴት እንደሚቀድመው ሳይ ግን በጣም እገረም ነበር” በማለት ጽፈዋል፡፡
ለኔልሰን ማንዴላ የቦክስ ስፖርት ከዚህ ያለፈ ሌላ ትርጉምም ነበረው፡፡ ይህንንም በመጽሃፋቸው እንዲህ በማለት ገልፀውታል:- “የቦክስ ስፖርት ነፃና ዲሞክራሲያዊ ነው፡፡ በቦክስ ሪንግ ውስጥ ማዕረግ፣ እድሜ፣ ቀለምና ሀብት ምንም ቦታ የላቸውም፡፡ ፖለቲከኛ ከሆንኩ በኋላ የምሬን ተቧቅሼ አላውቅም፡፡ ዋናው ፍላጐቴ ልምምዱ ላይ ብቻ ነበር፡፡ አድካሚው ልምምድ ጭንቀትና ውጥረትን ማስተንፈሻ ድንቅ መሳሪያ ሆኖልኝ ነበር፡፡ ከባድ የቦክስ ልምምድ ካደረግሁ በኋላ አዕምሮዬንም ሆነ አካሌን ቅልል ይለው ነበር”
ኔልሰን ማንዴላ ለቦክስ ስፖርት የነበራቸውን ስሜት በመጽሀፋቸው ላይ በይፋ ከመግለፃቸው በፊት ዋልተር ሲሲሉስን ከመሳሰሉት የቅርብ የትግልና የእስር ቤት ጓዶቻቸው በቀር የሚያውቅ ሰው እምብዛም አልነበረም። የአለም የቦክስ ሻምፒዮን የነበረው አሜሪካዊው ሹገር ሬይ ሊዎናርድ፣ የአለም ሻምፒዮንነት ክብር የተቀዳጀበትን ቀበቶ በስጦታ ያበረከተላቸውም ይህንን ታሪካቸውን ጨርሶ ሳያውቅ ነው፡፡ ሹገር ሬይ ሊዎናርድ ያበረከተላቸው ይሄው የሻምፒዮንነት ቀበቶ፣ ሶዌቶ በሚገኘው የኔልሰን ማንዴላ ቤተሰብ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጦ በጐብኝዎች እየታየ ይገኛል፡፡  ዛሬ ኔልሰን ማንዴላ የሚለው ስም በአለማችን አራቱም ማዕዘናት እንደ ጉድ የናኘና በቢሊዮን በሚቆጠሩ የአለማችን ህዝቦች ዘንድ በሚገባ የታወቀ መሆኑን አሌ ብሎ መከራከር ጨርሶ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ከ1926 ዓ.ም በፊት ግን የማንዴላ ወላጆች ሮሊህላህላ ማንዴላ እንጂ ኔልሰን ማንዴላ የሚል ስም ያወጡለት ወይም በዚህ ስም የተመዘገበ ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ለሁሉም ተማሪዎች የክርስቲያን ስም ማውጣት ይገባል በሚል ኔልሰን የሚለውን ስም ያወጣላቸው፣ የዘጠኝ አመት ብላቴናና የሜቶዲስት ቤተክርስቲያን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆነው ያስተምራቸው የነበረ መምህራቸው ነበር፡፡
ኔልሰን ማንዴላ ሲገረዙ የወጣላቸው ስም ዳሊ ቡንጋ የሚል ሲሆን ትርጉሙም የባህላዊው የቡንጋ አመራር አካል መስራች ማለት ነው፡፡ በአብዛኛው ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ በአክብሮት የሚጠሩበት “ማዲባ” ደግሞ የሚለው የጐሳ መጠሪያ ስማቸው ነው፡፡
ለኔልሰን ማንዴላ በተዘጋጀው የመታሰቢያ ስነ ስርአት ላይ ንግግር ካደረጉት መሪዎች አንዱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ናቸው፡፡ እሳቸውም ኔልሰን ማንዴላ ለነፃነት ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት በማውሳት፣ አለም ከእሳቸው ህይወት ጠቃሚ ልምድ ሊቀስም ይገባል ብለዋል፡፡  እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ግለሰብ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ያደረጉት ንግግር እንከን የለሽ ነው፤ እንደ ሀገር ከታሰበ ግን በጣም ኮሚክ ነው። ለምን ቢባል የአፓይታይድን ስርአት ሲያራምድ ከነበረው የደቡብ አፍሪካ የነጮች መንግስት በበለጠ የኔልሰን ማንዴላን የነፃነት ትግል የተቃወመች፣ በመጨረሻም ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና ጨርሰው ሀገራቸው እንደገቡ እግር በእግር ተከታትላ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ፣ ከዚያም የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸው ለሀያ ሠባት አመታት በወህኒ ቤት እንዲማቅቁ ያስደረገችው አሜሪካ ስለነበረች ነው፡፡ ይህም አልበቃ ብሏት እስከ 2008 ዓ.ም ደረስ ኔልሰን ማንዴላንና ይመሩት የነበረውን የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በአሸባሪና በአሸባሪ ድርጅትነት መዝግባ ይዛቸው ነበር፡፡
ኔልሰን ማንዴላ፤ ኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ለስድስት ወር የተሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና አጠናቀው ሲመረቁ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ሽልማትም፣ ማስታወሻም የሚሆን አንድ ሽጉጥ ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ ይህንን ሽጉጥ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት አንድ ሰዋራ ቦታ ላይ ቀብረውት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከቀበሩበት ፈልገው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ሽጉጡን ፈልጐ ማግኘት ከቻለ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ቢሉም ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ አገኘሁ ያለ የለም፡፡ 

 http://addisadmassnews.com


እንደኔ እና እንደኔ ዘመን ልጆች…


- በኤሮግራም ደብዳቤ የተፃፃፋችሁ
- ራሺያ እጅ ስራ ተሰርቶ የመጣ ፎቶ ቤታችሁ የነበረ
- የካሴት ክር ለማጠንጠንና የምትፈልጉትን ዘፈን ለመስማት በእርሳስ ወይ በእስኪብርቶ ስታሽከረክሩ የዋላችሁ (ኤ እና ቢ የተምታታባችሁ፡ ወደፊት እና ወደ ኃላ የተደበላለቀባችሁ)
- የተቆለፈ ስልክ በሹካ፣ በፀጉር ማስያዣ ስትደውሉ እጅ ከፍንች የተያዛችሁ
- የማይክል ጃክሰንን "አይ አም ባድ" "አምቤ አምቤ" እያላችሁ ያቀነቀናችሁ፡ "ፋንኪ ታውን"ን "ኮቱም ጃኬቱም
ቆሽሿል "ብላች...ሁ ያስነካችሁ
- ፀጉራችሁን በእሳት በጋለ ሹካ የተተኮሳችሁ
- የሰኞ ጠዋት የግል ንፅህና ፍተሻ ያማረራችሁ
- ጠዋት ጠዋት ከኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ጋር "ኢንተርናሲዮናል"ን ልባችሁ እስኪፈርጥ ያቀነቀናችሁ፡
- "ጉልቴ ዘ ላንድ ሎርድ"፣ ሽልንጌን"፣ "የቡልቻ ልብ ነኝ"፣"አብዲሳ አጋ"፣ "ፋኖስና ኩራዝ "ከልባችሁ የቀረባችሁ
- "አፕሮች"፣ "ጋይድ "እና "ኮመን ሚስቴክ ኢን ኢንግሊሽ" የተባሉት መፅሃፍት መቼም የማይረሷችሁ
- ኮኮስ እየለቀለቃችሁ ያደጋችሁ
- የቢራ ጠርሙስ የሚመስለውን የፓራፊን ቅባት ክዳን በሚስማር የበሳችሁ
- እንሾሽላ ውስጥ እጅና እግራችሁ እስኪቃጠል የሞቃችሁ
- የአጥሚት ድስት ቂጥ እየተሻማችሁ የላሳችሁ
- ጆሯችሁን ተበስታችሁ ሰበዝ የሰካችሁ
- ቅልልቦሽ በየደረጃው ጣታችሁ እስኪፋፋቅ የተጫወታችሁ
- ቅጠል ቆርጣችሁ፣ በክር አስራችሁ፤ እግራችሁ እስኪጣመም ጢቢጢቢ የተጫወታችሁ
- ለኳስ መስሪያ የአባቶቻችሁን ካልሲ ከቁጥር ያጎደላችሁ
- ለሱዚ መጫወቻ የእናቶቻችሁን /የታላቅ እህታችሁን ስቶኪንግ አበላሽታችሁ የተገረፋችሁ
- በሾላ ላስቲክ ምን የመሰለ ኳስ የገነባችሁ
- ስልክ እንጨት ላይ ኳስ አስራችሁ ቴዘር የተጫወታችሁ
- ክረምትን በቆርኪ፣ በብይና በጠጠር ጨዋታ ያሳለፋችሁ
- በዱቤ ዱቄት ላስቲክ ደብተር የያዛችሁ
- በ" ሰይ ባንከረባብት"የብይ ሃብታችሁን ያደረጃችሁ
- አረንጓዴ- አረንጓዴ- ቢጫ- ቢጫ- ቀይ! አንዴም እየዘለላችሁ፣ አንዴም ቁጢጥ እያላችሁ፡ ከዚያም እንደስልክ እንጨት እየተገተራችሁ የፈነደቃችሁ
- አሌ ቡም የተጫወታችሁ
- የልጅነት ኩላሊታችሁ ከሹሌ እርግጫ የተረፈላችሁ
- በ”አኩኩሉ አልነጋም” ጨዋታ አልጋ ስር ተደብቃችሁ በዚያው እንቅልፍ ያሸለባችሁ
- "ፒቲ ጎል" ሰርታችሁ ኳስ የተራገጣችሁ
- የዛሬን አያድርገውና መጠጥ እንዲህ ሳይስፋፋ ሻሜታ በመጎንጨታችሁ የተገረፋችሁ
- ከባድ ጥፋት ፈፅማችሁ በሳማ የተለበለባችሁ፡ በርበሬ የታጠናችሁ
- እስኪብርቶና እርሳስ ጣቶቻችሁ መሃል ተደርጎ ክፉኛ የተቀጣችሁ፡ በባለእንጨቱ ማስመሪያ የተገረፋችሁ
- እጅ በጆሮ ይዛችሁ መቀመጫችሁ በቺንጋና በቁራጭ የውሃ ጎማ ያረረ

…እስቲ እንያችሁ!

ሕይወት እምሻው

Monday, December 16, 2013

”ፖለቲካ ሀጢአት ነው ወይ? ” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቅ አጭር እና ግልፅ ምላሽ


በሳምንቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ደብረዘይት ደብረ መድሃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስያን  ባዘጋጀው የመንፈሳዊ ጉዞ ላይ Gubaeበብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ተሳትፈዋል።መርሃግብሩ ላይ ከምዕመናን እና በቀጥታ በማኅበራዊ ድህረገፆች ለአባቶች የጥያቄ እና መልስ መርሃግብር ተዘጋጅቶ ነበር። ለተነሱ ጥያቄዎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ መስጠታቸው ከማኅበሩ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ የተገኘው መረጃ ይገልፃል።ምእመናን ከእንደዚህ አይነት መርሃግብሮች እና ከሊቃውንቱ ቀጥተኛ እና  ትክክለኛ መረጃ ማግኘታቸው  ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ከገፁ ላይ የተገኘውን ከእዚህ በታች እንዲህ ይነበባል-
”ቀጥሎ የሚኖረን መርሐ ግብር የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ሲሆን ሊቃውንቱ መልአከ ታቦር ተሸመ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል፤ መጋቤ ሐዲስ ደጉ ዓለም ካሣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር፤ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ መምህር፤ ሲሆኑ ከምዕመናን ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ደግሞ በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ አቅራቢነት ያስተናግዳሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይመለስልን የምትሉት ጥያቄ ካላችሁ በውስጥ መስመራችንም ሆነ በ ኢ-ሜላችን ብትሉክልን እናስተናግደዋለን፡፡
……………………

ጥያቄ 2 . ቅዱስ ጳውሎስ ሀገራችን በሰማይ ነው ስላለ እኛ ክርስቲያኖች በምድራዊት ሀገራችን ላይ እንዴት እንስራ?

እግዚአብሔር ሰማይ ዙፋኔ ምድርም የእግሬ መረገ ናት እንዳለ አሁን ዛሬ ተቀምጠን የምንዘምርበት፣ የምንማርበት፣ የምናመሰግንበት፣ ይሄ ምድርም የእግዚአብሔር ፍጥረት ስለሆነ ሰው ለሀገሩም ሊሰራ ሊሞት ይገባዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአድዋ ድል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ሱታፌ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ መልአከ ታቦር ተሸመ ዘሪሁን የሊቃውንት ጉባኤ አባል ……………………..
ጥያቄ 4 ፡ ፖለቲካ ሀጢአት ነው ወይ?

ሰው በዚህ አለም ሲኖር ከሀጢአት በቀር በአለም ያለው ሁሉ ይመለከተዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እነ ዳዊት፣ እነሰሎሞን ፖለቲከኞች ነበሩ ስለዚህ ሀጢአት አይደለም ሀጢአት የሚሆነው አያያዙን ማወቅ ሲያቅት ነው፡፡ ወተት መጠጣት ሀጢአት አይደለም በረቡዕ ከተጠጣ ግን ሀጢአት ይሆናል፣ ቢላዎ ባለሞያ ሴት ካገኘችው ያገለግላል ባለጌ ካገኘው ሰው ይጎዳበታል ፖለቲካም አያያዙን ካወቅንበት ሀጢአት አይደለም፡፡ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለምዓየሁ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ መምህር።”
ምንጭ - https://www.facebook.com/mkidusan

የመዲናችን ገመናዎች በ‹‹ሮዛ›› መጽሐፍ ውስጥ ሲቃኙ



ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “በመዲናዋ ምስጢራዊ የወሲብ ገበያ ደርቷል” በሚል ርእስ በመታሰቢያ ካሳዬ የተጻፈውና በህብረተሰብ አምድ ላይ የተስተናገደው ጽሁፍ፣ ከሰሞኑ ከመጻሕፍት አዟሪዎች ደረት ላይ የማይጠፋውንና በማህበራዊ ድረ ገጾች ትኩስ መነጋገሪያ የሆነውን “ሮዛ” የተሰኘ መጽሀፍ አስታወሰኝ። ሁለቱም ጸሀፍት ለአብዛኞቻችን አዲስ አበቤዎች እንግዳ የሆኑና የማናውቃቸውን የመዲናችንን አስገራሚ ድብቅ እውነታዎች አስቃኝተውናል፡፡ የዛሬ ጽሁፌ አቢይ ትኩረት ግን “ሮዛ” በሚል ርእስ ለህትመት የበቃውን የሮዛ ይድነቃቸው የእለት ማስታወሻዎች ስብስብ መጽሀፍ ላይ ሂሳዊ ምልከታን ማቅረብ ነው፡፡
የእለት ማስታወሻዎች ተሰብስበው በመጽሀፍ መቅረባቸው በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ውስጥ የተለመደ አይደለም፤ በቅርብ አመታት ውስጥ ለህትመት የበቁ የስመ-ጥር ኢትዮጵያውያን ግለ-ታሪክ መጻህፍት ከእለት ማስታወሻዎች ስለመጠናቀራቸው እስካሁን ያገኘሁት ተጨባጭ ፍንጭ የለም፡፡
ጎምቱው ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ማንኛውንም የተለየ ቅጽበት ባስተዋለ ቁጥር ማስታወሻ ደብተሩን ከኪሱ አውጥቶ የመሰጠውን ቅጽበት፣ ሃሳብ ወይም ክስተት በዝርዝር የመጻፍ ቋሚ ልምድ እንደነበረው የቀድሞ የስራ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ በአንድ አጋጣሚ አጫውተውኛል፡፡ ከነስህተትና ድብቅ አጀንዳቸውም ቢሆን ከነዚህ ማስታወሻዎች ተነስቶ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”፣”የደራሲው ማስታወሻ” እና “የስደተኛው ማስታወሻ” የተሰኙትን መጻህፍት ለህትመት እንዳበቃ ራሱ በስደተኛው ማስታወሻ ላይ ይገልጻል፡፡ ዛሬ ለዳሰሳ የመረጥኩት “ሮዛ” የሚል ስያሜ የተሰጠው መፅሐፍም ሮዛ በምትባል ኢትዮጵያዊት ኮማሪት የተጻፈ የግል ማስታወሻ ነው፡፡ ምንም እንኳ የግል ማስታወሻዎቿ አርታኢ እጅ ላይ ወድቀው መጠነኛ የይዘትና የቅርጽ ለውጦች ቢደረጉባቸውም የግል ማስታወሻዎችን ወደ መፅሐፍ ቀይሮ በማሳተም ረገድ ምናልባትም ቀዳሚ ስራ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡
ከዚህ የስነ ጽሁፍ ዘውግ ጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በውል የተዋወቅነው አዶኒስ ከአመታት በፊት ወደ አማርኛ ተርጉሞ ባቀረበልን “The Diary of Ana Frank” (የአና ፍራንክ ማስታወሻ) በሚለው መጽሀፍ ይመስለኛል፡፡ አና እነዚህን በመላው አለም በበርካታ ቋንቋዎች ተተርጉመው በሚሊዮኖች ኮፒ የተሸጡላትን የእለት ማስታወሻዎች የከተበችው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በሆላንድ ርእሰ መዲና አምስተርዳም ከናዚዎች በተደበቀችባት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ በድርሰት ስራቸው የተደመምንባቸው በርካታ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ደራሲያን ስራዎች ከደራሲያኑ የእለት ማስታወሻዎች የተወለዱ ነበሩ፡፡ ለአስረጅነት የቨርጂንያ ዉልፍን፣ አዳም ረታ በ”እቴ ሜቴ ሎሚ ሽታ” ድርሰቱ ውስጥ የሚያነሳትን ዝነኛዋ የኢሮቲክ ልቦለዶች ደራሲ የሆነችውን አናይስ ኒንን፣ ለየት ባሉት አጫጭር ልቦለዶቹ የሚታወቀውን ፍራንዝ ካፍካን፣ የዝነኞቹን አሜሪካዊያን የኢሮቲክና ሮማንቲክ ልቦለድ ደራሲዎቹን የኤሪካ ዮንግንና የሳንድራ ብራውንን ስራዎች ማንሳት እንችላለን፡፡
አናይስ ኒን “የኔም ሆነ የሌሎች እውነተኛ ማንነት በአንዳች አይነት የስሜት ጡዘት ወይም ቀውስ ውስጥ ስለሆነ እነዚህ ቅጽበቶች በምንም ሁኔታ እንዲያመልጡኝ አልፈቅድም፤ በፍጥነት አንዳች ሳላስቀር በእለት ማስታወሻዎቼ ላይ አሰፍራቸዋለሁ” ብላ ነበር፡፡ ፍራንዝ ካፍካ  “በህይወታችን የተለያዩ ምእራፎች ያሳለፍናቸውን የደስታና የሀዘን፣የጭንቀትና የፈንጠዝያ፣የድሎትና የውጣ-ውረድ ጊዜያት በእለት ማስታወሻዎቻችን በኩል መለስ ብለን ስንመለከታቸው በርግጥም መኖራችንን፣ ከመኖርም አልፈን የኖርነውን በጽሁፍ ለዘለቄታው ማስቀመጣችንን በውል እንገነዘባለን፤ ከእለት ማስታወሻችን በተሻለ የኖርነውን ህይወት፣ ቅጽበታዊ ስሜቶቻችንን ሳይቀር በግልጽነትና በታማኝነት የሚዘግብልን ድርሳን የለም” ይላል፡፡ ስመ - ጥሩ ደራሲ ዴቪድ ሴዳሪስ በበኩሉ “የእለት ማስታወሻዎቻችን ቢያንስ በሁለት  ምክንያቶች ይጠቅሙናል፤ ባለፈ ብስጭታችን፣ ስቃያችን፣ ስህተታችን፣ ድክመታችን፣ እንጭጭነታችንና ውጣ ውረዳችን ዘና እያልን እንዳንደግማቸው ትምህርት እንወስዳለን፤ ‘መጋቢት 3 ቀን 1998 ላይ እኮ እንዲህ ብለህ ነበር’ ብለን ክርክር በመጀመር ሙግት እንረታበታለን” ሲል ተናግሯል፡፡
ሮዛ ራሷም ለዳሰሳ በመረጥኩት ማስታወሻዋ ውስጥ እንደምትገልጸው ኮሌጅ የበጠሰች ሴተኛ አዳሪ ናት። ለሮዛ ዳዬሪዋ (የእለት ማስታወሻዋ) ብቸኛ የሚስጥር ጓደኛዋ የሆናት ይመስላል፤ ይህን የግል ማስታወሻዋን ነው እንግዲህ አደባባይ ያሰጣችው፡፡ በዚህች ምድር ላይ ገሚስ አድሜን ያሳለፈች የአገር ልጅ ለነገ ሳትል ጥብቅ ሚስጢሯን ሁሉ በመጸሐፍ መልክ ድንገት ስትዘከዝክ “ለምን?” ማለታችን አይቀርም፡፡ እኔም ለምን ብዬ ደጋግሜ ጠየቅኩ፡፡ መላምት እንጂ መልስ አላገኘሁም፡፡ ምናልባት ከብዙዎቹ ሴተኛ አዳሪዎች በተለየ ኮሌጅ መበጠሷ ህይወቷን ለሌሎች በማሳየት ማህበረሰባዊ ግዴታዋን ለመወጣት አስባ ይሆን?ምናልባት ሲሶ እድሜዋን የኖረችበትንና እሷ እምብዛም የማትቆጭበትን የቡና ቤት ህይወት በመተረክ ርካሽ ዝናን በአቋራጭ ለማግኘት አቅዳስ ይሆን? ነው ወይንስ ሙአመር ጋዳፊን ማግኘቷን እንደ ታላቅ ስኬት በመቁጠር እዩልኝ ስሙልኝ እያለችን ይሆን? እነዚህን ሁሉ መላምቶች ለመሰንዘር የተገደድኩት መጽሀፏ ውስጥ ምንም አይነት አስረጅ ባለማግኘቴ ነው፡፡ በመጸሐፉ የመጀመርያዎቹ ጥቂት ገጾች መረዳት የቻልኩት ሮዛ  ከያንዳንዱ የ ‹‹ሾርት›› እና የ‹‹አዳር›› ቢዝነስ በኃላ የዕለት ማስታወሻ የመያዝ ልምድ እንዳላት ብቻ ነው፡፡ ምናልባት መጸሐፉ የራሱ መግቢያ ተበጅቶለት ቢሆን ኖሮ እኛም ከመላምት በዳንንና ስለ ጸሐፊዋ ግብና ተልእኮ ብዙ መረዳት በቻልን ነበር እላለሁ፡፡ “ከሾፌር፣ ከሴተኛ አዳሪ፣ ከዘበኛና ከቤት ሰራተኛ የምታመልጥ አንዳችም የአለም ሚስጥር የለችም” በሚል መሪ ቃል ሽፋኑን ያደመቀው ይህ መጸሐፍ፤ ደራሲዋ የሙአመር ጋዳፊ ድንኳን ውስጥ የዘለቀች ‹‹ጀግና›› መሆኗን ገልጾ የልብ ምታችንን ያፈጥንብናል፡፡
በእርግጥ ይህ መጽሀፍ እስካሁን ካነበብኳቸውና ተመሳሳይ ይዘት ካላቸው መጻህፍት በብዙ መልኩ እንደተለየብኝ አልክድም፡፡ መጽሀፉ በርካታ አመታትን በዲፕሎማቶችና ከፍ ባለው ማህበረሰብ ዙርያ በሴተኛ አዳሪነት ህይወት ውስጥ ባሳለፈች፣ ከአንድም ሁለት ሶስት ዓለምአቀፍ ቋንቋ በምትናገር የተማረችና፣ ሯሷን በንባብ የገራች ኮማሪት መጻፉ ብቻ አይደለም ልዩ የሚያደርገው። አጻጻፏ በራሱ አንባቢ ላይ በግድ ቅጽበታዊ ስሜትን የማጋባት ባህሪ አለው፡፡ ስታዝን ይከፋናል፣ስትደሰት እንስቃለን፣ስትበግን እንንገበገባለን፣ ስትስቅ ፈገግ እንላለን…በማያገባን እያስገባችን ስሜታችንን ትሾፍረዋለች፡፡ እለታዊ ማስታወሻዋ የእንቶ ፈንቶ ጉዳይ ቢመስልም የዘመናችንን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣፣ባህላዊ፣ሃይማኖታዊና ስነልቦናዊ እውነታዎች በማስታወሻዎቿ በኩል በግርድፉ ታሳየናለች። ይህንን ደግሞ ከአንዲት ኮማሪት የምንጠብቀው ስላይደለ እንገረማለን፡፡ የቡና ቤት ሴት ሆናም የኛን የሞራልና መንፈሳዊ ዝቅጠታችንን ጥልቀት ስትነግረን እንድንሸማቀቅ አድርጋ ነው፡፡ በዕለት ማስታወሻዋ የመኝታ ገድሎቿን እየተረከችልን እሷን ሳይሆን እኛን እንድንታዘብ የሚያደርግ ስሜትን ትረጭብናለች፡፡ ይህንን ማድረግ የቻለችው ከልቧ በፍጹም የተቆርቋሪነት ስሜት ስለምትጽፍ ይሆናል፡፡ ከኪነ-ጥበብ ስራ በላይ ዘመንን ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ ነገር ያለ አይመስለኝም ነበር፤ የፈጠራ ስራ ባልሆኑት የሮዛ የግል ማስታወሻዎች ውስጥ ይህንን ሁለንተናዊ የዘመን መንፈስ መመልከቴ ሳያስገርመኝ አልቀረም፡፡
“ሮዛ” እንደ “መሀልዬ መሀልይ ዘ ምናምን” እያሉ ከተድባበ ጥላሁን ቱባ ስራ በኋላ የልብ ካውያ እንደሆኑብን ገበያ ተኮር መጻህፍት የገድለ ወሲብ ጥርቅም አይደለም፤ ወይም ደግሞ ከጋዜጣ ወደ መጽሐፍ እንደተገለበጡት ስራዎች የቡና ቤት ሴቶችን ግልብ ቃለመጠይቅ ወደ ጽሁፍ ቀይሮ ለንባብ ያበቃም አይደለም፡፡ በእርግጥ እነዚህ መጻህፍትም ቢሆን ይብዛም ይነስ በተለያየ ዘመን እና ቦታ የተኖረን ህይወት ለዘለቄታው ለመጪዎቹ ትውልዶች የሚያስተላልፉ ቋሚ ሰነዶች እንደመሆናቸው ሚናቸውንና ጠቀሜታቸውን እያሳነስኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። የስብሀት ገብረ እግዚአብሄር “ሌቱም አይነጋልኝ” መጽሀፍ ባይኖር በንጉሱ ዘመን በውቤ በረሀ የተኖረውን ህይወትና የዘመን መንፈስ እንዴት ማወቅ ይቻለን ነበር?የአለማየሁ ገላጋይ “አጥቢያ” ልቦለድ ባይኖር አሁን ሙሉ በሙሉ በፈረሰችው አራት ኪሎ ውስጥ የተኖረውን ህይወት፣የነበረውን ማህበራዊ መስተጋብር መጪዎቹ ትውልዶች እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? በማህበረሰብ ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራንስ ከተጻፉ መዛግብት በላይ ምን አይነት ተጨባጭ መነሻ ይኖራቸዋል?
ከላይ ከተጠቀሱት መጻህፍት በተለየ የሮዛ ህይወት በአንድ ሰፈር የተገደበ አይደለም፤የስራዋ ባህሪ ሆኖ መላው አዲስ አበባን ያካልላል፡፡ የሮዛ ህይወት ከድብቅ (ህቡእ)የመዲናችን የአስረሽ ምቺው ቪላዎች እስከ ሼራተን ቪላ እና የሊቢያው መሪ የጋዳፊ ድንኳን ድረስ ይዘልቃል፡፡ ጋዳፊ የአፍሪካ ህብረት አመታዊ ስብሰባን አስታከው የሀበሻ ቆነጃጅትን ለገዙት ‹‹ኤር አፍሪክ›› አየር መንገድ በሆስቴስነት ሲመለምሉ ሮዛ እንዳገኘቻቸው ትገልጻለች፡፡ ከሳቸው ጋርም ባረፉበት ሼራተን ቪላና በድንኳናቸው ውስጥአጭር ሆኖም አስገራሚ ቆይታ ማድረጓንም ትተርክልናለች፡፡ ሮዛ በመጸሕፏ እንደነገረችን ከሆነ ጋዳፊ በርግጥም ወፈፌ ነበሩ። ይህን ቆይታዋን “ከጋዳፊ ጋር ድንኳን መጋፈፍ” በሚለው የመጽሀፉ ሰፊ ምእራፍ ውስጥ በዝርዝር ገልጻዋለች፡፡ ከአመታት በፊት እዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ጋዳፊ በሼራተን ስላካሄዱት የሆስቴስ ምልመላ አጠቃላይ ሂደት በስፋት ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ምናልባት ሮዛ በዚሁ ምልመላ ወቅት አንዷ ታዳሚ መሆኗን መገመት ይቻላል፡፡
በ”ሮዛ”ውስጥ 29 በቀላሉ ከአእምሮ የማይጠፉ ታሪኮች አሉ፡፡ እንደገመትኩት አርታኢው በታሪኮቹ መረጣ ላይ ዋናውን ሚና ሳይወጣ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ለአመታት ከጻፈቻቸው በርካታ የእለት ማስታወሻዎች ውስጥ በሰው ዘንድ ልዩ ስሜት የሚፈጥሩትን ታሪኮች ለማወቅ ሙያዊ ትኩረትና ክህሎት ይፈልጋል፡፡
በ”ሮዛ” ውስጥ በመጀመሪያ ላይ የምናገኘው ታሪክ “ኮሌጅ በጠስን” የሚለውን ነው፡፡ ሮዛ በዚህ ታሪክ ውስጥ የትምህርት ፖሊሲያችን የደረሰበትን ዝቅጠት፣ የራሷንና የኮሌጅ ጓደኞቿን ህይወት በማውሳት ታሳያለች፤
…ኮሌጅ የበጠሱ የኔ “ባቾች” እንዳሁን ዘመን ተመራቂዎች ሁሉም ኮብልስቶን አንጣፊ አልሆኑም፡፡ በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ አልጋ አንጣፊ የሆኑም አሉ፡፡ እንደኔ እና እንደወይንሸት የተማረ ሸሌ ሆነው የቀሩም አሉ፡፡ እንደ መዲና፣እንደ ራሄል፣እንደ ሂዊ፣እንደ ፎዚያ፣ እንደ ጠይባ አረብ አገር ለግርድና የሄዱም አሉ፡፡ እንደ አብዱልሰመድ(ወሎዬው) በአካውንቲንግ ተመርቀው የመን አገር ፍየል ለማገድ የተሰደዱም አሉ፡፡እንደ ምስኪኑ ሀብትሽ ሰፈር ውስጥ ጸጉር አስተካካይ የሆኑም አሉ፡፡ ሀብትሽ “ አታካብዱ ያው ነው፣ድሮም በጭንቅላቴ ነበር የምሸመድደው አሁንም ጭንቅላት ነው የምከረክመው፤አሁንም ድሮም ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ነኝ!” እያለ ራሱ ላይ ይቀልዳል፡፡ የክላስ ልጆችን ሳስብ እንደ ሀብትሽ አንጀቴን የሚበላኝ ሰው የለም፡፡ ሀብትሽ ለአራት አመት “ስፔስ” እየተመላለሰ፣አይኑ እየተጨናበሰ፣እንቅልፍ እንዳያሸንፈው እግሩን በሳፋ እየዘፈዘፈ፣ ሌት-ተቀን ትምህርቱን ሲሸመድድ ቢኖርም ያቺ ቆሽማዳ ህይወቱ ፈቀቅ አላለችም…(ገጽ-5)
በመጽሀፉ ውስጥ “ዋለልኝ” በሚለው ታሪክ ውስጥ አቸኖ የተባለውን የቺቺንያ ለማኝ እናገኛለን፤ዋለልኝ እንግሊዝ ለንደን ውስጥ በሚገኝ አንድ ግዙፍ ኩባንያ ውስጥ በስራ አስኪያጅነት የሚሰራና በርካታ ሺህ ፓውንድ ደሞዝ የሚከፈለው የቀድሞ የኢህአፓ አባል ነው፡፡ በኢህአፓ ትግል ወቅት በደረሰበት ስነ ልቦናዊ ችግር ምክንያት ወሲብ መፈጸም አይችልም፡፡ የሴት ገላ አቅፎ ለመተኛትም የቻለው በእንግሊዝ ቆይታው ረጅም ጊዜ በወሰደ የስነ ልቦና ህክምና ነው፡፡ በዚህ ቅንጭብ ታሪክ ውስጥ ሮዛ ተራ የህይወት ትዝብቷን እንዴት ከዘመናችን ማህበረ ፖለቲካ ጉዳዮች ጋር አቆራኝታ እንደምትመለከታቸው እንረዳለን፡፡ የሮዛ አንዳንድ ትዝብቶች አጥንታችን ድረስ ዘልቀው የሚሰሙን ናቸው፡፡ ለማሳያ ያህል የአቸኖን ቅንጭብ ታሪክ እንመልከት፡-
ሰኒና ወገቧን ያቀፋት ወጣት ኮንትራት ታክሲ ውስጥ ሊገቡ ሲሉ የእግር አልባው ለማኝ የአቸኖ ድምፅ ገታቸው። ከኋላቸው ስለነበርኩ ለማኙ ምን እንደሚላቸው እየተከታተልኩ ነበር፡፡ አቸኖ ሁሌም እንደሚያደርገው የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም በርካታ አረቄዎችን እንደተጋተ የድምጹ ቅላጼ ያሳብቃል፡፡
“አባቱ!እስቲ ብር ልቀቂብኝ!”
ወጣቱ ምንም ምጽዋት ሳይሰጠው ሰኒን እንዳቀፈ ወደ ታክሲው አመራ፡፡ አቸኖ ከመቅጽበት እሳት ለበሰ፤ሁልጊዜ ነው እንዲህ የሚሆነው፡፡ ሰው ሳይመጸውተው እንዳላየው ሆኖ ለማለፍ ሲሞክር ክፉ ይናገራል፤አቸኖ ሰኒን ያቀፈውን ወጣት ምን ሊለው እንደሚችል እየጠበቅኩ ነበር፡፡
“ትሰማኛለህ ወንድሜ!አንተ እንደዚህ በሰላም አየር የሴት ወገብ እንድታቅፍ እኮ ነው እኔ ባድመ ላይ በሻእቢያ ፈንጂ ሁለት እግሮቼን ያጣሁት! ተጸይፈኸኝ ነው ዞረህ እንኳን ልታየኝ ያልፈለግከው?”አለው፡፡
አቸኖ ምጽዋት ሲጠይቅ ለመላው ቺቺንያ በሚሰማ አስገምጋሚ ድምጽ እያንባረቀ ስለሆነ ያስፈራል…(ገጽ 111-112)
ሮዛ “የተከበሩ ማዳም ኤልዛቤጥ” በሚለው ታሪክ ውስጥ የማዳም ኤልዛቤጥ ግዙፍ የመስቀል ፍላወር ቪላ የሚሰጠውን ህቡእ የወሲብ አገልግሎትና በዚያም የሚደርሰውን አሰቃቂ አጋጣሚ በዕለት ማስታወሻዋ ታስቃኘናለች፡፡ ማዳም ኤልዛቤጥ የእድሜያቸውን ሲሶ በፈረንሳይ ያሳለፉ እመቤት ናቸው፡፡ ከዚህ ታሪክ በርግጥም በመዲናችን ውስጥ በርካታ የማናውቃቸው ገመናዎች መኖራቸውን እንረዳለን። ”ፍቅርተን ማን ገደላት?ባሏ” በሚለው አሳዛኝ ታሪክ ውስጥ ሮዛ የአፍ ወለምታ ህይወትን የሚያክል ውድ ነገር የሚያስቀስፍበትን ገጠመኝ ትነግረናለች፡፡
“ጥኡም ወዲ አስመራ” በሚለው ማስታወሻዋ ውስጥ አባትና ልጅ በአንድ ምሽት ሳያስቡት ከሷ ጋር ለመተኛት በሚያደርጉት ትግል ድንገት ግንባር ለግንባር መገጣጠማቸውን በመተረክ፣ የዘመናችንን እውነታ ፍንትው አድርጋ ታሳየናለች፡፡ ይህንን ታሪክ አንብቦ አለመደንገጥ ይከብዳል፡፡ “የቤዛ አልፋና ኦሜጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ደግሞ ወንድም ከቡና ቤት ሴት ጋር እየቀበጠ ከበርካታ አመታት በፊት ከቤት ወጥታ የቀረች እህቱን፣ በዚያው ሆቴል ውስጥ በሴተኛ አዳሪነት ስትሰራ እንደሚያገኛት እንመለከታልን፡፡
የሮዛ የስራ ጸባይ በራሱ በየእለቱ ከተለያዩ የህይወት ጽንፍ የሚመጡ በርካታ ሰዎችን እንደሚያገናኛት ከመጽሀፉ እንረዳለን፡፡ በማስታወሻዎቿ ውስጥ ሮዛ ስለራሷ ገመና ብቻ አይደለም የምትተርክልን፡፡ ስለ ቡና ቤት ሴት ጓደኞቿ(የስራ ባልደረቦቿ)፣አብረዋት ስለተማሩ ወንዶችና ሴቶች፣ ስለፓይለትና ፕሮፌሰር ደምበኞቿ፣ በስካር ነብዘው በተንቋረረ ድምጻቸው “ከኛ በላይ ላሳር” ስለሚሉ ትምክህተኛ ምሁራን፣ስለአፍሪካ ዲፕሎማቶችና ሴሰኝነታቸው፣ራሳቸውን ከፓሪሱ “ኤፍል ታወር” በላይ ቆልለው ስለሚያዩ ዳያስፖራዎች…እያሳቀችን ትተርክልናለች። ደግሞ ማሳቅ ትችላለች፡፡ የስነ-ጽሁፍ አንዱ ግብ አንባቢን ማዝናናት መሆኑ ይታወቃል፡፡
”Usman The Pimp” በሚለው ታሪክ ውስጥ ብዙ አለም-አቀፍ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረውን መልከ-መልካሙን አስጎበኚ ኡስማን እናገኛለን። ኡስማን በቅልጥፍናው በርካታ ሀበሻ ቆነጃጅትን ከአረቦች፣ከነጮች፣ከአፍሪካውያንና፣ከእስያውያን ቱሪስቶች ጋ ያገናኛል፤ሁሌም ባተሌና እረፍት አልባ ነው። የውጭ ዜጎቹን ከሀበሻ ቆነጃጅቱ ጋ የሚያገኛኝበት ህቡእ መረብ ስፋትና ጥልቀት በተለይ በአለም-አቀፍ ስብሰባዎች ወቅት አስገራሚ ነው፡፡ እኛ የዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ እያልን የምናንቆለጳጵሳት መዲናችን፣ በእያንዳንዱ አለማቀፍ ስብሰባዎች ምሽት ታላቅ የወሲብ ንግድ እንደሚካሄድ የምንረዳው በዚሁ የኡስማን ዘ ፒምፕ ታሪክ ውስጥ ነው፡፡ የሴት ደላላ ሆኖ የተነገረን የኡስማን ታሪክ “ተወልጄ እድሜዬን ሁሉ በኖርኩባት አዲስ አበባ እንዴት ይሄ ሁሉ ጉድ መኖሩን እስካሁን አላወቅኩም?” ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡ ሮዛ ከጋዳፊ የፕሮቶኮል ሀላፊ እና ከራሳቸው ከሊቢያው መሪ ጋር እንድትገናኝ አስፈላጊውን ሁኔታ ያመቻቸውም ይኸው ሴት አቅራቢ ኡስማን ዘ ፒምፕ ነው፡፡ ሮዛ ኢትዮጵያዊያን ሴት እህቶቻችን አረብ አገር ብቻ ሳይሆን እዚሁ በአገራችን ለወሲብ ገበያ በስፋት እንደሚቀርቡ ትነግረናለች፡፡ ሴቶቻችንን ለአረቦች በረብጣ ሪያል በመሸጥ ሀብት ንብረት ያፈሩ ሰዎችን ለማሳየትም ይህንኑ ዝናው በከተማዋ ቆነጃጅት ዘንድ የናኘውን ኡስማን ዘ ፒምፕን ታሪክ ታቀርብልናለች፡፡
“ራቁት ጭፈራ ቤቱ ተዘጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ሮዛ ደምበል ህንጻ ስር ስለነበረው ’ኢን ኤንድ አውት’ ስለተባለውና ከበርካታ ዓመታት በፊት በፖሊስ አሰሳ ስለተዘጋው ራቁት ቤት ቆይታዋ ታወጋናለች፡፡ ይህ የራቁት ቤት በአሰሳ መልክ ሲዘጋ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በበርካታ የአገራችን ሚዲያዎች በስፋት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ጥቂት ስመጥር ምሁራንና አርቲስቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ይታወሳል። ሮዛ የቤቱ ታዳሚዎች እነማን እንደነበሩ ብቻ ሳይሆን በዚሁ ህንጻ ውስጥ በሚገኝ ሊፍት ውስጥ ብዙ የወሲብ ገድሎች ይፈጸሙ እንደነበረ በምልሰት ትተርካለች፡፡ እንደምሳሌም ‹‹የሊፍት ቴክኒሻኑ ፈሌ›› በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ይሆናል ብለን የማናስበውን ድብቅ የሊፍት ውስጥ የቤርጎ አገልግሎት እናገኛለን፡፡
ከታሪክ ታሪክ የሮዛን ስሜት እየተጋራሁ ነው መጽሀፉን የጨረስኩት፡፡ ማስታወሻዎቹ በቀልድና በጨዋታ የተዋዙ ስለሆኑ አዝናንተውኛል፡፡ በየታሪኮቹ ጣልቃ በማህበረሰባችን ሁኔታ ያዘንኩባቸውና የደነገጥኩባቸው ቅጽበቶችም ነበሩ፡፡ 29ኙም ታሪኮች ስሜት ይነካሉ ማለት ይቻላል፡፡ የማስታወሻዎቹ ስነ-ጽሁፋዊ ውበትም ማለፊያ ነው፡፡የሮዛ ለየት ያሉ የህይወት ትዝብቶች፣ ምልከታዎችና ለማንኛውም ነገር ያላት በሳል አስተሳሰብ ይማርካል። አንዳንዶቹ ማስታወሻዎች የተጻፉበት ቀን ተገልጿል፤ በርካቶቹ መቼ እንደተጻፉ ግን አልተገለጸም፡፡ቀኑ ቢገለጽ በጊዜው ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ እንድናውቅና ሌሎች ተዛማች ክስተቶችን እንድናሰላስል ይጋብዘን ነበር፡፡
ሮዛ ታሪኩን በስራ ቦታዋና በስራ ባልደረቦችዋ ቋንቋ በማቅረብዋ አልወቅሳትም፡፡ ግልጽነቷንና ታማኝነቷን አበረታታለሁ፡፡ መሸፋፈኑና መደባበቁ ነው ክፉኛ የጎዳን፡፡ ቃላት የሚጠበቅባቸውን ነገሮችን የመግለጽ ሚና በአግባቡ እስከተወጡ ድረስ ነውር አይሆኑም ብዬ አምናለሁ። ሮዛ “ሩካቤ ስጋ”፣”ግብረ ስጋ”፣”ተራክቦ ስጋ”፣”የጭን ገረድ”፣”የከንፈር ወዳጅ”፣”እቁባት” ወዘተ የሚሉ በስራ ገበታዋ ላይ ፍጹም የማትጠቀማቸውን ማለዘቢያና ማሽሞንሞኛ ቃላትን በማስታሻዎቿ ውስጥ ብትጠቀም ኖሮ አስመሳይ ትሆንብኝ ነበር። አርታኢዋም ይህን ነጻነቷን ስላልነፈጋት ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡ ስለቡና ቤት ህይወት እየተወራ ቃላትን ማሽሞንሞን የመጽሀፉን ጠቅላላ መንፈስ የሚያውከው ይመስለኛል፡፡
ሮዛ የአዋቂ መጽሀፍ ነው፤እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንዳያነቡት በሽፋኑ ላይ ተገልጿል። እንደ አደገኛ መድሀኒት ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች ከማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ግን ይህ በሽፋኑ ላይ መገለጡ አደጋውን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው፣ የእለት ማስታወሻዎች በባህሪያቸው ቅጽበታዊ ስሜቶች በትኩስ ስሜት፣ በማያመዛዝን ህሊና እና በጥድፊያ ወደ ጽሁፍነት የሚቀየሩ ሰዋዊ ትዝብቶች እንደመሆናቸው፣ ‹‹ሮዛ›› በዚህ ስሜት ውስጥ ሆና የከተበቻቸው ማስታወሻዎች በአፍላ እድሜ ላሉ ወጣቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት አደጋው የትየሌሌ የሚሆንበት አጋጣሚ የሰፋ ነው። በመሆኑም በኔ ግምት የአርታኢው ሚና መሆን የነበረበት እነዚህን ስሜት ያናወጣቸው የግል ማስታወሻዎችን ማለዘብና ማስከን ብሎም ለአንባቢ የማይጎረብጡ፣ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ መነበብ የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን አርታኢው አሳክቶታል ብዬ አላምንም፡፡
ምክንያቱም የመፅሐፉ ስሜት አንባቢ ዘንድ ሲደርስም ቢሆን የልብ ምትን የሚያፈጥን፣ የቡና ቤት ሁካታው የሚሰማ፣ ፈንጠዚያው ያልበረደለት ሆኖ ነው፡፡  መጽሀፉ ውስጥ በርካታ የፊደል፣የቃላትና የሀሳብ አለመጣጣም ስህተቶች አሉ፡፡አርታኢው “ሮዛ በተለያየ አይነት ስሜት ውስጥ ሆና በተለያየ ቅጽበትና ጊዜ የጻፈቻቸው ማስታወሻዎች ስለሆኑ እንደፈለገች በመዘባረቅ መጻፏንና ያም ከነስህተቱ ማለፉን አንባቢዎች ይወዱታል፤ይረዱታል” የሚል አቋም ቢይዝ እንኳን መሰረታዊዎቹን ስህተቶች ማረም ነበረበት፡፡ ለምሳሌ “ሊሊ ቂጦ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ሊሊን አንዳንድ ቦታ ላይ ሚሚ ሆና እናገኛታለን፡፡”የቤዛ አልፋና ኦሜጋ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ታሪኩ የሚከወንበት  ኦሜጋ ሆቴል አንድ ቦታ ላይ ኦሜድላ ሆቴል ተብሎ እናገኘዋለን፡፡” የሚልኪና የሹገር ማሚዎቹ አጭር የህይወት ታሪክ” በሚለው ታሪክ ውስጥ ወይዘሮ ሳሮን በምን አስማት ቲና እንደምትሆን ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባት እነዚህ ስህተቶች አርታኢውን ሰነፍ ያስብሉት ይሆን እንጂ ጸሐፊዋን ክፉኛ የሚያስተቹ ናቸው ለማለት አልደፍርም፡፡
 በተለያየ ውጥንቅጥ ስሜት ውስጥ ሆነን ክስተቱን ለማስቀረት ብቻ እንዳሻን ስለምንጽፍ (ዲያሪ የመጻፍ ልምድ ካለን)በሌላ ጊዜ በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነን ስንመለከታቸው እንዲህ አይነት ተራ፣አስቂኝና አዝናኝ ስህተቶችን እንደምንፈጽም ባልዘነጋውም አርታኢው የሮዛን ስህተቶች ማለፍ አልነበረበትም ባይ ነኝ፡፡ አርታኢው “የእለት ማስታወሻ ከነስህተቱ ነው የሚያምረው፤አለበለዚያ ለዛውንና ወጥነቱን ያጣል” የሚል አቋም ያለው አይመስለኝም፡፡ መጽሀፍ ላይ ሁሉም አይነት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡በቀጣይ እትሞች ላይ እነዚህ ስህተቶች እንደሚታረሙ እምነቴ የፀና ነው፡፡

addisadmas

Thursday, December 5, 2013

ከ“ፎርጅድ” ፖለቲከኞች፣ባለሥልጣናት፣ ፓርቲዎች፣ … ይጠብቀን!

“የመለስን ራዕይ እናስፈጽማለን” እያሉ ተጐልቶ መዋል ምንድነው?
ሰሞኑን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለውን የፎርጅድ “ስፔሻሊስት” ጉድ ሰምታችሁልኛል? የመቶ ምናምን መስሪያ ቤቶችን ማህተም፣ ቲተር፣ ወዘተ… በመቅረፅ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ (ሳይማሩ ድግሪ እኮ ነው!)፣ መንጃ ፈቃድ፣ የጋብቻ ሰርተፊኬት፤ ውክልና፣ ሊብሬና ሌሎች ሰነዶችን “ሲያመርት” መክረሙን የሰማሁት ከኢቴቪ የፖሊስ ፕሮግራም ነው፡፡ (ፎርጅድ በፎርጅድ ሆነናላ!) ይሄኛውን የፎርጅድ “ስፔሻሊስት” ከቀድሞዎቹ ልዩ የሚያደርገው ምን መሰላችሁ? ያልደፈረው የመንግስት መስሪያ ቤትና የግል ተቋማት የለም፡፡ (አይዞህ ያለው ማነው?) የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የግል ክሊኒኮች፣ የመንግስትና የግል ዩኒቨርስቲዎች፣ ወዘተ (የማን ቀረ ታዲያ!) ማህተሞችን … ፎርጅድ እየሰራ የተለያዩ ማስረጃዎችን ያቀርባል ወይም ይቸበችባል፡፡ (ፎርጅድ ፈላጊው “በሽ” ነው ማለት እኮ ነው!)
የሚገርማችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህተምና ቲተር እንኳን አልቀረም እኮ፡፡ የእነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ቲተርና የኦነግን (አደጋ አለው!) ማህተምም ሲያዘጋጅ እንደነበር ተገልጿል - የፎርጅዱ ስፔሻሊስት፡፡ እኔ የምለው ግን … በ“ፎርጅድ” ሙያ የሚያሰለጥን “ስውር ተቋም” አለ እንዴ? (ከሽብርተኝነት አይለይም እኮ!?) እዚህ አገር ታሪካዊቷን ጦቢያ “ፎርጅድ” የማድረግ አሻጥር (Sabotage) ተጠንስሷል ማለት ነው?
የፎርጅዱ ስፔሻሊስት ሲገርመኝ ሰሞኑን ደግሞ በዚያው የፖሊስ ፕሮግራም ላይ የመኪና ስርቆት የፈፀመች የአዲስ አበባ ኮረዳ ተመለከትኩና በግርምት ተሞላሁ፡፡ እንዴ… ማንን እንመን ታዲያ? (በፎርጅድ ኮረዶችም ተከበናል ማለት እኮ ነው!)
እኔ የምላችሁ … ይሄ የሌብነት ጉዳይ “ፕሮፌሽናል ቢዝነስ” መሰለ እኮ! (የሌቦች ማሰልጠኛ ተቋም ተከፈተ እንዴ?) በዚሁ ሰሞን 20 የሚደርሱ ከተለያዩ ሙያዎች የተውጣጡ ግለሰቦች በፎርጅድ ሰነዶች እየተጠቀሙ፣ የአፍሪካን መዲና ሲያጭበረብሩ እንደከረሙ ፖሊስ ተናግሯል፡፡ ይታያችሁ … ከመኪና አከራዮች ውሃ የመሰለች መኪና ይከራዩና ፎርጅድ ውክልና አሰርተው
ጆሮዋን ይሏታል፡፡ የድግስ ወንበሮችና ድስቶች እንዲሁም የግንባታ ማሽኖች እየተከራዩም  ቸብችበዋል፡፡ (8ኛው ሺ ገባ እንዴ?) የእነዚህ “ቁጭ በሉዎች” ሰለባ የሆነች አንዲት እመቤት ለፖሊስ ስትናገር፤ ሌቦቹ “ያሪስ” መኪና ይዘው ወደ ቢሮዋ እንደመጡ ገልፃለች፡፡ (ያሪሷም እኮ ፎርጅድ ናት!)
ለነገሩ የዚህ የፎርጂድ ነገር በሌቦች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በመንግስትም በተቃዋሚዎችም በምሁሩም በባለሙያውም … በሁሉም ዘንድ እየታየ ነው፡፡ ሰሞኑን አንዲት የስራ ባልደረባዬ መታወቂያዋን ለማሳደስ ወደ ቀበሌ ጐራ ብሎ የገጠማትን አጫወተችኝ፡፡ የቀበሌው ሠራተኞች ወደው ይሁን ተገደው (እነሱም አያውቁት!) የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምስልና “የመለስን ራዕይ እናስፈፅማለን” የሚል መፈክር የተፃፈበት ቲ-ሸርት ለብሰው ተደርድረዋል-ቢሮአቸው ውስጥ፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ቲ-ሸርቱ ለስራ ሊነሽጣቸው (Inspire ሊያደርጋቸው) አልቻለም፡፡ እንደውም መልበሳቸውንም ሳይዘነጉት አልቀሩም፡፡ ለነገሩ የራሱ ራዕይ የሌለው ሰው “የታላቁን መሪ” ራዕይ ላስፈፅም ቢል እንዴት ይሆናል? (“የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” አሉ!) እናም ባልደረባዬን በቅጡ ሊያስተናግዷት አልቻሉም፡፡ (መታወቂያ ማደስ እኮ ነው!) እሷ ተገትራ እነሱ ወሬያቸውን እያደሱ ነበር፡፡ የማታ ማታ ዱላ ቀረሽ ሙግት ገጥማ ነው መታወቂያዋን ያደሱላት፡፡ (የፎርጅዱ “ስፔሻሊስት” በቀን ስንት የቀበሌ መታወቂያ ያመርት ይሆን?)
በነገራችሁ ላይ አንድ ፖሊስ ኦሪጂናሉንና ፎርጅዱን የቀበሌ መታወቂያ አነፃፅረው ሲናገሩ “ፎርጅድ የሚመስለው የቀበሌው ነው” ብለዋል፡፡ (የፎርጅዱን ስፔሻሊስት ወደ ህጋዊ መስመር ማምጣት አይቻልም እንዴ?) በእርግጥ መጀመሪያ ቅጣቱን መቀበል አለበት፡፡ እናላችሁ … “የመለስን ራዕይ እናስፈፅማለን” የሚል ቲሸርት ለብሰው ወሬና ሃሜት ሲያነክቱ የሚውሉ የቀበሌና የወረዳ ሰራተኞች ሁሉ “ፎርጅድ ኢህአዴጐች” ናቸው፡፡ (ኢህአዴግም ፎርጂድ አለው እንዴ?) 
ይሄውላችሁ … በቲቪ መስኮት “ኪራይ ሰብሳቢ… ፀረ ሰላም ሃይላት፣ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ” እያሉ የሚያደነቁሩን ስንቶቹ ካድሬዎችና ባለስልጣናት ሙሰኞች ሆነው እንደተያዙ በዓይናችን በብሌኑ ዓይተናል፤ሰምተናልም፡፡ አሁን እነዚህ ምን ይባላሉ? “ፎርጂድ ባለሥልጣናት!”  (“made in” የት ይሆኑ?) አንዳንዴ ሳስበው የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ፎርጅድ ሰነዶች ብቻ ሳይሆን ፎርጅድ ተቃዋሚዎችን የሚሰሩም ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ ጊዜ ፊቱን ያዞረባቸው ቀን ግን ቅሌት ቀለባቸው ይሆናል፡፡ (“የህዝብ ነኝ” እያሉ ህዝብን ማታለል አደጋ አለው!)
በየጊዜው የአገሪቱ የትምህርት ጥራት “ወድቋል” ሲባል እንሰማለን አይደል?! አንድም ቀን ግን ተጠያቂው “እገሌ ነው” ብለን ደፍረን አናውቅም (እኛም ራሳችን ፎርጅድ ሳንሆን አንቀርም!) እርግጥ ነው ኢህአዴግ መራሹን መንግስት የሚወነጅሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይሄ ግን “ክሊሼ” ነው - የተሰለቸ፤ የታከተ ሰበብ! ነገርዬውን ጠልቃችሁ ስትመረምሩ ግን ዋንኞቹ ተጠያቂዎች “ፎርጅድ መምህራን” እንደሆኑ ትገነዘባላችሁ፡፡ እንዴ … ሴት ተማሪዎችን “እራት ልጋብዝሽና ስለ ግሬድሽ እንመካከር”፣ “250 ብር አምጣና ማርክ ልጨምርልህ” የሚሉ መምህራኖች እኮ በርክተዋል፡፡ እናም የትምህርት ጥራት እንጦሮጦስ የወረደው በእነዚህም “ፎርጅድ የቀለም ሰዎች” ምክንያት ነው፡፡ (መንግስትም ግን ከተጠያቂነት አያመልጥም-ጠያቂ ካለ!) የሰው ፈጠራ ወይም የጥበብ ሥራ አሊያም ሃሳብ፣ ወዘተ … መንትፈው የራሳቸው በማስመሰል እነሆ በረከት የሚሉን “ከያኒያን”ም እኮ “ፎርጂድ አርቲስቶች” ናቸው-የጦቢያ የጥበብ ቆሌ የተጣላቻቸው!
እንግዲህ ፎርጅድ ያልገባበት የህይወት ዘርፍ የለም፡፡ ለምሳሌ እዚህቹ መዲናችን ላይ የፍቅር ፎርጅድ የሚሰሩ እኮ በሽበሽ ናቸው - ከወንዱም ከሴቱም፡፡ መጀመርያ ላይ “እመቤቴ፣ ንግስቴ፤ ማሬ ወለላዬ …” እያለ የፍቅረኛውን እግር ለማጠብ የሚዳዳው የጦቢያ ወንድ፤ አግብቶ “ንብረቱ” ካደረጋት በኋላ ግን ውጭ ውጭውን ያያል፤ ኮረዳ ያማርጣል፡፡ ይሄንን እኔ “ፎርጅድ ባል” ብየዋለሁ፡፡ “ፎርጅድ ሚስቶችም” “በሽ” ናቸው!! (ዘመኑ እኮ ነው!)
ቁጥራቸው ባይበዛም መታወቂያቸው ወይም ፓስፖርታቸው ላይ “ፎርጅድ ኢትዮጵያዊ” በሚል መገለፅ ያለባቸው አንዳንድ በ “ሃሰት” የተሰሩ ዜጐችም አሉ - እዚህችው ጦቢያችን ምድር ላይ፡፡ ባለፈው ጊዜ የአገልግሎት ቀኑ (expiration date) ያለፈበት የታሸገ ምግብ ከውጭ አስመጥተው በሱፐርማርኬት ስለሚሸጡ ስግብግቦች አልሰማችሁም? እስቲ አስቡት … የተበላሹ የህፃናት ምግብና ወተት ለወገን እየሸጡ ትርፍ ማጋበስ … ምን ይባላል? እውነቴን ነው … እነዚህ ከሽብርተኞች በምንም አይለዩም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ህሊናቸውን ለገንዘብ የሸጡ ግለሰቦች “ሆዳም” ወይም “ስግብግብ”፤ በሚል ለመግለፅ መሞከር ዝም ብሎ ቃላት ማባከን ነው፡፡ ትክክለኛው መጠሪያቸው “ፎርጅድ ኢትዮጵያውያን” ነው-ተመሳስለው የተሰሩ! (“ሃሰተኛ” ኢትዮጵያውያን እንደማለት!) በዜጐቻቸው ሰቆቃ የከበሩ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችም እንዲሁ ከዚህ የተሻለ ስም ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ እነሱም “ፎርጅድ ኢትዮጵያውያን” ናቸው (እንደ ፎርጅድ ብር ቁጠሯቸው!) ጥፋት እንጂ ልማት የላቸውም፡፡
እንዴ … ሰሞኑን በመከራና በችግር ተጠብሰው ከሳኡዲ እየተመለሱ ያሉት ዜጐች ለዚህ ጦስ የተዳረጉት እኮ በእነሱ ነው፡፡ እህቶቹን ሲኦል እየወረወረ በሚያጋብሰው ገንዘብ እንቅልፉን ለጥጦ የሚያድር ሰው ኢትዮጵያዊ ሊባል አይችልም … “ፎርጅድ ኢትዮጵያዊ” እንጂ!
ደሞ አሉላችሁ … እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያሉ “እንቁ ኢትዮጵያውያን”! የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ የስደተኛ ዜጐች እንግልት እንዴት እንዳንሰፈሰፋቸው አላያችሁም? በየመድረኩ በመቆርቆር ስሜት የሚያንፀባርቋቸው ንግግሮች በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡ “ለካ ኢህአዴግ እንዲህም ያሉ ሰዎች አሉት!” (ደሞ እንዳይሰማኝ!) ከባለስልጣንነታቸው ይልቅ ሰዋዊነታቸው የሚልቅ፤ ከኢህአዴግነታቸው የበለጠ ኢትዮጵያዊነታቸው የሚጐላ ምርጥ የጦቢያ ልጅ! ከዚህ በላይ እንዳላደንቃቸው ግን “አደጋ አለው!” (ኢህአዴግ ፓርቲው እንጂ ግለሰቦች ሲሞሉ አይወድም!) ፓርቲው እኮ የተገነባው በግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡ (ረስቶት ይሆናላ?!)

addisadmas

Monday, December 2, 2013

የሽፍታው፣ከተሜዎቹና፣አራዊት ቃል ኪዳን



የሽፍታው፣ከተሜዎቹና፣አራዊት ቃል ኪዳን
 
የአራዊት ሁካታ በጣም የሰለቸው፣
ብቸኝነት ጎድቶት ኑሮ የመረረው፣
አንድ ልዩ ሽፍታ ከተማ የማያውቅ፣
ጥቅትቅ ባለ ደን የሚኖር በድብቅ፤
ከዕለታት በአንድ ቀን ከሩቅ የሚመጡ የሰዎች ድምፅ ሰምቶ፣
ሲጠባበቀቸው አሳቻ መንገድ ላይ ለዝርፍያ አድብቶ፣
ወደእሱ ሲቀርቡ ሲጠራ ድምጻቸው፣
የጫካውን ሰላም ሲያደንቁ ሰማቸው፡፡

ለመዝረፍ የአደባው ይሕ አደገኛ ሰው፣
ለመማረክ ወጥቶ እሱ ተማረከ በውይይታቸው፡፡
ስለደኑ ውበት ስለጫካው ሠላም፣
ገነት የገቡ ያህል ተደስተው በጣም፣
እያወዳደሩ ከከተማው ኑሮ ሠላም ከጠፋበት፣
ጩኸት ከበዛበት ኹከት ከሞላበት፣
ሲያደንቁ ሰማቸው የጫካውን ሠላም የጫካውን ውበት፡፡
የእኚህ ከተሜዎች እጅግ የተዋቡ፣
በከተማው ኑሮ ምሬታቸው ገርሞት ተመስጦ ቀልቡ፣
ከአደባበት ወጣ ሊቀላቀላቸው፣
ሊካፈል አስቦ በውይይታቸው፡፡
ግን ከተሜዎቹ ሰው ሽሽትን መጥተው፣
እዚህ ሠላም ቦታ ሰው በማየታቸው፣
ፊታቸው ደመነ እጅግ ቅር አላቸው፡፡
ሰላምታውን ሲሰጥ ሽፍታው ቀረበና፣
የድመፁ አወፋፈር የቅላጼው ቃና፣
ጆሯቸው ሲገባ ፊታቸውን ሞላው ፈገግታ እንደገና፡፡
ሁሉም በአንድ ቃል አጸፋ መልሰው ለሰጠው ሰላምታ፣
ሰው በማይኖርበት በዚህ ልዩ ቦታ፣
ምን እንደሚሰራ በአንድነት ጠየቁት፣
ተክለ ቁመናውን በአግራሞት እያዩት፡፡
ፈገግታ ተላብሶ ያ ሪዛም ገጹ፣
ሽፍታውም መለሰ በነጎድጓድ ድመፁ፡፡
በብቸኝነቴ ከሰው ሳላወራ፣
ከዛፍ፣ከወፎቹ ከአራዊቱ ጋራ፣
ብዙ ዓመት ኖሪያለሁ እኔ በዚህ ሥፍራ፡፡
ፍጹም ተማርሬ  በብቸኝነቴ፣
ከተማ ለመግባት ነበረ ምኞቴ፡፡
አሁን ግን ስሰማ የእናንተን ውይይት፣
ልቤ አመነታ ከጫካው ለመውጣት፣
የከተማው ኑሮ የሚብስ ይመስላል፣
እንኳን እኔንና የጫካውን ልዑል፣
ያደጋችሁበት እናንተን አማሯል፡፡
አዎ በትክክል ከዚያ ሰላም ጠፍቷል፣
ጩኸትና ምሬት ሁከት በዝቶበታል፡፡
አንተም አትታለል አተናፍቅ ከተማውን፣
ከደኑ አትውጣ ኑር የምትኖረውን፣
ፍቃድህ ቢሆንስ ለእኛም አለማምደን፣
የዚህን የአንተ አገር ጥቅጥቅ ያለውን ደን፣
ይህን ንፁህ አየር በነፃ  እየማግን፣
በወፎች ዝማሬ በአራዊት ቡረቃ እየተደሰትን፣
በዚህ ሰላም ቦታ ልንኖር መጥተናል፣
የአንትም ብቸኝነት ከእንግዲህ አብቅቷል፡፡
ቃል እንገባባ ፍፁም ላንካካድ፣
ነበሳችን ከደኑ ከአራዊት ትዛመድ፣
ተነስተን እንጓዝ እረጅሙን መንገድ፣
ሀረናን ሰንጥቅን አማዞን እንሂድ፡፡




 

ታሪኩ በትክክል ከግጥሙ ጋር ባይገናኝም አንድ የተነገረኝ አባ ኤበሉ (የእንትና አባት) የሚባል እውን ይኖር የነበረ ሽፍታ ታሪክ ለሀሳቡ መሻዬ ነው፡፡
ኤበሉ ማለት በአማርኛ እንትና እንደሚባለው ነው፡ ሥሙን በትክክል ያልገለጽኩት ይህን ግጥም ከምታነቡት የተወሰናችሁት የዚህ ሥም መጠሪያ ሊኖራችሁ ስለሚችል ደግሞ የእኔ አባት ሽፍታ የነበረው መቼ ነው እንዳትሉ ነው፡፡  ይህ ሽፍታ የሚዘርፈው ከሚስቱ ጋር ሲሆን ሚስቱ ጠበመንጃ እሱ ደግሞ ቦምብ ይዘው ነው የሚዘረፉት፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ቂም የያዘበት የባለአባት ሰርግ ላይ ይገኝና ያ ሁሉ ሰው ባለበት ሁሉንም በቦመብ እያስፈራራ የባለአባቱን ሚስት (ሙሽራይቱን) ይዞ ወደ ሚኖርበት ጫካ (ደን) ሲሄድ የምትከተለው ስንኝ በሰርገኞቹ ተቋጥራለታለች (ኦሮምኛ ለምታውቁት ብቻ በመሆኑ አዝናለሁ)፡፡
አባ ኤበሉ ኤሳ መኒ ኢሳ፣
ቦምቢን ነማ ቦቤሳ፡፡
ሀረናን ለማታውቁ ባሌ ውስጥ ያለ የታወቀ ደን ነው (ጉግልም ብታደርጉ ታገኙታላችሁ)፡፡

የታላቋ ቀን ልጅ -2005 (መነሸው 1994) ዓ.ም (Son of the great day-2012 (mini-draft 2002)
 
 
ewunet.blogspot.com

አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል ክፍል 8



ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን!
አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን ዘንድ በመረጥካትና ስለብዙዎች ልቧ (አእምሮዋ) ሐዘንን (ነብዩ እንደተናገራት ፍላጻዎችን) ሁሉ ያስተግድ ዘንድ ባጸናሀት፣ ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች እናትህ ማሪያም ሥም ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
የባለፈው ማይክሮ ችፕስ 3፡ ውጤታማ አስተዳደር ማሳጣት፡፡ አንቺ ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል ክፍል 7 መሆን ሲገባው ክፍል 6 ተብሎ የቀረበው ስህተት ስለነበር የታላቋ ቀን ልጅ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይሄኛው ክፍል 8 ይሆናል፡፡ አስቀድሜ ለአንባብያን እንደገለጽኩት የታላቋ ቀን ልጅ አንዴ ይጽፋል እንጂ ተመልሶ ለማስተካከል አያነብም በዚህ ላይ የአማርኛ ሶፍት ዌር የኪቦርድ አጠቃቀም ችግር አለበት፡፡ በመሆኑም በጽሑፎቹ ላይ ብዙ ግድፈቶች ይታዩበታል ለዚህም ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም መሠረታዊ ሀሳቡን አንባብያን በሚረዱት ሁኔታ አስቀምጬዋለሁ ብሎ ያምናል፡፡ 
የአገር አስተዳደር ዝቅጠታችን ቢዘረዘር ማለቂያ የሌለው ትንተና ይሆናልና በመጠኑ አሁን ስላለው አስተዳደር አንስቼ ወደሌላ ወደ ማይክሮ ችብስ 4 እገባለሁ፡፡ በክፍል 7 (በስክተት ክፍል 6 በተባለው) እንዳነሳሁት ብዙዎች በፓርቲነትም ይሁን በሌላ ቡድን የሚንቀሳቀሱት አገርን ለማስተዳደር በቂ ዝግጅት አድርገው አይደለም፡፡ ይህ እውነታ የደርግንም አስተዳደረር ይጨምራል፡፡ የንጉሱ አስተዳደር በግርግርና በአብዛኛው በተማሪዎችና ባልበሰሉ ወጣቶች ጫጫታ ሲፈርስ አገሪቷን በበቂ ዝግጅትና መረጋጋት ሊመራት የሚችል አካል በመታጣቱ ከብዙ ግርግር በኋላ ደርግ እጅ ላይ ወደቀች፡፡ ሊያውም ስንት የበሰለ ልምድና ብቃት ያለቸው ጀነራሎች እያሉ በአንድ ሻለቃ (ኋላ ኮሎኔል በሆኑት) መዳፍ ገባች፡፡  ደርግ 17 ዓመታት አባክኖ የአሁኑ አስተዳደር ሲተካም ነገሮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ 17 ዓመት በዱር ተዋግቶ የመጣ ኃይል ቢሆንም እስከመጨረሻው ድረስ ኧረ እንደውም ስልጣኑንም ከያዘ በኋላ አገርን ለመምራት ግልጽ አላማ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ ሕወሐት የተባለው አላማው ትግራይን ከኤርትራ ጋር ለመገንጠል እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በወቅቱ አብሮ የገባው ኦነግ ግልጽ የሆነ የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያ መገንጠል የሚል አቋሙ አሁንም ያለ ነው፡፡ ሌላው የኦሮሞን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለው ኦሕዲድ አሁንም የገዥው አንድ አካል የሆነው በደርግ ውድቀት ጊዜ ገና ሁለት ዓመት እንኳን ያልሆነው አምቦቀቅላ ነበር፡፡ ነገሩ አሁንም ከ20 ምናምን ዓመት በኋላም ያው ነው፡፡ ኢሕዲን (አሁን በአዴን) አገር የመገንጠል አላማ ባይኖረውም ሰው የለውም አሁንም ድረስ ይህ ፓርቲ ሰው አልባ ነው፡፡ ደሕዴግን ተውት ማንስ ከቁጥር ያስገባዋል? ያው ግን ኢሕአዴግን ለመመሥረት ከአራቱ አንዱ ሆኗል፡፡ በእንዲህ ያለ ውዥንብር እነዚህ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመታየት ራሳቸውን ኢሕአዴግ ብለው ሰይመውና ሌሎችንም ትንንሾችን ከየቦታቸው ለስብሰባ ጠርተው በድፍረት አገርን መምራት ጀመሩ፡፡ ልክ ነበሩ ደርግም በድፍረት እንጂ አገርን ለመምራት በሚያስችል ብቃትና ዝግጅቱ አልመራትም፡፡ ልብ በሉ ኢሕአዴግ አገርን አንደ አገር ለመምራትና የሀገር መምራት ኃላፊነት ሊመጣለት እስከሚችል ድረስ ቢያንስ 10 ዓመት ፈጅቶበታል፡፡ በዚህ መካከል ብዙ ውድመቶች ተከስተዋል፡፡ የኢሕዴግ ባለስልጣናትም ስኳሩን መላስ ለምደው ኋላ ሱስ ሆኖባቸው ዛሬ ሀገርን መዝረፍ ሕጋዊ ያደረጉትን ልምምድድና ሥልጠና ያደረጉት በእነዚያ ዓመታቶች ነው፡፡ የ1990ው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጥቶ እስከሚገላግለን ድረስ እናቲቱ ኢትዮጵያ በጡት በምትጠባው ኤርትራ ሞግዚትነት ትተዳደር ነበርም፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ኢትዮጵያውያን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የተቆጠሩበት ኤርትራውያኑ በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ነግሰው የታዩበት ወቅት በመሆኑ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አንድጦርነቱ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አስደንጋጭ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በብዙዎች ዘንድ የጦርነቱ መቀስቀስ ወሬ እንደ ታላቅ የምስራች ነበር፡፡ በእርግጥም ሰዎች ይችን አገር ሊያጠፉ በተነሱበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ በልዩ ጥበቡ ተዓምሩን ያሳየን ጊዜ ነበር፡፡  በወቅቱ ተሰብስበው በአንድ ሆቴል ውስጥ የጦርነቱን መነሳት ድንገት ከሰሙት ጓደኛሞች አንዱ በደስታ እየዘለለ "ዛሬ እግዚአብሔር እየፈረደ ያለው በላይ በሰማይ ርቆ ሳይሆን እዚህ ያለንበት ጣሪያ ኮርኒስ ውስጥ ሆኖ ነው!" በማለት ነበር ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ፍትህ ለኢትዮጵያውያን እንደወረደ የተናገረው፡፡ እውነት ነው! አምላክ ሕዝቡን መዳኘት ነበረበት ምድራዊ ዳኞች ሁሉ አልቀዋልና፡፡ ያኔ የአገር ፍቅር ወኔውም አልነጠፈም ነበርና የኤርትራውያንን ሳያስተውሉ በቆፈሩት ጉድጓድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀበራቸው፡፡ ይህ በአቶ መለስ ይመራ የነበረውን የኢሕአዴግን አስተዳደር ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ነው እንደ አገር መሪነት መንፈራገጥ የተጀመረው፡፡
ኢሕአዴግ ብዙ ጥፋቶችን ቢያጠፋም ካለማወቅ ወይም ከአቅም ማነስ ሊሆን ስለሚችል ይቅር ሊባል ይችላል፡፡ እንደኔ ግን ሁለት ጥፋቶቹ መቼውንም ቢሆን ይቅር ሊባሉ የማይችሉ  ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ማድረጉና የብሔር (የጎሳ) ክፍፍል፡፡ እነዚህ ደግሞ ጥፋቶች ሆን ተብለው የተደረጉ ክፋቶች እንደሆኑ ሳስብ ይበልጥ አዝናለሁ፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የባሕር በርን ዳግም ለመመለስ ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ግን ነገሩ "እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው" እንደተባለው ሆነ፡፡ አንዴ ሳያየው ነደፈው አሉ ሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ያ ባለፈው የነደፈኝ ነገር ይሄውልህ ብሎ በጣቱ ነክቶ ለጓደኛው ሲያሳይ ነደፈው አሉ፡፡ በቃ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲሁ ነው የሆነው በወደብ ጉዳይ፡፡ አቶ መለስ ከኢሳያስ ጋር አላቸው የተባለው የሥጋ ዝምድና የሁን ወይም የሚመሯትን ኢትዮጵያ ጥላቻ ወይም ሌላ አዚም ብቻ አጥብቀው ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ እንድትሆን የታገሉ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው፡፡
የኢሕዴግ አስተዳደር በወቅቱ እንደ አገር መሪነት ራሱን ባወቀበትና ትንሽ ትንሽም ቢሆን ልማትም እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅትም ቢሆን በአስተዳደር በደል የተከፋው የኢትዮጵያ ሕዝብ በ1997ቱ ምርጫ አይደለም ኢሕአዴግን የትኛውንም ሀይል እድሉን ካገኘ ሊጥል እንደሚችል ምልክት ሰጠው (በጉልበትም በሰላማዊ መንግድም)፡፡ ከዚያ በፊት በ1994 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ላይ በተፈጸመው ድብደባ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቤተመንግስት ሳይቀር ሰብሮ ሊገባ እንደሚችል ስለተረዳ ፌደራል የተባለ ያገኘውን ከመደብደብና ከመግደል ሌላ ለምን ብሎ የማይጠይቅ ኃይል አደራጀ፡፡ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ግን ፌደራል ተብዬውም ሊቋመው የሚችል ስላልነበር የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል በተለይም  በሕዝብ ላይ አዘመቶ ራሱን ከጊዜያዊ ውርጅብኝ አስጣለ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከሕዝብ ውጭ የትኛውም ኃይል አቅም እንደሌለው ስለገመተ ይመስላል ሕዝብን በተለያየ ነገር መደለልና መለማመጥ ጀመረ፡፡ ሒደቱም እውነት ለመናገር ጥሩ ነበር፡፡ ራሱንም ከየተኛውም ፓርቲ በላይ ለሕዝብ አሳቢ አድርጎታል፡፡ ሕዝብንም ለማረጋጋት ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አቶ መለስ ታች እየወረዱ ማነጋገር ጀመሩ፡፡ በእርግጥም ጠ/ሚኒሰቴሩ በዚህ ወቅት ታላቅ የሕዝብንም ፍቅር አግኝተዋል፡፡ አሳቸውም የሕዝብነታቸውን እያረጋገጡ መጡ፡፡ ያቺ ድሮ በብሔር መከፋፈሉ ትክክል ነው ብለው ያመኑባት ነገርም ትንሽ ሕሊናቸውን ነክታቸው ነው መሰለኝ "ልዩነታችን ውበታችን አንድነታችን ኃይላችን ምናምን" ማለትን አበዙ በተግባርም ይህንን አንድነት ለመፍጠርም የብሔር ብሔረሰብ ቀን በሚል በዓል ማክበር ተጀመረ፡፡ ጥሩ ነው ቢያንስ አንድነት የምትለው ቃል አዋጭነቷ ተረጋገጠላት!
ጉዱ ግን ለመለማመጥ በተደረገ እንቅስቃሴ ውስጥ አደገኛ የሆኑ ዜጎችን አፈራ፡፡ ለመደልል እያለ ባለስልጣናትንና በተለያየቦታ ያሉ ወሳኝ ግለሰቦችን ያቀማመሳቸው ዳረጎት በኋላ መቆጣጠር ወደማይችለው ግልጽ የሀገር ዝርፊያ ተሸጋግሮ ይሄው አሁን የምናያትን የምጣኔ ሀብትና የግብይት ሥርዓት ያጣች አገር ፈጠረ፡፡ ነገሩ እንዲህ ታች ድረስ አልደረሰም እንጂ የኢሕአዴግ ትልልቅ ባለስልጣናት ዝርፊያውን ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ እያጧጧፉት ነበር፡፡ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ግን በቃ -----! ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከጥቂት የአገሪቱ ባለስልጣናት በቀር በየትኛውም ደረጃ ያሉ መዝረፍን የመጀመሪያ ተቀዳሚ ስራቸው አደረጉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ግን አቶ መለስ በግላቸው የሚታሙ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ችግሩን ከእንጭጩ ማስቀረት ባለመቻለቸው ምክነያት ኋላ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ራስ ምታት እነድሆነባቸው እንገምታለን፡፡ እዚህ ላይ በአንዳንድ ድረ-ገጾች በአቶ መለስ ሥም በውጭ አገር የሚገኝ ገንዘብ መጠን በሚል የሚሰራጨው ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ አቶ መለስ ድሮ ጫካ እያሉ ገንዘብ ለድርጅቱ በሥማቸው እነደሚቀመጥ ይነገራል፡፡ ያም ገንዘብ እስካሁንም በእሳቸውና በሌላ አንድ ሰው ሥም በውጭ አገር ባለ ሒሳብ እንዳለ ይነገራል፡፡ እንደውም ሌላው ሰው በአሜሪካ ይኖሩ ነበርና በአንድ ወቅት ሚስታቸው ይህንን ገንዘብ በባለቤቴ ሒሳብ የሚገኝ የጋራችን ነው በማለት ተካፍለዋል ይባላል፡፡ በአቶ መለስ ግን ከኢትዮጵያ የተዘረፈ ገንዘብ በውጭ አገር ባንክ አለ የሚለው ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን አቶ መለስ በግላቸው እንጂ ለእርሳቸው ቅርብ የተባሉትን ሰዎችንም ነጻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡  
ከላይ እንደተጠቀሰው አቶ መለስ ከ1997 በኋላ በሕዝብ ዘንድ ከፈተኛ የሚባል ተወዳጅነትን አትርፈዋል፡፡ በእርግጥም የአገርና የሕዝብ አሰቢነታቸውም በግልጽ በሚታይ ሆኔታ ጨምሯል፡፡ አቶ መለስ በግላቸው ባላቸው ችሎታ የሚታሙ ባይሆንም ለዘመናት በአብዛኞቹ የአስተዳደር ዘመናቸው በሕዝብ ዘንድ ተዋዳጅ አልነበሩም፡፡ ወደመጨረሻው የአስተዳደር ዘመናቸው በሕዝብ ዘንድ ያለቸው ተወዳጅነት ተደምሮ ምርጥ የአገር መሪ የሚያሰኛቸውን ብቃት ደርሰው ነበር፡፡ ሆኖም ግን አቶ መለስ በግላቸው ምርጥ ይሁኑ እንጂ አገሪቱን በቀጣይነትና በብቃት ሊመራ የሚችል መዋቅር አላዘጋጁም፡፡ ይልቁንም በአስተዳደር ብቃታቸውና በሕዝብ ዘንድ ተዋዳጅ የሆኑ ባለስልጣናትን ከሕዝብ እያገለሉ ራሳቸው ብቻ ጎልተው ታይተው ነበር፡፡ ለዚህ ደግም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት በሕዝብ ዘንድ ጥሩ እይታ የነበራቸው አንደ አቶ አረከበን የመሰሉ ኃላፊዎችን ወደ ጓዳ ማድረጋቸው ነው፡፡ በግላቸው ከአደረጉት ጥረት ሌላ መዋቅራዊ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓትን ባለማስፈናቸውም አሁን ለተፈጠረው ሌላ ውዥምብር አገሪቷን ጥለዋት አልፈዋል፡፡ በድምሩ ግን የአቶ መለስ የመጨረሻ ዓመታቶቻቸው ጥሩ የሚባል ነበር፡፡
አሁን ያለው አስተዳደር እንደገና እንደ አዲስ የሆነ ይመስላል፡፡ በዚህ ላይ ድሮውንም በዝርፊያ የተዘፈቀ ሥርዓት ታክሎ፡፡ አሁን ያሉት ጠ/ሚኒስቴር ከግል ብቃታቸው ባሻገር የነበረውን ውስብስብ የአገሪቱን የአስተዳደር ሥርዓት ለመቆጣጠር  ቀደመው በበላይነት ቁልፍ ቦታዎችን የያዙ ባለስልጣናትን ለመቆጣጠር እንኳን እንደሚቸገሩ ይገባኛል፡፡ ሲጀምር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብሮ የመጣ የመሪነት ኃይል ያለው መንፈስ ይላቸውም፡፡ ብዙዎች የማይረዱት ነገር ሰው ስለተማረ ወይም የተለያየ ኃላፊነት ላይ ስላለ አገር ለመምራት ያበቃዋል ተብሎ እንደሚተሰበው አይደለም፡፡ በራስ የመተማመንና የመሪነት ኃይል ያለው መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ የመሪነት ኃይል መንፈስ ደግሞ የሚመጣው ጥልቅ ከሆነ ራስን በትልልቅ ቦታዎች ላይ የማየት አቅም ሲኖር ነው፡፡ መሪ ለመሆን ሕዝብን አገርን አኔ ብሎ ማሰብ መቻልን ይጠይቃል፡፡ የአቶ መለስ የመጨረሻ አስተዳደር ዘመን አቅም እዚህ ደረጃ በመድረሱ ነበር በትክክልም ለሕዝብም ለአገርም ኩራት እስከመባል የደረሱት፡፡ አቶ መለስ ይህን አቅም ለመገንባት ግን አመታት አባክነዋል ሊያውም ሁሉንም ነገር መዘወር የሚያስችል ሥልጣን ይዘው፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ግን ጠ/ሚኒስቴር ተባሉ እንጂ ምን ያህል ሥልጣን እንዳላቸው አጠያያቂ ነው፡፡  ያልተለመደ ሶስት ምክትል ጠ/ሚኒስቴሮች ተመድበውላቸዋል፡፡ እንዚህ ምክትሎች ግን የተመደቡት በአጋዥነት ሳይሆን የጠ/ሚኒስቴሩን ሥልጣን ለመጋራት ነው፡፡ ሊያውም ቁልፍ የተባሉትን ሳይቀር፡፡ ከዚህ ውጭ ባሉ ክፍተቶች ደግሞ በየፓርቲው ያሉ ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነቱ አይቀሬ ይመስላል፡፡ በእኔ እይታ ኢትዮጵያ አሁን እየተመራች ያለችው በአቶ ኃ/ማርያም ሳይሆን በደቦ ይመስላል፡፡ ነገሮችም ቻይናውያን እየሰሩልን ካሉት ግንባታዎቻችን ውጭ ዝም ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ አቶ ኃ/ማርያም ጠ/ሚኒስቴር የሆኑበት ሂደት የቱንም ያህል ሕገ-መንግስታዊ ነው ቢባልም ስህተት ነው ብዬ እንዳምን ተገድጃለሁ፡፡ ሌላ በኢሕአዴግ ውስጥ ነባር ተሳትፎ የነበረው ሰው ቢሆን በተሸለ ነበር፡፡
ሌላው የኢሕአዴግ መሥራች የተባሉት ፓርቲዎችን ስናይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የተሻለ የሚባል ሰው እንደሌላቸው እናስተውላለን፡፡ በሁሉም ፓርቲዎች ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙት ባለስልጣኖቻቸው እንኳንስ ለጠ/ሚኒስቴርነት ለሌላውም ይሁን እየተባለ እንጂ ከብቃት አንጻር የሉበትም፡፡ በሚኒሰቴርነት ደረጃ ያሉትን በናስተውል ከአቶ መለስም ጊዜ ጀምሮ የወረደ ብቃት ያላቸው ይበዛሉ፡፡ አሁን ደግሞ ብሷል፡፡  ከመስራች ፓርቲዎቹ ደግሞ ትልልቅ ሕዝብ አለን የሚሉት የባሰ የወረደ ብቃት ባላቸው መሪዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ከኦሕዴድ ብንጀምር ማን ጥሩ ሊባል እንደሚችል ይከብዳል፡፡ በአዴንም እንደዚያው ነው፡፡ ደሕዴግን አንኳን ማን ያስታውሰዋል ደግነቱ በዋናው ተወከለ እንጂ፡፡ ዞሮ ዞሮ ያው ሕወሐት አነስተኛ ሕዝብና የፓርላማ ውክልና እየተባለ በወገዝም በጣት  የሚቆጠሩ ቢሆኑም ሰዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ አቶ ቴዎድሮስ አድሀኖም በፊትም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርነታቸው ብቸኛው (ሌሎቹ ሁሉም በራሳቸው አቅደው የሚሰሩ ሳይሆኑ የአቶ መለስን አፍ የሚጠብቁ ነበሩ) የሚኒሰቴር ሥልጣን የነበራቸው ነበሩ አሁንም የሚያሳፍሩ አይደሉም፡፡ ልብ በሉ እኝህ ሰው የሕዝብና የአገር አኔነት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ በሥልጣናቸው ያላቸው ስኬታማነትና ሞገስ ሚስጢርም ይሄው ይመስላል፡፡ ከላይ ያነሳሁትን አገረርን ለመምራት  የአገርና ሕዝብ እኔ ብሎ ማመን  ቁልፍ እንደሆነ አስታውሱ፡፡  አርከበም በዚህ የሚታሙ አይደሉም፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮንም ደህና እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ ከሌሎቹ ግን እንደዚህ በምሳሌነት እነኳን ሊጠቀስ የሚችል ለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ስለሌለም ይመስላል አሁን ምክትል የሆኑት የብአዴንና የኦሕዴድ ተወካዮች የተመረጡት የቱንም ያህል የምክትሉን ቦታ ባይመጥኑም፡፡
ይህ ችግር ምነአልባት የሕዋሐት የኖረ የበላይነት ወደሌሎቹ ፓርቲዎች ደህና ሰው እንዳይመጣ ውስጣዊ ሴራ ተደርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ሆኖ የፓርቲዎቹ የየራሳቸው ራዕይ ማጣት ግን በየፓርቲዎቹ ብቃት ያለው መሪ መታጣት ዋነኛ ምክነያት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መጀመሪያ ሀሳቡ ከአቶ ተፈራ ዋልዋ ሲነሳ በደናገጥ ፈጥሮ  በኋላ በታመነበት የመተካካት መርሆ መተካካቱ ተተገበረ ቢባልም አተገባበሩ ብቃትን ለማምጣት ሳይሆን ሥልጣን ለወዳጅ ግለሰቦች ማውረስ አይነት ነበር፡፡ ይባስ እሱም ቀርቶ ተተኩ የተባሉትም የአቶ መለስንም ሞት እንደ ጥሩ አጋጣሚ አግኝተውት ነው መሰለኝ ተመልሰው አሁንም ዘዋሪ ሆነዋል፡፡

የታላቋ ቀን ልጅ እንኳንስ ብሔረሰብን መሠረት ያደረጉ ጎጠኛ ፓርቲዎች ውክልናን ይቅርና በአጠቃላይ በኮታ የሚባሉ ውክልናዎች አይመቹትም፡፡ ምርጥ ያአገር ልጆችን ወደመሪነት ማምጣትን አንጂ የአኛ ቀበሌ አልተወከለምና አንድ ሰው ከእኛ የሚባል ነገር በአገር ጉዳይ ቀልድ አይገባውም፡፡ የእኛው አገር እውነታ ግን ኮታ እንጂ ብቃት አይደለም፡፡ ክልሎቹ ሁሉ የአገር ሸክም በሆኑ ባለስልጣኖች ተወክለው በብዙዎቹ ክልሎች ያሉ ልማቶች ከፌደራሉ መንግስት ካልተሰሩ በቀር ንቅንቅ የሚሉ አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት በደልና ዝርፊያው የተሰራውን ሁሉ የሚያወድም ነው፡፡ ቢሆን ቢሆን በአንዱ ክልል ምርጥ መሪ ከተገኘ በዚያው ክልል ባያስተዳደር የተሻለ በሌላ ክልል ቢሰራ፡፡ አሁን ያለንበት አይነት አስተዳደር ግን ጥሩ ውዥምብር ስለሆነ ምዕራባውያኑንም ይሁን ሌሎችን እንደልባቸው ለመዘወር እድል ስለሚሰጣቸው እንዲሁ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ ሕዝብ የእኔ የሚለውን ብዙም አይወዱትም፡፡
ማይክሮ ችፕስ 4 መሀይም ምሁራንን ማፍራት ምሁር ምሁራንን መንጠቅ
ቀደም ብዬ ከአነሳሁት የትምህርት ሂደቱን የማምከን ሴራ ጋር ይያያዛል ግን ይሄ በከፍተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርቶችን ስለሚመለከት ልለየው አሰብኩ፡፡ ዛሬ የአገሪቱን ቁልፍ ኃላፊነት የያዙ ብዙ ሰዎች እራሳቸውን የ60ዎቹ እያሉ ከሚኮፍሱት የመከነ አእምሮ ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹም የትምህርት እድል አግኝተው ወደተለያየ አገራት ሄደው የመጡ ቢሆኑም ስለተማሩት ነገር ቢጠየቁ መልስ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ በውጭ አገር ሄደው ከተማሩት በብዙ እጥፍ አገር ውስጥ የተማሩት የተሻሉ ለመሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ በቀድሞው ዘመን የውጭ ትምህርት ይሰጡ የነበሩት በብዛት ወዳጅ አገር እየተባሉ የሚጠሩት የሶሻሊዝም ሥርዓት የሚከተሉ በመሆናቸው ብዙዎች ወደእነዚህ አገራት ሄደው ተምረዋል፡፡ ዛሬ ሥልጣኑን ከያዙትም እነዚህ ይበዛሉ፡፡ በወዳጅ አገራት ተምረው የመጡት ምሁሮቻችን ግን ብቃታቸውን ላየ አንዴ የት ነበር ሄደው የነበሩት ሻኪሶ ወርቅ ቁፋሮ ነው ወይስ ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ያሰኛል፡፡ እንደውም አንድ ከቡልጋሪያ የሁለተኛ ዲጊሪውን ይዞ የመጣ ሰው ያንተ ዲግሪ ከቡልጋሪያ ነው ወይስ ከዚችው ከእኛው ቡልጋ ነው እያሉ ሲፎግሩት ሰምቼ ትክክለኛ አገላለጽ ነው ብያለሁ፡፡ በቃ እንደውም ድሮ አገር ውስጥ የተማሩትም ካል ተሰርዞባቸው የመጡ ነው የሚመስለው፡፡ እርግጥ በዚያን ወቅት የትምህርት እድሉ ይሰጣቸው የነበሩት ከጅምሩም የተወዳዳሪነት ብቃት ያላቸው አልነበሩም፡፡ የሚያሳዝነው ግን በጣም በሰለጠኑና የሳይንስ መሠረት ናቸው በተባሉት አገር የተማሩት ደግሞ ይብሳሉ፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት አብዛኛው የሄድ የነበረው በሳይንስ ቀዳሚ ወደነበረችው ወደራሽያ ነበር፡፡ ግን የራሽያን ዲግሪ ሁላችንም የምናውቀው አይነት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አብዛኛው የትምህርት እድል በምዕራባውያኑ አውሮፓ አገራት በተለይም ጀርመን፣ ኒዘርላንድ፣ ቤልጅየምና የመሳሰሉት የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይ የጀርመን የትምህርት ዕድል ከሁሉም ይበዛል፡፡ በተመሳሳይ ጀርመን በምዕራባውያኑ አውሮፓ በሳይንስ ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ እንደ ራሽያው ሁሉ በጀርመን ተምሮ የመጣ ዜጋ ግን ዲግሪው አጠያያቂ እየሆነ ነው፡፡ እውንም ጀርመን ክፍል ውስጥ ባይገቡ እንኳን ሁለ ነገሯ ለማስተማር የሚችል አገር ናት ብዬ  አምናለሁ፡፡ ብዙዎችም እንደሚያማርሩት ለውጭ ዜጎች የሚሰጠው ትምህርት ብቃትን ለማሳደግ ሳይሆን ጭራሽ ለማፍዘዝ ነው ይባላል፡፡ በእርግጥም ማንም አገራት ወሳኝ የሆነ ጥበባቸውን ለእኛ አስበው ላያስተምሩን ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ግን የእኛው ችግር ዋነኛውን ቦት የሚይዝ ይመስለኛል፡፡ የጥበባቸውን ሚስጢር እንደማይነግሩን ካሰብን ሚስጢሩን መጎርጎር ነበረብን፡፡ ግን እኛ የሄድንባትነ አገር ከረገጥን ጀምሮ እነሱ የሚሰጡትን እነኳን ትምህርት አንከታተልም፡፡ ከዚህ የዘንው የሄድንወ ድህነታችን ያስገበግበንና ወራዳ ወደሆኑ ሥራዎች ሳንቲም ለመልቀም እንሰማራለን፡፡ ቀኑን ቆጥረን ግን ዲጊሪውን ይሰጡናል፡፡ በቃ የሚፈለገው እሱ ነው የነጠፈ ጭንቅላት የከበደ ዲግሪ ይዘን ወደአገራችን፡፡ ያለ ደረጃችን ወርደን ወረዳ ሥራ የሠራንባቸው ዘመኖቻችንም በዛው ልክ ጭንቅላታችንን ስለሚያወርዱት ትልቅን ነገር መመኘት፣ ክብርን፣ ሞገስን እንረሳለን፡፡
ልብ በሉ ሥራ አይሰራ እያልኩ አይደለም፡፡ የቱንም የወረደ ሥራ ብንሰራ ግን ማንነታችንን ረስተን መሆን የለበትም፡፡ ተቸግረን ታች ወርደን እንሰራለን፡፡ ግን አእምሮአችንና ምኞታችንን እላይ ማማው ላይ በክብር አስቀምጠን ሊሆን ይገባል፡፡ እዛድረስ ያወረደንን ችግርም ነገ እንዴት እንደምነበቀለው በማሰብ፡፡ ልብ በሉ የሄ ሀሳብ ኩራትና ጉረኝነት ከሚሏቸው ሀሳቦች ተቃራኒ ነው፡፡ ታች ወርደን መስራታችንን ፈጽሞ መርሳት የለብንም፡፡ ይህ እንዴትና ከየት የት እንደደረስን የምንማርበት ሌሎችንም የምናስተምርበት ነው፡፡ ክፋቱ የሚመጣው ከሁለት ጽንፍ ላይ ከሚገኙ የአስተሳሰብ ዝቅጠቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉረኝነት ሲሆን ታች ወርደን እንዳልሰራን ድንገት ዛሬ ሲያልፍልን ሌሎችን የመናቅ በሽታ፡፡ አደገኛው ምንግዜም የማይታመን ሕሊና እነዳለን የሚያረጋግጥ ዝቅጠት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሌላውም በተመሳሳይ ወርዶ መስራት አለበት ብሎ ማመን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጉረኝነቱ በተቃራኒ ወራዳን ሥራ ለሌሎችም መናፈቅና፣ ትልልቅ ራዕይ የማጣት ችግር ነው፡፡ እኔ ስለተቸገርኩ ታች ወረጄ የሠራሁትን ሌሎች ከእኔ በኋላ ያሉት እነደኔ ወርደው እነዳይሰሩት ሌላ የተሻለ እድል መፍጠር ሲገባኝ ያው እኔ ያለፍኩበትን የችግር ሕይወት ብቻ የሕይወት ስኬት መስመር አድርጎ ማሰብ ትንሽነት ነው፡፡ ችግርን ልንበቀለው እንጂ ልናወርሰው መሆን የለበትም፡፡ እንዲህ ባለ አስተሳሰብ ታዲያ ገንዘብ ብቻ እንጂ ክብር የተባለ ነገር ሳይገባቸው በሀላፊነትም ሲመጡ ያንኑ የወረደ አስተሳሰባቸውን ብቻ ሊያስተገብሩ ይሞክራሉ፡፡
በብዙ አገራት ከሚሰጡ የትምህርት እድሎች በተሻለ አሜሪካ ዕውቀትና ጥበብ የሚገበይባት ናት፡፡ ከሳይንሱም መዳበር በተጨማሪ ሁሉም አይነት ቀለም ሕዝብ የሚኖርባት ስለሆነ ባይተዋርነቱ ስለማይኖር ለተማሪዎች ጥሩ ድጋፍ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ እርግጥ የአሜሪካ የትምህርት ተቋማትም ከሌሎች በተሻለ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓታቸው በሚገባ አይነት ነው፡፡ በዚህ ላይ የእኛውም አገር የትምህርት ሥርዓት በብዙ መልኩ ከአሜሪካ የትምህርት ሥርዓት ጋር ስለሚመሳሰል በጎ አስተዋጽዖ አለው የሚል ግምት አለኝ፡፡ በአሜሪካ አንዱን ከአንዱ መለየቱም ብዙ አይደለም፡፡ በተለይ አሁን አሁን፡፡ በአውሮፓና በሌሎች አገራት ግን እስካሁንም የዘር ልዩነቱ አለ፡፡ በብዙ አገራት ደግሞ ለታዳጊ አገራት እየተባሉ የሚዘጋጁ ሥልጠናዎች በእርግጥም ዜጎችን ለማደንቆር ሆን ተብለው የተወጠኑ ይመስላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሥማቸው ኢንተርናሽናል የሚል ቅጽል ያለባቸው የሥልጠና ፕሮግራሞች በጣም አደገኛና ምንም ይሄ ነው የሚባል ዕውቀት የማይገበይባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም እኛን ከመናቅ የተነሳ ይሁን ከሌላ አንጻር አይታወቅም ዝም ብለው ዲግሪ የሚሰጡ አሉ፡፡ በዚህ የትምህርት ተቋሞቿ አለም ዓቀፍ ዝናን ያተረፉት ኢንግሊዝ ትታወቃለች፡፡ ይህ ደግሞ የዚያች አገር መርዛማ የሆነ ሴራ ነው፡፡ ዲግሪውን በሥራ ላይ አንቀበልም ቢባል እኛ የሰጠንውን የማትቀበሉት እነማን ናችሁ ይሉናል፡፡
እንግዲህ እንደነዚህ ያሉ መክነን ሁሌም ከችግር እንዳንወጣ የሚደረጉ ተዘዋዋሪ ሴራዎች እንዳሉ ለግንዛቤ እንዲረዳ ጠቆምኳቸው እንጂ የማክሮ ችፕሶቹ ነገር ግን ከዚህም በላይ ሊሆን እነደሚችል እገምታለሁ፡፡ ጉዳዩ ቀጥታ አእምሮን በሚያመክን የቴክኖሎጂ ውጤትም ሊሆን ይችላልና፡፡ ጨረር ወይም ሌላ ቴክኖሎጂ ማለቴ ነው፡፡ ሌላው በክፉ መናፍስት እገዛ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ዛሬ የአለም ፍትጊያው እዛላይ እንደሆነ ብዙዎቻችን አልነቀንም፡፡ የሚስጢራዊ ማሕበረሰብ ዋናኛ ሥራው እንዲህ ያሉ ሴራዎችን መተግበር እንደሆነ እናስተውል፡፡ እኛ ለመለወጥ አንጥራለን በዙሪያችን ግን ብዙ ወጥመዶች እነዳሉ ብዙ አናስተውልም፡፡ አንች ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል!
በተከታታይ 8 ክፍሎች የቀረበው አንች ታቦኪያለሽ ውሻ ይደፋብሻል እዚህ ላይ ይብቃን፡፡ በሌላ ርዕስ እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት፡፡ 
ልዑል አባት ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ የምናስተውልበትን አእምሮ ስጠን! አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ሕዳር 19ኛው ቀን 2006 ዓ.ም (Son of the great day 28th of November 2013)
 
ewunet.blogspot.com

Saturday, November 30, 2013

“ዜጐች የተሰደዱት መንግስት የሥራ ዕድል ባለመፍጠሩ ነው”


“ዜጐች የተሰደዱት መንግስት የሥራ ዕድል ባለመፍጠሩ ነው”

መንግስት ከሣውዲ የሚመለሱ ዜጐች ቁጥር አስቀድሞ ከተገመተው በላይ መሆኑን ገልጿል። ቀድሞ የተመላሾቹ ቁጥር

28 ሺህ እንደሚሆን ቢገመትም አሁን ወደ 80ሺህ እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡ በስደተኞቹ ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከማውገዝ አልተቆጠቡም፡፡ ጉዳዩ በሰከነና

የዲፕሎማሲ መርሁ በሚፈቅደው መንገድ መያዙንም ገልፀዋል፡፡ መንግስት ከዚህ በላይ በዲፕሎማሲው ርቆ ሊሄድባቸው

የሚችልበት አማራጮች  እንደሌሉ የሠሞኑ መግለጫዎቹ ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ

ሣይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ መንግስት የዜጐቹን መብት በማስከበርም ሆነ የሃገርን ክብር በማስጠበቅ ረገድ ምንም

አልተራመደም ይላሉ - ተመላሾቹን ከመቀበል የዘለለ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች መውሰድ አለመቻሉን በመግለፅ፡፡ ዶ/ር

መረራ ጉዲና በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡንን አጭር ማብራሪያ እነሆ:-


በሣውዲ አረቢያ በዜጐቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ተከትሎ መንግስት ጉዳዩን የያዘበትን መንገድ እንዴት

ገመገሙት?
ሁለት ሶስት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ስዊድን በመሳሰሉት ሃገሮች ያሉ ኢትዮጵያውያን በሣውዲ

አረቢያ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ እየፈቀዱላቸው፣ እዚህ መከልከሉ በዜጐች ላይ ተጨማሪ ወንጀል መስራት ነው፡፡

ሁለተኛው በተለያየ መንገድ እየሰማን እንዳለው አሁንም ቢሆን በ40ሺህ የሚቆጠሩ ዜጐች እየተንገላቱ ነው፡፡ እሪታና

የይድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ የሚያወራው ሌላ ነው፡፡ መደብኩ እንኳን ያለው 50

ሚሊየን ብር አንድ እነሱ “የመንግስት ሌባ” የሚሉት የሚሠርቀው እኮ ነው። 50 ሚሊየን ብር ለ70ሺህ ሰው ነው

የመደቡት። ነገር ግን በሙስና የተከሰሱት ሰዎቻቸው እኮ የዚያን ሶስት እጥፍ ሰርቀዋል ተብሏል፡፡ በእውነቱ የተመደበው

ገንዘብ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ሌላው ደጋግመው የሚያሰሙት፤ የሣውዲ አረቢያ መንግስትን ድርጊት የሚኮንን ሳይሆን

ወዳጅነት እንዳይበላሽ ትልቅ ስጋት ያላቸው የሚያስመስላቸው ነው፡፡ ከዜጐች ድብደባ፣ ግድያና እንግልት ይልቅ

የሣውዲ መንግስት ፍቅር የያዛቸው ነው የሚመስለው፡፡ ስለዚህ በሚፈለገው መንገድ ለጉዳዩ ምላሽ እየሰጡ አይደለም

የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ ድሮውንም ቢሆን እነዚህ ዜጐች የተሰደዱት የኢትዮጵያ መንግስት የስራ

እድል መፍጠር ባለመቻሉ ነው፡፡ ሃገሪቷን የስደት ሃገር ያደረገው ራሱ መንግስት ነው፡፡
በሃላፊነትም ያስጠይቀዋል፡፡ ስለዚህ መንግስት በቀን ይሄን ያህል ሰው መለስኩ ከሚል፣ በመሠረታዊነት ዜጐች

የማይሰደዱባት ሃገር መፍጠር አለበት፡፡ የስራ እድል ሊኖርና የሰብአዊ መብት ሊከበር ይገባል፡፡
መንግስት በዜጐቹ ላይ ለተፈፀመው ግፍ፣ በአለማቀፍ ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲው ምን ድረስ ነው ሊሟገት የሚችለው?
መንግስት እኮ ደጋግሞ የሚነግረን በህገወጥ መንገድ ከሃገር የወጡ ናቸው እያለ ነው፡፡ እንኳን በዚህ ዘመን ቀርቶ በጥንት

ዘመንም ስደተኞች ክብር አላቸው፡፡ ዝም ብሎ ይገደሉ፣ ይፈለጡ፣ ይቆረጡ አይባልም፡፡ ስለዚህ ሣውዲ አረቢያ ኋላቀር

በሆነ መንገድ ዜጐቻችንን ስታንገላታ በህግ መክሰስም ይቻላል፡፡ ሌላ አማራጭ ከተፈለገም እንደወዳጅ መንግስትና

የንግድ ሸሪክ ብዙ ተጽእኖ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይልቁንስ የኢትዮጵያ መንግስት እያየ ያለው፣ እዚህ ያሉ ተቃዋሚዎች ምን

አሉ የሚለውን ብቻ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ከሰሱን፣ አጣጣሉን የሚለው ላይ ነው ያተኮረው፡፡
ከዚያም ሲያልፍ ሌት ተቀን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ዜጐቹ በህገወጥ መንገድ መሄዳቸውን ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ

መጀመሪያ የዜጐችን ነፍስ ማዳን ነው፤ ሌላው ደግሞ ለስደት የዳረገንን የኢኮኖሚ ችግር በመፍታት፣ ኢትዮጵያን ከስደት

ሀገርነት ዝርዝር ለማውጣት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ግን አሁን ባለው ሁኔታ የዚህ አዝማሚያ እምብዛም እየታየ አይደለም፡፡
መንግስት በሣውዲ አረቢያ ላይ ይከተል የነበረውን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ለመፈተሽና ለመቀየር የእነዚህ ዜጐች እንግልት

ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ?
አሁን እኮ መንግስት ጠንከር ያለ መግለጫ እንኳ አላወጣም፡፡ በመኮነን ደረጃ እንኳ ደፍሮ መግለጫ ማውጣት

አልቻለም፡፡ ሌሎች ሀገሮች እኮ ቢያንስ በዜጐቻቸው ላይ በደል ሲፈፀም በመንግስት ደረጃ የመረረ ጩኸት ያሰማሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከህዝቡ ጋር አብሮ ሊጮህ ቀርቶ፣ የህዝቡንም ድምጽ እያፈነ ነው፡፡ ለዚህ ነው በተለይ

በፖለቲካ ዲፕሎማሲው በኩል እየተወሰደ ያለው እርምጃ በቂ አይደለም የምለው፡፡
መንግስት ዜጐቹን ከሃገሪቱ ከማስወጣት ባለፈ እርምጃ ያልወሰደው የኢኮኖሚ ጥገኝነት ጉዳይ ስላለ ነው፤ የኢትዮጵያ

ዋነኛዋ የውጪ ንግድ ሸሪክ ሣውዲ በመሆኗ ነው የሚሉ አስተያየቶችንስ እንዴት ያዩዋቸዋል?
በእርግጥ የኢኮኖሚ ጥገኝነቱ አለ፡፡ እናውቃለን። ታላላቅ የሣውዲ አረቢያ ከበርቴዎች በዚህች አገር ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡

ነገር ግን ለኢኮኖሚ ሲባል የዜጐችን መብትና ብሔራዊ ጥቅምን አሣልፎ መስጠት በየትኛውም የፖለቲካ አማራጭ ፈጽሞ

አይመከርም፡፡ ከምንም በላይ የዜጐች መብትና የሃገር ክብር ይቀድማል፡፡ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሰው እየተንገላታ

ለኢኮኖሚ ጥገኝነቱ ሲባል ዝምታን መምረጥ እንዲሁም የዜጐችን ጩኸት ወደማፈኑ መሄድ ተገቢ አይደለም፡፡
አንድ መንግስት በሌላ ሀገር የሚኖሩ ዜጐቹን መብት ለማስከበር ከአለማቀፍ ህግና ፖለቲካ ተመክሮ አንፃር ምን ያህል

ርቀት ነው ሊጓዝ የሚችለው?
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ጨርሶ እስከማቋረጥ ይደርሳል፡፡ ከዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጥ ባለፈም ችግሩን ለአለማቀፉ

ህብረተሰብ በጩኸት ማሰማትም ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን አፉን ሞልቶ ‘በዜጐቻችን ላይ እየተሰራ ያለውን

ግፍ እንኮንናለን’ ለማለት እንኳ እየጨነቀው ነው፡፡ እዚህ ያለውን ኤምባሲ እንኳ ሲያነጋግሩ፣ ዋናውን አምባሳደር

አይደለም፡፡ በሰለጠኑትን ሃገሮች ደረጃ ቢሆን በ30ሺህ፣ 60ሺህ የሚቆጠሩ ዜጐች እንዲህ ያለ እንግልት ሲደርስባቸው

ቀላል ጉዳይ አድርገው አይመለከቱትም፡፡ የህንድ፣ የፊሊፒንስ እና የሌሎች ሃገሮች ዜጐች ከኢትዮጵያውያኑ በተለየ

ክብራቸው ተጠብቆ ነው ከሃገር የወጡት፡፡ ይሄ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
የስደተኞቹ ስቃይ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት እንዳይውል መንግስት ጠይቋል፡፡ በእርግጥ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ውሏል?
የኢትዮጵያ ዜጐች በያሉበት ብሶት እያሰሙ ነው። በተለያዩ መንገዶች በየሃገራቱ በኢትዮጵያውያኑ ላይ የሚፈፀሙት

በደሎች ሲሰሙ ይዘገንናሉ፡፡ እኛ እኮ እየጠየቅን ያለነው የእነዚህ ኢትዮጵያውያንን መብት ነው፡፡ ነገር ግን መንግስት

ጉዳዩን በሌላ እየተረጐመው እኮ ነው የተቸገረው፡፡ 

 http://addisadmassnews.com