Monday, September 30, 2013

ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ

"ፋሺስቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት እንዳይመስላችሁ፡፡ ሸፍታ ማለት ያለ አገሩ መጥቶ የሰውን አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ መጥቶ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን፡፡” አቡነ ጴጥሮስ

ሐምሌ 22 ቀን ጀግናው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ በግፍ የተገደሉበት ቀን ነው፡፡ እኒህ ታላቅ አባት ለሰማዕትነት ያበቃቸው ዋናው ምክንያት በወቅቱ ለተጠየቁት ቀላል ለሚመስል ጥያቄ “ቃሌን አልክድም” ብለው በመቆማቸው ነበር፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ አገራችንን ወርሮ ሕዝቡን ባስጨነቀ ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ ከአርበኛው ጋር በመቆም የጣሊያንን ሠራዊት በድፍረት ሲቃወሙና አርበኛውንም ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ከጊዜያት በኋላ በፋሺስቶች ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ጣሊያኖች ራሳቸው በሰየሟቸው ዳኞች ፊት አቡኑን ለፍርድ በማቅረብ ከላይ ሲታይ በጣም ቀላል የሚመስል ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል፡፡ የጥያቄው ዓላማ አቡኑን የጣሊያን ተገዢ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበረውን ሕዝባዊ ዓመጽ ለማብረድ ቢቻልም ደግሞ የብዙሃኑን ድጋፍ ለማግኘት የታሰበበት ነበር፡፡

ስለዚህም የግራዚያኒ ዳኞች አቡነ ጴጥሮስን ለፍርድ ባቀረቧቸው ጊዜ የጠየቋቸው “ሊቀጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ እንዲሁም ሌሎች የጣሊያንን የበላይነት ተቀብለዋል፤ እርስዎም እንዲሁ ተቀብለው ሌሎችም እንዲቀበሉ ቢያደርጉ ይሻላል፤ ብቻዎን ማመጽ ምንም አይሰራልዎትም፤ ይህንን ቢያደርጉ ምን ይመስልዎታል …” የሚል እንድምታ ነበረው፡፡ … አቡኑም “ከመሞት መሰንበት” በማለት የቀረበላቸውን ምክር አዘል አስተያየት መቀበል አላቃታቸውም፡፡ ሆኖም ለእምነታቸውና ለሕዝባቸው የገቡትን ቃል ከሚክዱ ሞትን ንደሚመርጡ በድፍረት ለዳኞቹ መለሱላቸው፤ እንዲህም አሉ፤
“አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ … ስለ አገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ … እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ” የሚል ነበር፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” አ.አ. 1980፤ ገጽ 157)

ረቡዕ ሐምሌ 22 ቀን 1928ዓም (July 29, 1936) አቡነ ጴጥሮስ ከፊት ለፊታቸው የተደገነውን የጣሊያንን መትረየስ ሳይፈሩ ከመገደላቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የሚከተለውን በመናገር የመጨረሻ ቃላቸውን ሰጡ፡፡
“ፋሺስቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት እንዳይመስላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ አገሩ መጥቶ የሰውን አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ መጥቶ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን፡፡” (ዝ.ከ.፤ ገጽ 157)

አቡነ ጴጥሮስ ይህንን ከተናገሩ በኋላ የፋሺስት የጦር መኮንኖችና ጄኔራሎች በተሰበሰቡበት አደባባይ የተሰማው የማያቋርጥ የጥይት እሩምታ ነበር፡፡ በእጃቸው ከያዙት መስቀል በቀር “መሣሪያ” በእጃቸው ያልነበራቸው የሃይማኖት አባት የተናገሩት ቃልና ያደረጉት ቆራጥ ውሳኔ የግራዚያኒን ጦር ወኔ ሰለበው፡፡ ለአቡኑ አንድ ጥይት አልበቃ ብሏቸው የመትረየስ እሩምታ ተኩስ በመልቀቅ በግፍ ረሸኗቸው፡

ፍርሃት ለአንድ ሰው መትረየስ ያስተኩሳል፤ ለአይጥ ታንክ ያሰልፋል፤ “ለቄጠማ ሰይፍ ያስመዝዛል”፤ የመናገርና የመጻፍ መብቴ ይከበር ለሚል የጸረ አሸባሪ ሕግ ያስወጣል፤ ሰላማዊውን ሰው “አሸባሪ” ያስብላል፡፡ ፍርሃት ያስደነግጣል፤ ያስፈራል፤ ያንቀጠቅጣል፤ ያሸብራል፡፡ ፈሪ የደፋሩ ድፍረት ያስደንቀዋል፤ ድፍረቱን ይመኛል፤ ከዚያ ለመውጣት ግን ራሱ ፍርሃት አንቆ ይይዘዋል፤ ፍርሃት ራሱ ፈሪውን ያስፈራዋል፤ “አልገዛም፤ ቃሌን አልለውጥም” የሚለው የደፋሩ ውሳኔና ቆራጥነት እጅግ ስለሚያሸብረው ራሱ ተሸብሮ ሽብር ይነዛል፤ ያስራል፤ ያሰቃያል፤ ይገድላል፡፡ አልበቃ ሲለው ሃውልት ያስፈርሳል፡፡ ግን አይረካም፤ ምክንያቱም ፍርሃት ሳይሆን ነጻነት ነው ርካታን የሚሰጠው፡፡ ስለዚህ እንደፈራ ኖሮ እንደፈራ ይሞታል፤ ቃሉን የሚጠብቀው ግን በነጻነት ኖሮ በነጻነት ይሞታል፤ ሞቶም ግን በቃሉ ምክንያት ይታወሳል፡፡ የጴጥሮስ ቃል መቼም አይሞትም!!
SOURCE:http://www.ethiopianreview.us/48377

ዓመፅ በሱዳን፥ስጋት በኬንያ፤ ትኩረት በአፍሪቃ

በሱዳን የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ዓመፅ ካርቱምን አልፎ መላ ሱዳንን አዳርሷል፤ ቢያንስ 30 ሰዎች ተገድለዋል። በኬንያ መዲና አሸባሪዎች ካደረሱት ጥቃት ወዲህ በነዋሪዎቹ በተለይም «ትንሿ ሞቃዲሾ» በሚባለው የናይሮቢ ሰፈር የሚኖሩ ሶማሌያውያን በስጋት ተውተውጠዋል። ከጥቃቱ ጀርባ በርካታ አወዛጋቢ ነገሮች መነሳት ጀምረዋል። ትኩረት በአፍሪቃ ይቃኛቸዋል።
ዓመፅ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምና በመላ ሀገሪቱ
የሚትጎለጎል ጥቁር ዳመና የሱዳን መዲና ካርቱምን ውጧታል። የቤንዚን ማደያዎች በእሣት ተያይዘው እየተንቀለቀሉ ነው። እዚህም እዚያም በየጎዳናዎቹ የመኪና ጎማዎች ይነዳሉ፤ የፀጥታ ኃይላት እንዳይጠጓቸው ለማድረግ በተቃውሞ ሰልፈኞቹ የተለኮሱ ናቸው። ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር ባሳለፍነው እሁድ የወሰዱትን የቁጠባ ርምጃ በመቃወም ድንገተኛው ዓመፅ ዳግም መላ ሱዳንን አዳርሷል።
«ምጣኔ ሀብታችን ላይ የተጋረጠው ችግር ሶሥት ምክንያቶች አሉት። ወደ ሃገር የምናስገባው ወደ ውጭ ከምንልከው ይልቃል። ለፍጆታ የምናውለው ከምናመርተው በላይ ነው። የገንዘብ ሚንሥትር ከሚያስገባው የሚያወጣው በዝቶበታል። በርካቶች ለነዳጅ ፍጆታ ይሰጥ የነበረው ድጎማ መሰረዙ ድሆችን እንደሚጫን ይገልፃሉ። መርሳት የሌለባቸው ጉዳይ ግን በእርግጥም ጫናውን በድሆች ላይ እንዲጠነክር ያደረገው የምጣኔ ሀብቱ ቀውስ ነው። »
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር ነበሩ በአንድ የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት። ይህ ንግግራቸው ግን ሕዝቡን ከማረጋጋት ይልቅ አስቆጥቶ መዘዝ ነው የጠራባቸው። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን የቤንዚን ዋጋ በእጥፍ ማሻቀቡን፣ የመጓጓዣ ክፍያ መናሩን እንዲሁም ያንን ተከትሎ የዕለታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመርን በመቃወም አደባባይ መዋል ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል።
በርካቶች የሱዳን መንግሥት ኅብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠረ በሚያጋብሰው ገንዘብ ተቀናቃኞቹን ለሚወጋበት የጦር ሰራዊት ማደራጃ ያውላል ሲሉ ይነቅፋሉ። የዲሞክራሲ ተሟጋች አምጋድ ፋሪድ።
«የሱዳን ህዝብ በመላ፤ የዚህን ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ውሳኔዎችና የኅይል እርምጃውን ይቃወማል። መንግሥት የተቃውሞውን ወገን ለመጨቆንና ጦርነት ለማካሄድ ብዙ ገንዘብ ያወጣል። ይህን ትቶ ለምን ለህዝቡ ቤንዚንና መባልእት አያቀርብም?»
በሱዳን የዲሞክራሲ ታጋዮች፤ ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት በዓረቡ ዓለም መቀጣጠል የጀመረው የፀደይ አብዮት ሱዳንም ደርሶ የረዥም ዘመን ገዢው የዖመር ኧል በሽር መንግሥትንም ማጋሉ አይቀርም የሚል ምኞት ሰንቀው ነበር። ሆኖም የኧል በሽር የፀጥታ ኃይላት በተቃውሞ ሠልፈኞች ላይ በወሰዷቸው ጠንካራ ርምጃዎች የተነሳ የዲሞክራሲ አቀንቃኞቹ ምኞት ሳይሳካ ቀርቷል። የሕዝባዊ ምክር ቤት ፓርቲ አባል ባሽር አደም ራሕማ የሚያክሉት ነገር አላቸው።
«መንግሥት ችግር ተጋርጦበታል፤ በጀቱ ክፉኛ ተናግቷል፤ የሚፈልገው ገንዘብ እየቦጠቦጠ የመንግሥት እና የባሽር ፓርቲ ወጪዎችን ብቻ መሸፈን ነው። ከእዚያ ባሻገር መንግሥት በዳርፉር፣ ደቡብ ኮርዶፋን እና በነጭ አባይ ግዛቶች ለሚመራው ጦርነት በርካታ ገንዘብ ያስፈልገዋል።»
በሣምንቱ መጀመሪያ ላይ በሱዳን ተቃውሞው ከተቀሰቀሰበት ቅፅበት አንስቶ በበርካታ የዓረቡ ሃገራት የተለመደ መፈክር በማስተጋባት ላይ ነው። «ሕዝቡ የመንግሥቱን መወገድ ይሻል» ሲሉ ሱዳናውያን በየአደባባዩ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። «ነፃነት፣ ሠላም እና ፍትኅ፤ ሕዝቡ ዓብዮት ይሻል!» የሚሉ መፍክሮች በጎረቤት ሀገር የሱዳን መዲና ካርቱም ውስጥ በተደጋጋሚ እያስተጋባ ነው። በሱዳን ኦምዱርማን ትናንትናም ከአርቡ ፀሎት በኋላ ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች አደባባይ ወጥተው «ነፃነት፣ ነፃነት» ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል። ፖሊስ በወቅቱ ሰልፈኞቹን በአስለቃሽ ጢስ ለመበተን መሞከሩም ተዘግቧል።
ስጋት የዋጣት የኬንያ መዲና፤ ናይሮቢ
ባሳለፍነው ሳምንት በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሰፊ የገበያ አዳራሽ አሸባሪዎች ጥቃት ካደረሱ በኋላ በርካቶች አሁንም ድረስ በስጋት ተውጠዋል። ከሶማሌ በተነሱ አሸባሪዎቹ በደረሰው ጥቃት ቢያንስ 70 ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል። የሶማሌው ኧል ሸባብ በኬንያውያን ላይ ሽብር የመንዛቱን ያህል ከደሙ ንፁህ የሆኑ ሠላማዊ ሶማሌያውያን ናይሮቢ ውስጥ በፍርሀት ተሸብበው ይገኛሉ።
ወደ ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል የሚያቀናው ጎዳና አሁን ለተሽከርካሪዎች ክፍት ሆኗል። ላለፉት ቀናት ይህ መንገድ ተዘግቶ ነበር። አሁን ተዘግቶ የቆየው ዋናው መገንጠያ ብቻ ነው። ጥይት መከላከያ ልዩ ሠደሪያ አድርገው ወደ ገበያ አዳራሹ የሚገቡትን እና የሚወጡትን አንዳንድ ወንዶች እና ሴቶች እንቅስቃሴ ለመቃኘት የጓጉ አላፊ አግዳሚዎች ከርቀት ቆመዋል።
የጀርመን የወንጀል ምርመራ ጽ/ቤት በናይሮቢ የተከሰተውን ፍንዳታ ለሚያጠናው የኬንያው ቡድን ርዳታ ለማድረግ የፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎቹን ልኳል። ከፍንዳታው በኋላ በርካታ ጥያቄዎች ማብቂያ የለሽ ጥያቄዎችን አጭረዋል።
«ከረዥም ጊዜ አንስቶ የታቀደበት ሳይሆን አይቀርም። መንግስት ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ቀደም ያለ መረጃ ሳይደርሰው እንዳልቀረ ጭምችምታዎች እየተሰሙ ነው። ሆኖም ያ ትክክል እንደሆነ ምንም ማረጋገጫ የለኝም።»
ሲል አንድ የጎዳና ሸቃጭ በከተማው የሚሰማውን ጭምጭምታ ተናግሯል። መላው የከተማው ነዋሪዎች አሸባሪዎቹ ጥቃቱን ለመፈፀም ምንያህል ሊዘጋጁበት እንደቻሉ እየተነጋገረበት ነው። ፈንጂዎች ቀደም ብሎ በገበያ አዳራሹ ውስጥ ሳይከማቹ አልቀረም ተብሏል። አንዳንድ ጋዜጦች የደኅንነት ሰዎች ጉቦ ሳይቀበሉ አይቀሩም ሲሉ ጥርጣሬያቸውን አሰምተዋል። በበርካታ የጥቃቱ ሠለባ ቤተሰቦች ዘንድ ሀዘን የመግባቱን ያህል አሁን ቀስ እያለ በኬንያውያን ዘንድ ቁጣ አለያም ጥላቻ እየተቀሰቀሰ ነው። ብዙዎች ምናልባትም ለዳግመኛ ጥቃት ናይሮቢ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የሶማሌያውያን ሰፈር ሴራ እየተጎነጎነባቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገራት የአሻራ ባለሙያዎች ፍንጭ ፍለጋ
የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገራት የአሻራ ባለሙያዎች ፍንጭ ፍለጋ
በመዲናዋ አንደኛው ክፍል የሚገኘው ኢስሊ የተሰኘው ሰፈር ውስጥ በርካታ ሶማሌያውያን ስለሚኖሩ ሰፈሩ «ትንሿ ሞቃዲሾ» እየተባለም ይጠራል። በሶማሌ የሚገኙ እስልምና አክራሪ ቡድኖችን በመፍራት ሸሽተው የመጡ ሶማሌያውያን እርስ በእርስ በተያያዙ ቤቶችና በተቀጣጠሉ ታዛዎች ስር ተጠልለው ይገኛሉ። ይሁንና የኧል ሸባብ ታጣቂዎች በገበያ አዳራሹ ውስጥ ጥቃት ለመፈፀም ተዘጋጅተው እንደነበር አስቀድመው የሚያውቁ እና ቡድኑን የሚደግፉ ሶማሌያውያንም እዚሁ ሰፈር ውስጥ መሽገው እንደሚኖሩ ይነገራል።
ከጥቂት ወራት አስቀድሞ ኬንያ ውስጥ በተደረገው የምርጫ ዘመቻ ይህን «ትንሿ ሞቃዲሾ» የተሰኘውን ሰፈር የማስወገድ ዕቅድ የምርጫ ቅስቀሳ ሆኖ ቀርቦ ነበር። እናም አሁን የሰፈሩ ነዋሪዎች የቁጣ ሰለባ እንዳይሆኑ ሰግተዋል።
«ሁኔታው አስጨናቂ ነው። ጥቃት ፈፃሚዎቹ ሙስሊሞች እንደሆኑ ተናግረዋል። ስለእዚህ ፖሊስ ወደ ኢስሊ መጥቶ በርካቶችን ማሰሩ አይቀርም። ፈርቻለሁ።»
«ጥቃቱ ዘግንኖኛል። ፖሊሶች ኧል ሸባብን ይደግፋሉ ሲሉ እኛን ነው ጥፋተኞች የሚያደርጉን። ግን እነሱ ይሄን ሁሉ ጭካኔ እየፈጠሩ ሙስሊሞች አይባሉም ። ያ ከእስልምና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።»
አንዳንድ ተንታኞች ከናይሮቢው ጥቃት ጀርባ የሚገኙ አክራሪዎች በመዲናዋ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ከእንግዲህ በጥርጣሬ እየተያዩ እንዲኖሩ ለረዥም ጊዜ ሳያቅዱበት አልቀሩም ይላሉ። ወጣት ሶማሊያውያን ሙስሊሞች ከሚደርስባቸው ጫና አኳያ በቀላሉ ወደ ኧል ሸባብ ሊገቡ ይችላሉ ሲሉም ስጋታቸውን ይገልፃሉ። የኬንያው ጥቃት እስልምና አክራሪዎቹ ምን ያህል በዓለም አቀፍ ደረጃ መረባቸው የዘረጉ እንደሆነ ጠቋሚ ነው ተብሏል።
እንደ ኬንያ የደኅንነት ሰዎች ከሆነ ከሽብር ጥቃት ፈፃሚዎቹ መካከል የአሜሪካን ዜግነት ያለው ግለሰብ እና አንዲት እንግሊዛዊት ሴትም እንደሚገኙበት አስታውቀዋል። በኢስሊ የሚኖሩ በርካታ ሶማሌያውያን ለጥቃቱ ሰለቦች የተሰማቸውን ሀዘን ለመግለፅና ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን መቆማቸውን ለማሳየት ባለፉት ቀናት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። እናም ልክ እንደ ተቀሩት ኬንያውያን እና መላው ዓለም ሁሉ እነሱም በጥቃቱ እጅግ መደንገጣቸውንና ማዘናቸውን ለማሳየት ይፈልጋሉ። ከእዚያም ባሻገር ከሶማሌያ የመጡ ሙስሊሞች በአጠቃላይ አሸባሪዎች አለመሆናቸውን ግልፅ በማድረግም እራሳቸውን ለመጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ

dw.de

መስቀል የሚያቃጥል (አይደለም)”


ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ሲኖዶሡ ውሣኔ ይሰጣል - አቡነ እስጢፋኖስ

በአቃቂ ቃሊቲ ገላን ጉራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ከሠማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ እስኪያስተላልፍ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ የአዲስ አበባና የጅማ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አሣሠቡ፡፡ “መስቀል ከሠማይ ወርዷል አልወረደም? ትክክለኛ ነው አይደለም?” የሚለውን ለመመለስ የግድ ቅዱስ ሲኖዶሡ ጉዳዩን መርምሮ ውሣኔ ሊያስተላልፍበት ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ይህን ለማድረግም ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ቋሚ አባላት እንዳሣወቁ ተናግረዋል፡፡ መስቀሉ እንደተባለው ከሠማይ የወረደ አለመሆኑ ከተረጋገጠም የቤተክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች ይጠየቁበታል ብለዋል-ብፁዕነታቸው፡፡
መስቀሉ ከሠማይ ወረደ በተባለ በ4ኛው ቀን ነሐሴ 27 ቀን 2005 ከሠአት በኋላ ወደ ስፍራው በማቅናት ተገቢውን የፀሎት ስርአት ከካህናቱና ከቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ጋር ካደረሡ በኋላ መስቀሉን ከወደቀበት መሬት አንስተው ወደ ቤተመቅደሡ እንዲገባ ማድረጋቸውን የገለፁት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፤ መስቀሉ ከሠማይ ስለመውረዱ በአይናችን አይተናል ካሉት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እንደማንኛውም ሠው መስማታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
መስቀሉን ከወደቀበት መሬት ያነሱት ብፁዕነታቸው፤ “መስቀሉ ያቃጥላል፤ ብርሃናማ ነፀብራቅ አለው” የሚባለውን አለማስተዋላቸውን ጠቁመው፤ “መስቀል የሚያቃጥል ሣይሆን የድህነት ሃይል ነው ያለው፣ የሚያቃጥል ቢሆን ኖሮ ከመሬት ላይ ማንሣት ባልተቻለ ነበር” ብለዋል፡፡ ወረደ የተባለውን መስቀል ለመመልከት ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ምዕመናን ለምን እንዳይመለከቱት ተከለከለ የሚል ጥያቄ ያነሣንላቸው ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶሡ ተጣርቶ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ ህዝበ ክርስቲያኑ ጉዳዩን በጥሞና እንዲያጤነው በማሠብ ነው” ብለዋል፡፡ (ምንጭ: አዲስ አድማስ)

Saturday, September 28, 2013

“ግንቦት ሰባት” የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከኤርትራ እንደሚያገኝ ገለፀ



በኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የ“ግንቦት ሰባት” አመራሮች ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ እና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ከስልጣን ለማውረድ ለሚያደርጉት ሁለገብ ትግል ከኤርትራ መንግስት የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ሰሞኑን ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡ ባለፈው ሰኞ ከሶስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ቨርጂንያ ግዛት የድርጅታቸውን አቋም የገለፁት የድርጅቱ አመራር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ጋር በአካል ተገናኝተው እንደተነጋገሩና ከኤርትራ መንግስት ጥሩ ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቁመው የመሳሪያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ ወደ ትጥቅ ትግል እንገባለን ያሉት አቶ አንዳርጎቸው ፅጌ፤ በስብሰባው ተሳታፊ ከነበሩ ሰዎች፤ ለምን ኤርትራን እንደመረጡና ሌላ አማራጭ ሀገር እንዳልፈለጉ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “በአሁኑ ሰአት ባለው ሁኔታ ከኤርትራ የተሻለ ድጋፍ የሚሰጠን የለም” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡ “ግንቦት ሰባት” ከአልቃይዳ፣ አልሸባብ፣ ኦነግና ኦብነግ ጋር አሸባሪ ተብሎ በፓርላማ መፈረጁ የሚታወስ ሲሆን የድርጅቱ መሪዎች በሌሉበት የሞትና የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡

 http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com

እኔና አንቺ …፩


ፖለቲካና ስደት
(ወለላዬ ከስዊድን)
መቼም እኔና አንቺን ሲፈጥረን
ጉዳችሁ አይለቅ ያለን ነን
ይሄው ደግሞ ተሰደንም
ልንስማማ አልደፈርንም።
ሳትሰሚኝ አጣጥመሽ
እኔም ያንቺን ሳላውቅልሽ
መግባባቱ እንዳቃተን
በየአቅጣጫው ተበታትነን
ስንፋተግ ዕድሜ ገፋን።
እውነታውን ስንሸሸው፣ መወያየት ስንፈራ
ቀለብ ሆነን ሀሜት ጉራ።
በይ ተይው ግዴለም፣ ድሮውንም ሲፈጥረን
ጉዳችሁ አይለቅ ያለን ነን።
ለነገሩ ትተነውስ ወዴት ልንደርስ
ግደለሽም እኛው ደፍረን እንዋቀስ
የዕለት የዕለቱን ትተነው
ዘላቂውን እንመርምረው።
የጋራ ችግራችንን ተነጋግረን
በጋራ እንፈታለን እያልን
በአፍ ብቻ ስንወተውት
ከልብ አጣን ስምምነት።
ስለሀገሬ ስለሀገርሽ
አንቺም ስሚኝ፣ እኔም ልስማሽ!
የማተያት፤ የማልተዋት
የጋራችን አንድ ሀገር ናት።
ታዲያ ይሄንን እያውቅን
በድርጅት ተከፋፍለን
እላይ ላዩን ታጋይ መስለን
ውስጥ ለውስጥ ተሸዋውደን
“በእከክልኝ ልከክልህ” ተዘማምደን
እንኳን ካለው ከጎናችን
ጸበኛ ሆ’ን ከህሊናችን።
የጠላታችንን ጠላት፣ ወዳጅ ማድረግ
እንቢ ብለን በማፈግፈግ
እሱ ራሱ ተስፋ እንዲቆርጥ
እንጥራለን ለመበጥበጥ
ይሄን አውቀን በአዲስ መንፈስ
ካልፈታነው ያለንን ቀውስ
ከቶ አንችልም የትም ልንደርስ።
ከአፍ ብልጠት ሳትቆጥሪብኝ
ማነህ? ብለሽ ሳታይብኝ
እንደ አባቶች በእርጋታ፣ እንደ እናቶች በጽሞና
ተወቃቅሰን እንቃና
ህዝብ ማለት እኮ-እኔና አንቺ ነን
ሀገርም ማለትም እኛ ነን።
ሀገር ሀገር ብንላት
በምላሳችን ጫፍ ለጥፈናት
አናድናትም ከጥፋት
እስቲ እንተወው አልልሽም ይሄንንስ
ትተነውስ ወዴት ልንደርስ?
ሌላ ሀገር እኮ ቢኖሩት
ያስጨንቃል የራስ እጦት
አዎን! ችሎ ማደር ይባላል
ችሎ ማደር ይቻላል
ሀገር ካልኖረ ችሎ፣ ታድሮስ የት ይገባል?
ይሄው! በትግሉ ጎራ ብንኮለኮልም
እኔና አንቺ ጠርተን አንጠራም
እርስ በእርስ ተቆራቁዘን
ተኮራርፈን ተሰዳድበን
ስም መግደያ ሰይፍ መዘን
ስንቱን ጥለን ጨፈጨፍነው
ስንቱን ሰቅለን አወረድነው
እኔና አንቺ ከመጣብን
ምን ያስዋሻል እንደዚህ ነን።
በይ! እንፍታው በንግግር
እንድንድን ከዚህ ችግር
እስከመቼ ተፈራርተን
ተባባሉ መባል ጠልተን
እውነታውን አንሸፍን
ድንገት እንኳን ቢሆነን ፈውስ
ተገጣጥመን እንዋቀስ።
አንዴ ወጥተን ሥልጣን ላይ
የልጅ ልጆች እዛው ሳናይ
እኔና አንቺን የሚነካን
ወያኔ ነው ውረድ ካለን።
የኔና ያንቺ ሥልጣን አቅም
ከልጆች መብት ብዙ አያንስም
ብናጠፋስ ማን ተናግሮን
እንዳላየ ነው የሚያልፈን
ይሄን ይሄን ካላረምን
ገዚው ፓርቲ የሚበልጠን
ልብ ብለን ካስተዋልነው
በሚንስትር ብቻ እኮ ነው።
እንተወው አልልሽም ይሄንንስ
እኔና አንቺው እንዋቀስ
መወቃቀስ ለህሊናው ላደረ ሰው
እንደ እንቆቆ መዳኒት ነው
ይሄን አውቀን አምነንበት
መራሯን ቃል እንጨልጣት
ካለን ሕመም ለመፈወስ
ደግመን ደግመን እንዋቀስ
ግድ የለሽም ገጽታሽን አታጥቁሪ
አንገትሽን አታዙሪ
ለሰው ያሉትን – ለኔ ብሎ መስማት
ይጠቅማል እንጂ የለውም ጉዳት።
በይ! እንግዲህ እንዋቀስ፣ ብለን ካልን
ስህተታችን ካስተማረን፤
ትንሽ ሲገኝ የምንኮራ
ወሬ ሰምተን የምንፈራ
በገዢና ተገዢ አይነት
በኔ አውቃለሁ ግትርነት
በተበለጥኩ ምቀኝነት
ተተብትበን ምንራኮት
የጠራ አቋም ያልጨበጥን
የማንፈትሽ ውስጣችንን
እኛን ጥለን ሌላ ምንጥል
በግማሽ ልብ ምንታገል
መወያየት አስፈርቶን
አሉባልታ የተጫነን
ምን ያስዋሻል፣ እኔና አንቺ እንደዚህ ነን።
ወለላዬ ከስዊድን
welelaye2@yahoo.com

zehabesha

በእስር ላይ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተፈቱ


በእስር ላይ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች
ዛሬ መስከረም 17 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲሁም በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ሰይፉን ጨምሮ በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የታሰሩት 26 የአንድነት አባላት ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ተፈተዋል፡፡ በፖሊስ ተይዘው ወደጣቢያ የተወሰዱት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ለመሆን በእጩነት የቀረቡትና የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ተክሌ በቀለ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስዩም መንገሻ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራና ሌሎች አመራሮችም ነበሩበት፡፡
አመራሮቹ የፊታችን እሁድ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊትለፊት ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አንድነት ፓርቲ ከ33 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለጠሩት የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በተለይ በአራዳ ክፍለ ከተማ በቅስቀሳ ላይ እያሉ መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ለእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ቢሰጥም የከተማው ፖሊስ ለቅስቀሳ የሚሰማሩ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችን በተደጋጋሚ ያለምንም በቂ ምክንያትና ክስ እያሰረ መፍታቱ አዲስ አይደለም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አመራሮቹንና አባላቱን ለምን እና በምን የህግ አግባብ ለሰዓታት እንዳሰረ ብንጠይቅም ታዘንነው ከማለት ውጭ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
 
 revolutiondemocracry

ኢትዮጵያን ያየሁበት ዓይን


ያን ፊሊፕ ቫይል ተወልዶ ያደገው በክሬፌልድ ከተማ ጀርመን ሀገር ሲሆን ጀርመናዊው ወጣት ገና የ14 ዓመት ልጅ ሳለ ነው ከጓደኛው ጋ በመሆን ለኢትዮጵያ ገንዘብ ማሰባሰብ የጀመረው። ይሄው ወጣት በአሁኑ ሰዓት «ኤምራ እና ዳቦ» የሚል ፊልም ኢትዮጵያ ውስጥ በመቅረፅ ላይ ይገኛል።
« 8ኛ ክፍል ነበርን ያኔ። በዕረፍት ሰዓት ያለማቋረጥ ቋሊማ እና ከስንዴ እና እንቁላል የተሰራ ጣፋጭ ቂጣ( ዋፍል) እንሸጥ ነበር። ከዛም በተጨማሪ ክሪፌልድ በሚገኙ የምሽት ክበቦች የተለያዩ የአፍሪቃ ድግሶች እናዘጋጅ እና ገንዘብ እናሰባስብ ጀመር። ከዛም 11ኛ ክፍል ስንደርስ ባንድ ጊዜ ያሰባሰብነው ገንዘብ 20 000 ዩሮ ደረሰልን።» ይህንንም ገንዘብ ያሰባሰቡት ካርል ሀይንስ በኧም ለመሰረቱት «ሰዎች ለሰዎች» ለተሰኘው ድርጅት ነው። ያን እና ጓደኛው ለ ድርጅት ብዙ ገንዘብ ስላሰባሰቡም ካርል ሀይንስ ቡም ሁለቱንም ኢትዮጵያ ሄደው እየተሰራ ያለውን እንዲጎበኙ ጋበዙዋቸው። በዕውን ለማያውቋት ሀገር ገንዘብ ያሰባሰቡት ወጣቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ጀመሩ ። ከዛ ሲመለሱም የበለጠ ለመርዳት ተነሳሱ። ለት/ቤት ግንባታ የታቀደው 20000 ዮሮ በቂ ስላልነበረም አስፈላጊ የነበረውን 50 000 ዮሮ ለማሰባሰብ እንደተበረታቱ ያን ይናገራል።
« አዎ! ተመልሰን እንደመጣን ክሪፌልድ በሚገኙ ት/ቤቶች እና በቤተ ክርስትያን የአባላት ማህበር ስለ ሰዎች ለሰዎች ስራ እና በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ እንገልፅ ጀመር። ኋላም የርዳታ ማህበር አቋቋምን። 150000 አባላት አሉን በየወሩ አንድ ዮሮ ርዳታ መስጠት የሚችሉ። በአሁኑ ሰዓት የተሰበሰበው 75 ሺ ዮሮ ደርሷል። እና የተጀመረውም ት/ቤት ተሰርቶ አለቀ። የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ በበጎ ፍቃደኝነት የጀመርኩትን ስራን በ2009 ዓም አልቆ ማየት መቻሌ እጅግ የሚያስደስት ነበር። »
Bildbeschreibung: Filmprojekt, Krefelder Jan P. Weyl dreht Kino-Spielfilm in Äthiopien namens Emra & Dabo 
Datum: 26.09.2013
zugeliefert: Lidet Abebe
Bildrechte : R&B RÄUBER & BANDITEN FILM ፎቶ አንሽ ለመሆን የሚመኘው አዳጊ ወጣት(የፊልም ተዋናይ)
ከኢትዮጵያ ጋ ጥብቅ ትስስር እንዲኖረው ትልቅ ሚና የተጫወቱት የወቅቱ የማህበራዊ ኢኮኖሚ አስተማሪው እንደሆኑ ይናገራል። ዛሬ የ26 አመቱ ያን ባለትዳር ነው። ባለቤቱ ኢትዮጵያዊት ናት። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሙኒክ በሚገኝ ዮንቨርስቲ የፊልም ስራ ያጠናል። በተጨማሪም « ኤምራ እና ዳቦ» የተሰኘ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀርፀው ፊልም፣ ደራሲ የፊልም መሪና ዋና አዘጋጅ ነው።
« ኤምራ እና ዳቦ»
« ኤምራ እና ዳቦ የሁለት ጓደኛሞች ታሪክ ነው። በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል አንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጓደኛሞች ኤምራ እና ዳቦ በልጅነታቸው ይለያያሉ። ኃላም ሁለቱም በተለያየ መንገድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሚኖሩባት አዲስ አበባ ይጓዛሉ። እዛም ህልማቸውን እውን ማድረግ ይፈልጋሉ። አንደኛው ጎበዝ ማራቶን ሯጭ ለመሆን ሲጥር ሌላኛው ደግሞ ፎቶ አንሽ መሆን ይፈልጋል።» ይሁንና ፎቶ አንሽ ለመሆን ያለመው ወጣት መጨረሻው የአዲስ አበባ ጎዳና ይሆናል። ሁለቱ ጓደኞችም ዳግም አዲስ አበባ ላይ ይገናኛሉ። ታሪኩ አንድ ሰው ምኞቱን ዕውን ለማድረግ ምን አይነት ጥረት እንደሚያደርግ እና ለጓደኝነት ምን ያህል መስዋት መክፈል እንደሚቻል ያንፀባርቃል ይላል፣ የፊልሙ ደራሲ። ታሪኩ ልብ ወለድ ብቻ ሳይሆን በከፊል በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ነው።
Bildbeschreibung: Filmprojekt, Krefelder Jan P. Weyl dreht Kino-Spielfilm in Äthiopien namens Emra & Dabo 
Datum: 26.09.2013
zugeliefert: Lidet Abebe
Bildrechte : R&B RÄUBER & BANDITEN FILM « ኤምራ እና ዳቦ» ፊልሙ በሚቀጥለው ዓመት በሲኒማ ይታያል ተብሎ ይጠበቃል
« በታሪኩ መካከል በርግጥ የተከሰቱ ነገሮች ይንፀባረቃሉ። ለምሳሌ ሁለቱ አዳጊ ወጣቶች መንደራቸውን ትተው የሚሄዱበት ሁኔታ፣ መንደራቸው ያገኙት ነጭ የውጭ ዜጋ በዲጂታል ካሜራ ፎቶ ማንሳቱ እና ኤምራ የራሱን ፎቶ ሳይ እሱም ካሜራ እንዲኖረው ተመኝቶ መንደሩን ትቶ ወደ ከተማ መሰደዱ…» ሌላም ሌላም በእውነታ ላይ ያተኮሩ ነገሮች በፊልሙ ላይ ይስተዋላሉ። ያን እና ባልደረቦቹ የጀመሩት ፊልም ግን ተሰርቶ አላለቀም። ከ90 ደቂቃው ፊልም 50 ደቂቃው ገና አልተቀረፀም።
« እስካሁን ሁሉንም ወጪ ራሳችን ነን የቻልነው። 18 የጀርመን ባልደረቦቼ የበረራ የመኖሪያ እና ምግባቸውን ራሳቸው ችለው ነው እየሰሩ ያሉት። ከ25 የሚበልጡ የፊልም ባልደረቦች እዛው ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፤ እነሱም በጠቅላላ ለነበረን የ 3 ወር የቀረፃ ጊዜ ያለ ምንም ክፍያ ነው ሲሰሩ የቆዩት። ፊልሙን ጀርመን ውስጥ ሲኒማ ቤት እንደሚታዩ ፊልሞች ከከተማው ድጎማ አግኝተን ለመስራት አንችልም። »ስለሆነም ያን እና ባልደረቦቹ በአሁኑ ሰዓት ፊልሙን ለመጨረስ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት እንደ አማራጭ ያዩት የህዝብ መዋጮ (ክራውድ ፈንዲንግ) ነው።
«ክራውድ ፈንዲንግ ማለት፤ አንድ ሰው ያለውን የፕሮጀክት ሀሳብ ኢንተርኔት ላይ ያወጣል። ከዛ ያንን ፕሮጀክት የሚደግፉ ወይም የዛ አካል መሆን የሚፈልጉ ሰዎች የተወሰነ የድጋፍ ገንዘብ በመስጠት ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ኤምራ እና ዳቦን የክራውድ ፈንዲንግ ገፅ indiegogo.com ላይ ከ40 ቀን በፊት አውጥተንዋል። ፊልሙን ለመቅረፅ በአጠቃላይ የሚያስፈልገንን 200,000 ዶላር ለማሰባሰብ አሁን 2 ሳምንት ተኩል ይቀረናል። »
Bildbeschreibung: Filmprojekt, Krefelder Jan P. Weyl dreht Kino-Spielfilm in Äthiopien namens Emra & Dabo 
Datum: 26.09.2013
zugeliefert: Lidet Abebe
Bildrechte : R&B RÄUBER & BANDITEN FILM የፊልም ቀረፃው ባልደረቦች
ገንዘቡን ለማግኘታቸው ምንም ዋስትና የለም። ይሁንና ርዳታ ሰጪው ገንዘብ ብቻ መስጠት እንዳይሆንበት ትናንሽ ስጦታዎች ከድጋፍ ጠያቂዎቹ ያገኛል። ፊልሙን የሚፃወቱት ተዋናዮች ሳይሆኑ ራሳቸውን ሆነው የሚቀርቡ ሰዎች ናቸው ይላል ያን ። የፊልሙን ታሪክ ለመፃፍ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት እንዲህ ይገልፀዋል። «በ2007 እና በ2008 በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ9 ወራት ቆይቻለሁ። ለ7 ሳምንታት የታቀደው ጉዞዬ በመጨረሻ 9 ወራት ፈጅቷል። በዚህ ጊዜም ለፊልሜ አስፈላጊ የነበረውን ሁሉ ማሰባሰብ ችያለሁ። ያ ማለት ለ 4 ሳምንታት አዲስ አበባ ከሚኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ጋ አብሬ በቅርበት ቆይቻለሁ፣ ከምዕራቡ ዓለም ስልጣኔ ርቄ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ከገበሬ አባወራዎች ጋ ቱኩል ውስጥ ቆይቻለሁ። በእንጦጦ ተራራ ላይ ከታዋቂ የማራቶን ሯጮች ጋ አብሬ ሰልጥኛለሁ። እና በዚህ መንገድ ነው ልገልፀው የፈለኩትን ታሪክ ያሰባሰብኩ።»
ፊልሙ በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋ ሲሆን በሌሎች ሀገሮች እንዲታይም በጀርመንኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችም ተተርጉሞ ይቀርባል። የያን እና ባልደረቦቹ ምኞች ዕውን ከሆነም በሚቀጥለው ዓመት በሲኒማ ይታያል።
ልደት አበበ
ተክሌ የኋላ

DW.DE

የደብሪቱ ወተት


(ወለላዬ)
cow milk
ሰፈራችንን መሀል ለመሀል ሰንጥቆ ከሚያልፈው መንገድ በስተቀኝ ሃያ አንድ መኖሪያ ቤቶች ይገኛሉ። ከነዚህ ቤቶች ነዋሪዎች ውስጥ ከአብዛኛዎቹ ጋር የስጋ ዝምድና አለን። በተለይ በአንድ ግቢ ውስጥ የምንኖረው ስምንት ቤተሰቦች ደግሞ የቅርብ – በጣም የቅርብ ዘመዳሞች ነን።
በነዚህ ቤቶች ውስጥ አያቶች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ አክስቶች፣ አጎቶች፣ አማትና አማቾች ሲኖሩ ከሁሉም የተውጣጣን የልጅ ልጆችም እንገኛለን። ከአጎቶቻችንና ከአክስቶታችን መካከል ሁለቱ ከኛ ዕድሜ ብዙ ስለማይርቁ ቀረቤታችን የጎላ ነው።
አሰግድ ገ/እግዚአብሔርና …
አሰግድ ቀልደኛ ነው። በማንኛውም ጊዜ በትንሹም በትልቁም ነገር እራሱን አዝናንቶ ሌላንም ለማስደሰት ይጥራል። የወጣለት ፀሐፊም ነው። እንደዛሬው የትያትር ጥበብ ሳይስፋፋ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ከሚሉ ጥቂት ተዋናዮች መካከልም አንዱ ነበር። አሰግድ አጎቴ ብቻ ሳይሆን ከጉርምስናዬ ማግስት ጀምሮ ምርጥ ጓደኛዬም ሆኖ ቆይቷል። ስለ አሰግድ ይቺን ካልኩ ይበቃኛል ወደቤታችን ድራማ ላምራ።
በቤታችን ውስጥ ቀንና ሰዓታቸው ያልተወሰነ፤ አጫጭር ድራማዎች በየጊዜው ይቀርባሉ። እነዚህ ድራማዎች አይጠኑም፤ ተዋናይ ተመርጦ አይመደብባቸውም፤ ፀሐፊና አዘጋጅ የላቸውም። አንዱ ባሻው መንገድ ይጀምረዋል፤ ሌላው አውቆም ሆነ ሳያውቅም ያግዘዋል፤ በቅብብሎሽ ወይም በግል ድራማው ተሠርቶ ይፈጸማል። ድራማው አስቂኝ ቢሆንም የማያቄሙ ተበዳዮችም ይኖሩታል። ብዙ ግዜ ድራማው በልጅ ልጆች የሚቀርብ ሲሆን፤ አሰግድ ድምቀት ሰጭ ሆኖ ያገለግላል።
አንድ ቀን እንዲህ ተሠራ። አንዷ አክስታችን ከመንደሩ ጠዋት ጠዋት የሚመጣላት ወተት በኪራይ ይዛለች። አከራይዋ ወ/ሮ ደብሪቱ ይባላሉ። ደብሪቱ ዝቅአድርጌ። ኃይለኛነታቸው በሰፊው ስለሚወራ ሰው ሁሉ በጥንቃቄ ነው የሚይዛቸው። የወተት ሂሳብ በወቅቱ ያልከፈለ የጭቃ ጅራፋቸውን ስለሚያወርዱበት ከቀኗ ውልፍች አይልም።
አክስቴ ዘንግታው ይሁን በሌላ አጋጣሚ የዛን ወር የወተት ሂሳብ ሳትከፍል ሦስት ቀን አልፏታል። በአራተኛው ቀን ጠዋት ወፍ ሳይንጫጫ የወ/ሮ ደብሪቱ ድምፅ በግቢያችን ውስጥ ተሰማ።
“ወ/ሮ አሰገደች እንደምን አደሩ? ምነው ምነው ትልቅ ስው አይደሉም እንዴ!? ከልጆቼ ጉሮሮ ነጥቄ ያከራየኽዎትን የወተት ሂሳብ ሊበሉኝ ነው? ወይስ ምን ሆነው ነው ሦስት ቀን ሙሉ ያላኩልኝ? ከኔ ከደሃይቱ ይሄን በልተው ምን ሊጠቀሙ ነው? ምነው ጡር አይሆንብዎትም ወይ? ነግሬዎታለሁ! ማንንም የምፈራ እንዳይመስልዎት፤ እንቢ ካሉ ሕግ ፊት ነው የምገትርዎት እከነሽና ደብሪቱ! ‘ግዛኝ ግዣኝ ብለው፣ ሊሸጠኝ አሰበኝ’ አለ ያገሬ ሰው! ዛሬ ባይልኩልኝ ወርድ ከራሴ …” የደብሪቱ ንግግር ማለቂያም የለው …
አክስቴ መግቢያ ቀዳዳ ጠፍቷታል፤ በሹክሹክታ ታወራ ጀመር “ይቺ ሴትዮ ጤናም የላት እንዴ?”
“ምን ጤናም የላት ትያለሽ? ለምንድነው! በወቅቱ ያልከፈልሽው?” ባለቤቷ ደነፋ።
“አንተ ደግሞ ዝም በል። ቢረሳ እንኳን ላኩልኝ ይባላል እንጂ፤ በጠዋት መጥቶ ምን ያስለፈልፋል።” አክስቴ ይበልጥ ጮኸች። የግቢው ቤተሰብ በሙሉ የሴትየዋን እሮሮ እየሰማ ነው። ማንም መልስ ሊመልስ አልፈለገም። ሁሉም አድፍጦ ዝም!
ደብሪቱ ብለው ብለው ድምጻቸው ሲጠፋ መሄዳቸው ስለታወቀ ከየቤቱ ብቅ ብቅ ማለት ተጀመረ። አክስቴ ከሁሉም ቀድማ ነበር ውጪውን የረገጠችው። የወንድሟ ልጅ በራፏ ላይ ቆሟል። “ውይ ሽመልስዬ እዚህ ምን ትሠራለህ? ይቺ እብድ በጠዋት ቀሰቀሰችህ አይደል?” አክስቴ ጥፋተኛነት ተሰምቷታል።
“ምን እኔን ብቻ የሰፈሩ ህዝብ በሙሉ እኮ ነው የተረበሸው! አዋጅ የሚናገሩ ነበር የሚመስሉት። ማን ያልሰማ አለ ብለሽ ነው” ሽመልስ ነገሩን ይበልጥ አደመቀው።
“ጉድ! ጉድ! ጉድ! አዋረደችን እኮ! እስቲ በለሊት መጥቶ አፍ መክፈት ምን አመጣው የሷን ብር ይዤ እንዳልጠፋ ነው? ወይስ ገንዘብ ሆነና እንዳልክድ …?”
“ኧረ! ሕግ ፊት እገትርሻለሁም ብለዋል!”
“ሂድ! አንተ ደግሞ ነገር አታንፏቅ፤ ለሃያ ብር ነው ሕግ ፊት የምትገትረኝ!?”
“እኔ ምን አውቃለሁ፤ ሲሉ የሰማሁትን ነው”
“እሷማ ምን ያላለችው አለ! ቆይ! ግድ የለም! እማደርገውን፤ እኔ ነኝ የማውቅ።” አክስቴ ወደ በሩ አመራች።
“እንዴ አሁን ልትሄጂ ነው እንዴ?” ሸመልስ ነገሩ አላማረውም።
“አሁንማ ምን ይሁን ብዬ እሄዳለሁ። እንደሷ አላበድኩ። እንደው እንዴት እንደገባች በሩን ለማየት እንጂ ቡናዬን ጠጥቼ ቀስ ብዬ እደርሳለሁ። የማደርገውን እኔ ነኝ የማውቅ። ሁለተኛ ግን የሷን ወተት … መርዝ ያስጠጣኝ።”
* * * * * * * * * * *
የአክስቴ ቡና ደርሶ ዘመድ ተሰብስቧል፤ ሁለት ሌሎች አክስቶቼና አንድ አጎቴ እስከሚስቱ ቦታቸውን ይዘዋል። አሰግድ አለ፤ ዙሪያውን በልጅ ልጆች ተከቧል። አያታችን በምርኩዛቸው መሬቱን እያንኳኩ ቀኝ እግራቸውን እየጎተቱ ገቡ። ሁሉም ብድግ ብሎ ተቀበላቸው። ማዕከላዊውን ቦታ ይዘው ከተቀመጡ በኋላ፤ “ጠዋት እንደዛ ትለፈልፍ የነበረችው ማናት?” ጥያቄ አቀረቡ።
“ወ/ሮ ደብሪቱ ናታ” አክስቴ ወ/ሮን ጠበቅ አደረገቻት።
“ምን ይሁን ብላ?” አባባ ነገሩ ገርሟቸዋል።
“አልሰሙም እንዴ ወተት አከራይዋ …
“እኮ ምን ይሁን ብላ መጣች?” አላስጨረሷትም።
“የወተት ኪራይ ሳትከፍይ ዘገየሽ ብላ፤ ልትሳደብ ነዋ! ጨፈረችብኝ እኮ! …”
“ለመሆኑ! በሩን ማን ከፈተላት?”
“እንጃላት! እጇን አስገብታ ከፍታ ወይም አንዱ ወጥቶ ይሆናላ”
“ገብቶ ማለትሽ ነው?” አባባ ወደ አሰግድ ተመለከቱ።
አሰግድ ሽሙጡ ቢገባውም መልስ ሊሰጥ አልፈለገም። “ደግሞ እኮ ስትናገር አንገቷን የታነቀች ነው የምትመስል” አለ አሰግድ፤ የሴትዬዋ ነገር እንዲሰፋ ፈልጓል፤ ሁሉም በጅምላ ሳቀ።
“ኧረ! የሚያንቅ ይነቃትና፤ ስትታይም የታነቀች ነው የምትመስል” የእህቷ መሰደብ ያንገበገባት ትንሿ አክስታችን ነበረች። የአሰግድ ሳቅ ጎልቶ ወጣ።
“አዎን ሳቅ አንተ! ጅብም ሲጎትተኝ ብታይ ሳትስቅ አትቀር። አይ! የኛ ወንድም!” አክስቴ ተናደደችበት።
“አንችስ ለምን ሳትከፍይ ቆየሽ?” አያታችን ሌላ ጥያቄ ወረወሩ።
“እርስት አደረኩት አባብዬ”
“እርስት አደረኩት! አንቺ የረሳሽ እንደሆን እሷም መርሳት አለባት?” ሁሉም ሳቁን ለቀቀው። አባባም በራሳቸው ንግግር ይስቁ ጀመር። ወርቅ ጥርሳቸው ከግራና ከቀኝ እንደ አንፖል ያበራል።
“እናስ! የሆነ እንደሆን ሀገር ጥዬ አልኮበልል፤ በጠዋት መጥቶ መለፍለፍን ምን አመጣው? ቆይ! ግድየለም! የማደርገውን እኔ ነኝ የማውቅ …”
“አክስቴ ገንዘባቸውን ወደዚያ ወርውሪላቸው እንጂ ምንም እንዳትናገሪ” ሽመልስ ጣልቃ ገባ።
“ለምንድነው የማልናገር? አንተን ደግሞ የሷ ጠበቃ ያደረገህ ማነው? ፎቃቃ”
“አይ! ወንድማቸው የአብዮት ጥበቃ ሊቀመንበር ናቸው ሲባል ስለሰማሁ …”
“ታድያ! የሆነስ እንደሆን በጠዋት እየተነሳሽ ሰው ስደቢ ብሎ ፈቅዶላታል ማለት ነው? ማነው ከዘሯ የነገሠ?” ትንሿ አክስት ተንጣጣች። አክስቴ እየተናገረች ሥራዋን አላቋረጠችም። ቁርስ አቅርባ ተበላ። አቦል ቡና ተዳረሰ፤ አሁን ሁሉም ጎኑ ካለው ሰው ጋር ጨዋታ ጀምሯል። አሰግድ ከኛ ጋር እየቀለደ ነው፤ አባባ ጣቶቻቸውን አቆላልፈው ሁለት አውራ ጣቶቻቸውን ማገለባበጥ ይዘዋል።
ሽመልስ ገባ ወጣ ይላል። አክስቴ አልወደደችለትም። “መቀመጫህ ላይ መርፌ የተሰካ ይመስል፤ ምን ያንቆራጥጥሃል? ቡና እያፈላሁ የሚክለፈለፍብኝ አልወድም … ትቀመጥ እንደሆን ተቀመጥ!” ሸመልስ ውጭውን መርጦ ወጣ።
ሁለተኛውና ሦስተኛው ቡና ተፈልቶ ተጠጣ። አክስቴ ስኒውን አነሳስታ፣ እቃውን አጣጥባ ልብሷን ለባብሳ ተነሳች። መሃረቧ ላይ ብር ቋጥራ ያዘች። ወ/ሮ ደብሬ ዛሬ ጉዷ ፈልቷል። ሁለቱ ሌሎቹ አክስቶቼ በዛው የምንደርስበት አለ ብለው ከአክስቴ ጋር ለመሄድ እየጠበቋት ነው። አሰግድ ሥራው ሊሄድ ተዘጋጅቷል። እግረ መንገዱን ግን የደብሬን ጉዳይ ለማየት ፈልጓል። አብዛኛው የልጅ ልጅ በር ላይ እንደዘብ ቆሞ ይሳሳቃል።
በዚህ መሀል ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ። የደብሬ ልጅ እንደወትሮዋ ወተቱን በነጭ ጨርቅ ሸፍና በራፋችን ላይ ቆማ ታየች። አክስቴ እንደዛ ተናግረው ካሁን ወዲያ ወ/ሮ ደብሬ ወተት ይልካሉ የሚል ግምት አልነበራትም፤ አብዛኛውም የሚያስበው ይሄንኑ ነው።
አክስቴ ልጅቷን እንደጉድ እያየቻት “አንቺ! …” ብላ ልትናገር ስትጀምር ሸመልስ አንዳች የሚያህል ድንጋይ ይዞ እግሯ ላይ ተከመረ።
“ምንድንነው ነገሩ?” አክስቴ አንባረቀች። ሁሉም ገርሞት ሽመልስ ላይ ዓይኑን ተክሏል።
“አክስቴ ይቅር በይኝ፤ ይቅር በይኝ” ድንጋዩን አስቀምጦ እግሯን አንቆ ያዘ።
“ምንድነው ነገሩ? ጤናም አልያዘኽ? ምኑን ነው ይቅር የምልህ? ኧረ! ይሄ ልጅ አንድ በሉልኝ …” አክስቴ ቆጣ ማለት ጀመረች።
ሁሉም በጥያቄ ያጣድፈው ጀመር፤ ምንድነው? ምን አድርገሃል? አባባ ተነስተው ጎኑን በምርኩዛቸው ጎንተል አደረጉት። ተናደዋል። “ምንድንነው ያደረግኸው? አትናገርም?”
ሽመልስ ይሄን ጊዜ ተነስቶ ቆመ። ፊቱ ፀሐይ ወጥቶ የሚዘንብ ቀን መስሏል። ሳቅም ድንጋጤም ይዞታል።
“ምንድነው ምን አድርገኻል?” የአክስቴ የግንባር ቆዳ ተሰበሰበ።
“ጠዋት …”
“እ … ጠዋት”
“እማማ ደብሬ”
“እ … እማማ ደብሬ ትናገር እንደሆን ተናገር” አክስቴ ይበልጥ ተናደደች።
“እማማ ደብሬ አልመጡም።”
“ታድያ! ማነው እንደዛ ይለፈልፍ የነበረው? እኔ ነኝ እንዳትለኝ ብቻ” አክስቴ አፏን ይዛ ዓይኗን አፈጠጠች።
“አዎን! እኔ ነኝ አክስትዬ ይቅርታ አድርጊልኝ” እንደገና እግሯን አንቆ ያዘ። ሁሉም ሳቁን ለቀቀው አክስቴ እንደመሳቅ እያለች ከእግሯ ላይ ካነሳችው በኋላ እጁን ቀጨም አድርጋ ይዛ “እስቲ እንደጠዋቱ ተናገር” አለችው።
ሽመልስ በአንድ እጁ ጉሮሮውን ይዞ ድምፁን አስተካክሎ መናገር ጀመረ፤ “ወ/ሮ እጅጋየሁ እንደምን አደሩ? ወር ሙሉ ወተቴን ጠጥተው ገንዘቤን ያላኩልኝ ምን ሆነው ነው? ምነው ነውር እማይደል …?”
ጠዋት የተሰማው የደብሪቱ ድምፅ በድጋሚ ግቢውን ሞላው።
(Photo: ILRI – ወ/ሮ ደብሪቱ አይደሉም)

 http://www.goolgule.com/debritus-milk/

Friday, September 27, 2013

የጤፍ ጥቅም የገባው የባህር ማዶው ድርጅት የጤፍ ጭማቂ እየሸጠ ነው፡፡



በካልሲየም፣ አይረን፣ ፎስፈረስ፣ ኮፐርና ማንጋኒስ ማዕድናት የዳበረ ነው፡፡ ከቫይታሚኖችም በቫይታሚን ቢ1፣ ቢ2 እና ኬ የበለጸገ ነው - ጤፍ፡፡ አብዛኞች ኢትዮጵያዊያን በየቀኑ የምንመገበው ጤፍ ከሌሎች በርካታ በረከቶች በተጨማሪ አንድ በተለይ በዚህ ዘመን በጣሙን ተፈላጊ የሆነ ባህሪ አለው፡፡

ግሉቲን…

አዎን ጤፍ ግሉቲን የለውም !

ግሉቲን፣ በእንደነ ስንዴና ገብስ ያሉት አዝርዕት ውስጥ የሚገኝ የፕሮቲን አይነት ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ሰውነታቸው ግሉቲንን ስለማይቀበል ለችግር ይጋለጣሉ፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት…በሌሎች ንጥረ ነገሮች የዳበረ ሆኖ ለዚህ “ሰውነት ግሉቲንን ላለመቀበል” ችግር ለተጋለጡ ሰዎች ከጤፍ የተሻለ አማራጭ ፈፅሞ አልተገኘም፡፡

በአንድ ወቅት፣ “ጥቂት ብረት ቢኖረው እንጂ ያን ያህልም ዋጋ የለውም” ተብሎ የተብጠለጠለው ጤፋችን፤ በቅንጣቱ ውስጥ ታላቅ በረከት እንደሰነቀ እየታወቀ ነው፡፡

ለዚህም ነው አማንዳ የተባለው ድርጅት የጤፍ ጭማቂ አዘጋጅቶ በኢንተርኔት መሸጥ የጀመረው፡፡ Amazon.com የተባለው ትልቁ የኢንተርኔት መጽሀፍትና የሌሎች ምርቶች ሻጭ ድረ ገጽም የጤፍ ዱቄት እያሸገ መሸጥ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የድሬቲዩቡ ግሩም እንዳዘጋጀው

ሀገር ማለት

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ አስቀድሞ ደራሲ በዓሉ ግርማ በኋላም ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ግጥሞቻቸውን ጽፈው ነበር፡፡ ሌላም የጻፈ ይኖራል፡፡ ነገር ግን እነኝህ የሥነ-ጽሑፍ ሰዎች ግጥሞቻቸውን ሲጽፉ የተቆነጸለ ወይም የተሳሳተ ትርጉም ሊያሰጥ በማያስችል ሁኔታ ግጥሞቻቸውን ባለመጻፋቸው እንደምገምተው እነሱም ሊሉ ባልፈለጉት መንገድ ተተርጉሞ የቅጥረኞች መጠቀሚያ እስከመሆን ድረስ በቃና ሕዝብን ለማደናገሪያ አገለገለ፡፡ ከሕዝቡ ጥቂት የማይባል ወገንም በመወናበድ ይሄንን የተሳሳተ ትርጉም ይዞ ማንጸባረቅ ያዘ፡፡ ይህም መሆኑ ሀገር በሕዝብ ልብ ውስጥ የነበራት ቦታና ትርጉም ከመዛባቱም ባሻገር በወደፊት የሀገር ህልውና ላይ ከባድ አደጋ የጋረጠ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ እናም እንደዜጋ አሳሰበኝና ይሄንን የተሳሳተ ትርጉም ለማረም የሀገርን ትርጉም ሳይቆነጸል ሳይጎነጠል ለማስፈር ተገደድኩና ይህችን ግጥም ጻፍኩ፡፡ ግጥሙ እንዳልኩት የሀገርን ምንነትና ሙሉ ትርጉም ለማስቀመጥ ሲባልና ሁሉም ሰው ሊገባው ሊረዳው በሚችል አገላለጽ ሲገለጽ ትንሽ ሊረዝም ችሏል፡፡ ለዚህ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በግጥሙ ላይ የተገለጹትን ተግሳጾችንና ስድቦችን ሁሉንም በግጥሙ ላይ ከተወከለው ገጸ ባሕርይ ተውሻለሁ ለራሱ ለባለቤቱ መመለስ ይኖሩባቸዋልና፡፡
ሀገር ማለት:-
አየ የኛ ተርጓሚ ፤ በቃላት ፍች ተራቃቂ
ወግ አሳማሪ ቀማሚ ፤የነገር ብልት ዐዋቂ
ከቃላት ሁሉ የከበደን ፤በሰዋስው ቃል እርባታ
ከምሥጢራት እረቂቁን ፤ሲተረጉሙት ባአንድምታ
ጠሊቅ ሰፊ ጥጥሩን፤ ሲተረተር ሲፈታ
በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀቱ ፤ያለሀፍረት ያለይሉኝታ
ተርጓሚ ነኝ አለና ፤ሞከረና ሊያምታታ
ሀገር ማለት ወንዝ አይደለም ፤ጋራ ሸንተረር ድንበር
ሀገር ማለት ሰዉ ነው ፤ብሎ ነገረን መምህር
ግድ የለኝም አይገባኝም ፤ለወንዙ ጋራው ሸንተረር
እያለ ተረጎመልን ፤አምልጦት ከከንፈር
አንጀትም የበላ መስሎት ፤ልባችንን ሊሰረሥር
አቤት አቤት ማስመሰል ፤አቤት አቤት አለማፈር
ለሕዝብ ሰብአዊ መብቶች፤ እንደሚያስብ በመቆርቆር
እንደሚመኝ እንደሚሰጥ ፤ለዜግነታቸው ክብር
ለማያውቁሽ ታጠኝ አያ ፤ ስንት እያለ የሚያይ አሣር
ያለ ሥራው ባልዋለበት ፤ መብቴን ስላለ ለመኖር
ዜጋነቱን እስኪረግም ፤እስኪጠላም መፈጠር
ለሕዝብ ጥሩ በተመኘ ፤መልካም በሠራ ለሀገር
ከሕዝቡ ዓይኑን የገለጠው ፤ለሀገር ይጠቅም የነበር
ታዲያ እሱ ግድ ከሌለው ፤ይቆራረስ የካሳ ሀገር
ለዚህ ኖሯላ ቀድሞውን ፤ስንት ዋጋ ስንት አሣር
ስንትና ስንት መስዋዕትነት ፤ የተከፈለበትን ምድር
እየገመደልክ ያደልከው ፤ ማንነኝ እኔ ሳትል ሳታፍር
የቃሉ ትርጉም ነው ብለህ ፤ ሊቅ ዐዋቂ መስለህ መምህር
ለማምታታት ማወናበድ፤ተመኝተህ እንድንደነቁር
ቃል በቃላት ሲተረጎም ፤እንዲህ ነው ተብሎ ሲነገር
እራሱን ቃሉን ነው እንጂ ፤በውስጡም ያለውን ምሥጢር
ምኞትን ማውራት አይደለም ፤ከቶም የማይመስል ነገር
ስሕተትህን ልክ ለማድረግ ፤ላለመዋረድ ላለማፈር
በሚገባ ስላወከው ፤ተሳስተህ እንደነበር
በእቃ እቃ ፍልስፍናህ ፤ የትም በሌለ ባልሠለጠነ
እየገመደልክ ማደልህ ፤ መፍትሔያችን እንዳልሆነ
ጊዜ ገልጦ ካስረዳህ ፤እንደመመለስ ወደ ምክር
ስሕተትህን ላለማረም፤ ከስሕተትህ ላለመማር
ሀገር ማለት ወንዝ አይደለም ፤ ጋራ ሸንተረር ድንበር
ብለህ ዐረፍከው አኞ ግትር ፤ የእኛ ዐዋቂ የኛ ምሁር
ምንነበረበት አሁን ፤ ይቅር በሉኝ ማለት ብትደፍር
ይሄው አይደል ድንቁርና ፤ ለራስ የማይበጅ ለሀገር
የከአፈርኩ አይመልሰኝ ፤የደናቁርት ፈሊጥ ቁማር
አንተ የእነሱው ፈላስፋ ፤የእኛው ደንቆሮ ልበ እውር
እንዲያው በሞቴ እባክህ ፤ሙታ ጉዳይህ ካላልከኝ
አንድ ነገር ልጠይቅህ ፤ሳትሸሽ ሳትዋሽ መልስልኝ
ሀገር ማለት ለኔ ሰው ነው ፤ያልክለትን ሰው ህልውና
ያለ መሬቱ እስኪ አሳየኝ፤ እንዲህ እንዲህ ነዋ በልና
አቃፊው ደጋፊው ቀርቶ ፤ማረፊያ መጋቢው ሳይያዝ
በልእኮ እንደምን ሆኖ ነው ፤ሀገር የምንለው አንት ውጉዝ
በላ ተናገር አይጭነቅህ ፤ አይደለም ወይ አፍህ ደኅና
መሠረት አልባ ነው እንዴ ፤ልጆችህ ያሉት ፍልስፍና
ባዶ ቅዠት ነው እንዴ፤የማይጨበጥ ደመና
አየህ የአንተን ዐለማወቅ ፤ድቅድቅ ድውይ ድንቁርና
መልስ አሳጣህ አስፈጠጠህ ፤ይሄ ብቻ ገና ገና
የማይነጣጠሉትን ከቶም፤የነፍስ የሥጋን ዝምድና
ለመነጣጠል ስትሞክር ፤በድን ለማድረግ ሙት መና
ቀን ሲያጋልጥህ አዋረደህ ፤መቼምም አትልም ቀና
የሚገርመው የሚደንቀው ፤ አንተ ባታውቅ ባትረዳ
ለራስህ ምንም አልነበር ፤ለእኛም መትረፉ እንጅ የጎዳ
የአንድ ሀገር የሀገሩም ሕዝብ ፤እጣ ፋንታው ሁሉ እንዳለ
የነበረውም ዋጋ ያለው ፤ሀገርን ከሌላው ያለዐለ
በአንተ እንጭጭ አስተሳሰብ ፤በማይዋጠው ተወዶ
የማማረጥ ዕድል ሳትሰጥ ፤እንዲወድቅ ማድረግህ ተቀዶ
ከሥር ነቅሎ አንጓለለን ፤ሁሉን ነገር አርጎ ባዶ
ገናገና መች ዓየነው ፤አለብን ገና ብዙ ዕዳ
የቀበርክብን ቦምብ በዕያይነት ፤ጊዜ ጠብቆ ሲፈነዳ
ከሸር ክፋት ተንኮልህ ፤መራሩና የበሰና
እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ፤በአህያ ሰብእና
ከህልውናህ ማጣመርህ ፤የሀገርን ህልውና
እንዳንተ አይሆንም እንጅ ፤አምላከ አበው አለና
ጠባብ ዘረኛ ከሆነ ፤ከዚህ ሌላ የጠበቀ
እሱ የዋሕ ነው ተላላ ፤ሥነ ልቡናን ያላወቀ
ሀገር ማለትስ ወገኔ ፤ሳትሸራረፍ ተቆራርጣ
ከጥንቱ ከመሠረቱ ፤ከሊቃውንቱ የመጣ
የሰው ልጅ ብቻ አይደልም፤ ነውም እንጂ ሳይቀር ሣሩ
እንስሳት አራዊት አዕዋፍ ፤ያለው ነገር ሁሉ በምድሩ
ከዳሸን እስከ ዐባይ አዋሽ፤ከዋልያ እስከ ግራሩ
ከዋዕይ ቃጠሎው ዳሎል ፤እስከ ደጋው ብርድ ቁሩ
ያለው ነገር ሁሉ ነው ፤አጥረህ የያዝከው በድንበሩ
ከቶውንም ጆሮ እንዳትሰጥ ፤እንዳትደነቁር በምክሩ
መቆሚያም እንኳን ታጣለህ ፤እንኳን መኖሪያ በኩራት
ሀገር ማለት መሬት አይደል፤እያልክ ቆራርሰህ በመስጠት
ከሀገር ትርጉም ዐቢዩ ፤ባይሆን ኖሮ ምድር መሬት
ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ፤ዘመድ ወዳጁ ያለበት
ተፋቅሮ የሚተሳሰብ ፤ተግባብቶ ያለው በኅብረት
ተነቅለህ ሄደህ ባለህበት ፤ እየተዋከብክ በውርደት
ስደተኛ መጻተኛ ፤እያሉ ስምክን ባልጠሩት
በሀፍረት ባልተሸማቀክ ፤ባላስደፋህ ባይተዋርነት
ልብ አድርግ ወገኔ ስማኝ ፤ሲዘረዘር ሀገር ማለት
ሀገር ማለት ሰንደቅ ናት ፤የቃልኪዳኑ ምልክት
ሀገር ማለት ሃይማኖት ናት ፤በቃሉ የነገረላት
ሀገር ማለት ጥበብ ናት ፤ተራቀው የማይጨርሷት
ሀገር ማለት ዕውቀት ናት ፤ብርሃን የሞላት ፍኖት
ሀገር ማለት ታሪክ ናት፤ማንነትህ የሚታይበት
ሀገር ማለት ቅርስ ናት፤ አሻራህ ቀርጾ ያወጣት
ሀገር ማለት ውርስ ናት፤ጸጋ ሀብት የምታፍስባት
ሀገር ማለት አደራ ናት ፤በእንክብካቤ የምትጠብቃት
ሀገር ማለት እናት ናት፤እጅጉን የምትወዳት
ሀገር ማለት አባት ናት ፤በጣሙን የምትኮራበት
ሀገር ማለት ሚስት ናት ፤ በፍቅሯ የምትሞትላት
ሀገር ማለት ልጅህ ናት ፤ በኃያሉ የምትሳሳላት
ሀገር ማለት ልጅህ ናት ፤ ደጀንነቱ የሆነህ ትምክሕት
ሀገር ማለት ወገን ናት ፤ መጠጊያ የምትሸሽበት
ሀገር ማለት ሕዝብ ናት ፤ብዙውን በአንድ ያዋሐደች ቋት
ሀገር ማለት ወግ ባሕል ናት ፤ ስትኖረው የምትደምቅበት
ሀገር ማለት ዙፋን ናት ፤ሉዓላዊ የሥልጣን ሹመት
ሀገር ማለት ዘውድ ናት ፤ግርማ ሞገስን የምትደፋባት
ሀገር ማለት ማዕረግ ናት ፤ልብ የምትሞላ በሐሴት
ሀገር ማለት ጌጥህ ናት ፤የሚሳሱላት የክት
ሀገር ማለት ክብር ናት ፤ በምንም የማይለውጧት
ሀገር ማለት ኩራት ናት ፤ ደረትህን የምትነፋባት
ሀገር ማለት ጽናት ናት ፤ የማይሠበር የማይወድቅ ቁመት
ሀገር ማለት ጀብድ ናት ፤የሠራት የጀግና ድፍረት
ሀገር ማለት አንድነት ናት ፤መነጣጠሉ የሚያፈራርሳት
ሀገር ማለት ፍቅር ናት ፤መሥዋዕትነት የማይፈሩላት
ሀገር ማለት እፎይታ ናት ፤ ምቾት የሞላት ዕረፍት
ሀገር ማለት ሥጋት ናት ፤የምትነሳ እንቅልፍ ቀን ከሌት
ሀገር ማለት ማተብ ናት ፤የማትፈታ ከአንገት
ሀገር ማለት ሕመም ናት፤ ስቃይዋ ዜማ ማኅሌት
ሀገር ማለት ጤና ናት፤የሕይወት መድኅን መድኃኒት
ሀገር ማለት ምሥጢር ናት፤ገመናን የምትከትባት
ሀገር ማለት ፊደል ናት ፤የሚገለጥባት የውስጥ ስሜት
ሀገር ማለት ሀቅ ናት ፤የልብ የኅሊና ሀብት
ሀገር ማለት ምግብ ናት ፤ሰውነት የምትራባት
ሀገር ማለት ጥማት ናት፤ ሲጠጧት የምትሰጥ ሕይወት
ሀገር ማለት ሥራ ናት ፤የህልውናህ መሠረት
ሀገር ማለት ዋስትና ናት፤ለሁሉም የምትቆምለት
ሀገር ማለት ደስታ ናት፤ የልብ ሰላም ሥምረት
ሀገር ማለት ሐዘን ናት፤የግድ ምንሠዋላት
ሀገር ማለት እርስትህ ናት፤ማርና ወተት የምታልብባት
ሀገር ማለት ጉልትህ ናት፤ሁሉንም የምትሆንባት
ሀገር ማለት ሁሉንም ናት፤የምናውቅ የማናውቀው
ሀብት አዎ ኢትዮጵያ ማለት መሠረት ናት ፤የምድርን ካስማ የተከለባት
ኢትዮጵያ ማለት የትም የሚያዩዋት ጉልላት ናት ፤የዓለም ጣራ ጠፈራት
ኢትዮጵያ ማለት የገባርት እርሻ ናት ፤የምትመግብ ዘለለት
ኢትዮጵያ ማለት የካህናቱ ጸሎት ናት ፤ከአምላክ የምታወርድ ምሕረት
ኢትዮጵያ ማለት የወታደሩ ትጥቅ ናት ፤የጠላት መቅሰፍት ወመዓት
ኢትዮጵያ ማለት የከያኔያን ጥበብ ናት ፤ዘወትር የሚቀኛት በስሜት
ኢትዮጵያ ማለት የመምህራን ሀሁ ናት፤ቁልፍ ምሥጢሩ ለዕውቀት
ኢትዮጵያ ማለት የነጋዴያን ንብረት ናት ፤እያደር የምትበረክት
ኢትዮጵያ ማለት የጋዜጠኞች እውነት ናት ፤ለክፉው የምትመር ሀሞት
ኢትዮጵያ ማለት የመሐንዲሶች ትልም ናት ፤የምትጠቅስ ሰማየ ሰማያት
ኢትዮጵያ ማለት የአብራሪዎች ዓለም ናት ፤የማትለየው በየሄደበት
ኢትዮጵያ ማለት የዳኞች ፍትሕ ናት ፤ሚዛኑ የሚፈርድበት
ኢትዮጵያ ማለት የሐኪሞቹ መድኃኒት ናት ፤ፈውሳ የምትሰጥ ሕይወት
ኢትዮጵያ ማለት የስፖርተኞቹ ጥረት ናት ፤ድል የምታቀዳጅ ጽናት
ኢትዮጵያ ማለት የሾፌሮቹ መንገድ ናት ፤ቢጓዝ የማይጨርሳት
ኢትዮጵያ ማለት የአናጢዎቹ መለኪያ ናት ፤የምትመጥን እንደ ፍላጎት
ኢትዮጵያ ማለት የግንበኞቹ ውኃልክ ናት ፤የምታስቀምጥ ያለመዛባት
ኢትዮጵያ ማለት የቀጥቃጮቹ እሳት ናት ፤አቅልጣ የምትቀርጽ ብረት
ኢትዮጵያ ማለት የወዛደሮቹ ጋዕር ናት ፤ነጭ ላቡ የምትወርድ በአንገት
ኢትዮጵያ ማለት የኮረዶቹ ሽልም ሞሰብ ናት ፤ነገዶች የተሠፉባት በአንድነት
ኢትዮጵያ ማለት የቆራጥ መሪ ዓላማ ናት ፤ተሳክቶ ሊያያት የሚሻት
ኢትዮጵያ ማለት የመሀይማን ዕውቀት ናት ፤ከምሁራኑም የሚልቁባት
ኢትዮጵያ ማለት ንግሥት ናት ፤ ተፈጥሮ የገበረላት
ኢትዮጵያ ማለት ጥበብ ናት ፤ ሥነ-ኪን ያረገደላት
ኢትዮጵያ ማለት መቅደስ ናት ፤ አማልክት የሚቀናኑባት
ኢትዮጵያ ማለት የሁሉም ሁለ ነገር ናት ፤ለሁሉም የሆነች ሕይወት
አይ አይ ተሳሳትኩ መሰለኝ ፤የለም አይደለም ከእነዚህ ፤ከእነዚህም ሁሉ በላይ ናት
በመሆኗም ነው ልጆቿ ፤ እነዚህን ሁሉ ጣል አርገው ፤ትተው ቁጭ አርገው የሞቱላት
በል እንዳትሞኝ ወገኔ፤ በቅጥረኛ ባንዳ ሰበካ
ነቅተህ ጠብቅ ድንበርህን፤እንኳን መስጠት አታስነካ
እንደአባት እናትህ ሳሳላት፤ዘራፍ በልላት ጦር እንካ
የነሱን አጥር አስከብር፤አደራቸውን እንዳትበላ
ደም አጥንታቸው እዚያ አለ ፤ዋ ይወቅስሃል በኋላ
ለዚህ አማላጅ የለውም ፤አለበት ጽኑ መሐላ
ለህልውናዋ ሙትላት፤ ለነፍስህ አላት ከለላ
እስካሁን እንደነበረች ፤ለዘለዓለምም ያለ ዲካ
አንተ ሞተህ ሕያው አርጋት፤እንዳትነጠቅ ተማርካ
ለመኖር ለባዕድ ሰጥተሀት፤ ያንተም ሳትሆን ከምትቀር
ሞተህ ለልጅህ አድርጋት ፤በሞት ወርሰሃት ተከበር
በልጅ በዘመድ ትኖራለህ፤ለዘለዓለም ቀርጸህ ዱካ
ተጠብቃ ትኖራለች፤ያለችግር ያለ ሳንካ
ደም አጥንትህ ያስከብራት፤ትውልድም ባንተ ይመካ
ያንተነቷ እንዲጸና ፤ምኞት ሕልምህ እንዲሳካ
ደም አጥንትህ ያስከብራት ፤ ትውልድም በአንተ ይመካ
የአንተነቷ እንዲጸና ፤ ምኞት ሕልምህ እንዲሳካ
ሰኔ 2002 ዓ.ም.
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com 

http://sodere.com

የመስቀል በዓል በጉራጌዎች ዘንድ – ከቅዱስ ሃብት በላቸው (ከአውስትራሊያ) [ጋዜጠኛ]


kitfoቅዱስ ሃብት በላቸው (ከአውስትራሊያ)
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበሩት አውደ-ዓመቶች አንዱ ነው።
የቤተክርስቲያናችን የታሪክ መፅሃፍት እንደሚገልፁት አይሁዳውያን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ደብቀው ቀብረውት ከ300 ዓመታት በላይ ስፍራው ሳይታወቅ ቆይቷል። በ326 ዓ.ም. ላይ ግን የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ፣ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ የት እንደሆነ ፍንጭ አገኘች። ከዚያም በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት ባቀጣጠለችው ጊዜ፣ ጢሱ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች።
ንግሥተ እሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣቸው ይነገራል። ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንኑ ታሪክ ተንተርሶ ነው።
የመስቀል በዓል በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙት በጉራጌ፣ በጋሞ፣ በከምባታ፣ በሃድያ፣ በወላይታ …ወዘተ ብሔረሰቦች ዘንድ ከሌሎቹ የቤተ ክርስቲያኗ በዓላት በተለየና በደመቀ መልኩ እንደሚከበር ይታወቃል።
በተለይም በጉራጌዎች ዘንድ ከሌሎች የሃይማኖቱ በዓላት ይበልጥ ደምቆ የሚከበር አውደ-ዓመት በመሆኑ ሁሉም በከፍተኛ ናፍቆት የሚጠብቀው ነው። በዓሉ እየተቃረበ ሲመጣ በጠንካራ ሰራተኝነታቸው የሚታወቁት ጉራጌዎች ዓመቱን ሙሉ ጥረውና ግረው ያገኟትን ጥሪት በመቋጠር በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ወደትውልድ መንደራቸው ይተማሉ። በብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ በተለይም በመስቀል በዓል ወቅት የሚሰጠው የአባትና እናትም ሆነ የሌሎች ሽማግሌዎች ምርቃት ትልቅ ቦታና ክብር የሚሰጠው በመሆኑ ይህ እንዲያልፈው የሚፈልግ የጉራጌ ልጅ የለም ማለት ይቻላል።ለመስቀል ልጆቻቸው ሳይመጡ የቀሩባቸው ወላጆች የበታችነት ስሜት ስለሚሰማቸው ከፍተኛ ቅሬታ ያድርባቸዋል።
በገጠር ለዚህ በዓል ዝግጅት የሚጀመረው ቀደም ተብሎ ሲሆን፣ ራቅ ያለ አካባቢ የሚኖሩ ልጆች ገጠር ለሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ፣ ሳሙና፣ ጨው፣ ጋዝ፣ ልብስ፣ ….ወዘተ ይልካሉ። በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችም በጋራ ሆነው ለበዓሉ ግብዓት የሚሆን እንሰት ይፍቃሉ፣ ለእንግዶች መቀመጫ የሚሆን ምንጣፍ (ጅባ) እንዲሁም ከቃጫ የሚሰራ የምግብ ማቅረቢያ በጋራ ይሰራሉ። ባንፃሩ ወንዶችም ለማገዶ የሚሆን እንጨት በመፍለጥ ያዘጋጃሉ። ይህም በብሔረሰቡ አነጋገር «የዌሬታ» በመባል ይታወቃል።
የበዓሉ ቀን እየተቃረበ ሲመጣም ሴቶች አረቄ በማውጣት፣ ጠላ በመጥመቅ፣ ሚጥሚጣ … ወዘተ በማዘጋጀት ስራ ይጠመዳሉ። መኖሪያ ቤቶችም ኖራ እና ቀለም እየተቀቡ አሸብርቀው እንግዶችን ለመቀበል ይሰናዳሉ።
በጉራጌዎች ዘንድ መስቀል መከበር የሚጀምረው ከመስከረም 13 ቀን ጀምሮ ነው። ይህም ቀን «የሴቶች በዓል» በመባል ተለይቶ የሚታወቅ ሲሆን በዕለቱም በቅቤና በአይብ ያበደ የጎመን ክትፎ ለበዓሉ ታዳሚዎች ቀርቦ በቆጮ ይበላል። ይህም እንደ ሴቶች ሙያ መፈተሻ ተደርጎ ስለሚወሰድ ምግቡ የሚዘጋጀው ከወትሮው በተለየ እጅግ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው።
ተከታዪ ቀን (መስከረም 14) ደግሞ «ይፍት» በመባል የሚታወቅ ሲሆን በዋነኛነት የልጆች በዓል ተደርጎ ይወሰዳል። በዕለቱ በየመንደሩ የተተከሉ ትናንሽ ደመራዎች ተለኩሰው በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በጋራ ተሰባስበው እየበሉና እየጠጡ ሲጫወቱ ልጆችና ወጣቶች እየዘፈኑ ይጨፍራሉ። ይህ በዕለቱ የሚለኮሰው ዳመራ «የዴንጊ እሳት» ይባላል።
መስከረም 15 ቀን ደግሞ ዋናው የበዓል ቀን ነው ማለት ይቻላል። በዕለቱ ቤተ ዘመዶች በዕድሜ አንጋፋ ከሆኑት ሽማግሌ ቤት ተሰብስበው ወንዶች ሊታረድ የተዘጋጀው ከብት ላይ እጃቸውን በመጫን በሽማግሌዎች ይመረቃሉ። የምርቃቱ ስነስርዓት እንደተጠናቀቀም ከብቱ ተጥሎ እየተበላና እየተጠጣ ጭፈራው ይቀልጣል። ይህ ስነስርዓት በአገርኛው ቋንቋ «ኬር» በመባል ይታወቃል።
መስከረም 16 ቀን ሁሉም ሰው ያዘጋጀውን ችቦ ይዞ የአካባቢው ማዕከል የሆነ ቦታ አስቀድሞ ወደተተከለው ግዙፍ ዳመራ ያመራል። በሃይማኖት አባቶችና በሽማግሌዎች ፀሎትና የምርቃት ስነስርዓት ከተከናወነ በኋላም ዳመራው ይለኮሳል። ቀደም ባለው ዓመትም ስለት ተስለው የደረሰላቸው ሰዎች ስለታቸውን ያቀርባሉ። በጉራጌዎች ዘንድ መስቀል የተኳረፈ የሚነጋገርበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የበደለ የሚክስበት፣ ነው። በዚህም የተነሳ በአካባቢው የተጣሉ ሰዎች ካሉ እርቅ ሳይወርድ በምንም አይነት ዳመራው አይለኮስም። በዚህ በኩል የአካባቢው ሽማግሌዎች ደም የተቃቡ ባለጋራዎች እንኳን ቢሆኑ ይቅር እንዲባባሉ በማድረግና ፍፁም ዕርቅ እንዲወርድ በማድረግ ከቀደምት አባት እናቶቻቸው የወረሱትን የሚያኮራ ባሕል ተግባራዊ ያደርጋሉ። በዚህ ስነስርዓት ላይ የታረቁ ሰዎችም ከዚያ በኋላ ወደቀደመ ጠባቸው መመለስ መጥፎ ነገር እንደሚያመጣ (እንደሚያስቀስፍ) ስለሚታመን በዳመራው ዕለት የታረቁ ባለጋራዎች መሃል የወረደ ሰላም ዘላለማዊ ነው ማለት ይቻላል።
መስከረም 17 ቀን ደግሞ ከቀናት በፊት ለበዓሉ የታረደው በሬ ሻኛ (ንቅባር) እንዳይበላሽ በጥንቃቄ ከተቀመጠበት እንዲወጣ ተደርጎ በአባት ወይንም በታላቅ ወንድም ቤት ውስጥ በሚጥሚጥና በቅቤ እየተለወሰ እየተበላና እየተጠጣ ጨዋታው ይደራል። በዚህ መልኩ በደመቀ ሁኔታ የሚከናወነው የመስቀል በዓል የሚጠናቀቀው እርዱ በተከናወነ በሳምንቱ ሲሆን ዕለቱም «አዳብና» በመባል ይጠራል።
ባጠቃላይ ከ«ንቅባር» (በዓሉ ከተጀመረበት ዕለት) አንስቶ እስከ አዳብና ድረስ የሚከበረው የመስቀል በዓል ለቤተ-ጉራጌዎች የመጠያየቂያ፣ የመደሰቻ፣ በሽማግሌዎች የመመረቂያ፣ ለአቅመ አዳም የደረሱት ለጋብቻ የመተጫጪያ፣ ለተጣሉ የመታረቂያ፣ በመሆኑ ለመስቀል ጓዙን አሰናድቶ ወደትውልድ አገሩ የማያቀና የብሔረሰቡ ተወላጅ ጥቂት ነው ማለት ይቻላል።
መልካም በዓል ይሁንልን!

zehabesha.com

“ወሲባዊ ጂሃድ (ጂሃድ አል-ኒቃ)” በሶሪያ! ሳዑዲ ሞት የፈረደችባቸውን ወደ ሶሪያ አዝምታለች


የቱኒዚያ ሴቶችና ልጃገረዶች በሶሪያ የአሳድን መንግሥት እየተፋለሙ ከሚገኙት እስላማዊ አማጺያን ጋር “ወሲባዊ ጂሃድ” በመፈጸም በጦርነቱ ላይ ተሳትፏቸውን እየገለጹ መሆናቸው ተነገረ፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ ጦርነት ላይ በሳውዲ አረቢያ የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ወንጀለኞች እንዲሳተፉ እየተላኩ መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡
በያዝነው የመስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ የቱኒዚያው የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሎትፊ ቢን ጄዱ በአገሪቱ ፓርላማ ፊት ቀርበው እንደተናገሩት በጦርነቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙት ተዋጊዎች ማደፋፈሪያ እንዲሆንና በትግሉ የነርሱንም ድርሻ ለመወጣት የቱኒዚያ ሴቶችና ልጃገረዶች ራሳቸውን በ“ወሲባዊ ጂሃድ” በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ሎትፊ ቢን ጄዱ (ፎቶ: አልጃዚራ)
በአረቡ ዓለም በሚገኙ የዜና ማሰራጫዎች በሰፊው የተዘገበው ይህ ዜና እንደሚያስረዳው ሚኒስትሩ ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ “እነዚህ ሴቶች” አሉ ሚኒስትር ቢን ጄዱ “እነዚህ ሴቶች (ሶሪያ በሚቆዩበት ጊዜ) ከ20፣ 30፣ 100” አማጺያን ጋር በመተኛት የወሲብ “አገልግሎት” ይፈጽማሉ፡፡  “ወሲባዊ ግንኙነቱንም የሚያደርጉት በ“ጂሃድ አል-ኒቃ” (ማለትም ወሲባዊ ቅዱስ ጦርነት) ስም ሲሆን ወደ ቱኒዚያ የሚመለሱትም እርጉዝ ሆነው ነው” በማለት ሚኒስትሩ ለተከበሩት የፓርላማው አባላት በግልጽ አብራርተዋል፡፡
ከጂሃዲስቶቹ ልጅ አርግዘው የሚመጡት ሴቶች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ሚኒስትሩ አልጠቆሙም፡፡ ሆኖም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በጉዳዩ ላይ እንደሚሳተፉ ከዚህም በተጨማሪ ከ3ሺህ በላይ ቱኒዚያውያን የአማጺያኑን ኃይል ለመደገፍ እንደዘመቱ ይነገራል፡፡ ይህ የቱኒዚያውያኑ ቁጥር በአሳድ ላይ ጂሃድ በማወጅ የሶሪያን አማጺዎች ከተቀላቀሉት የሌላ አገር ዜጎች ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ ነው፡፡
ሚኒስትሩ እንደሚሉት ከሆነ እርሳቸው ሥልጣን ከያዙ ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ “ስድስት ሺህ ያህል ወጣቶች በሶሪያ የእርስበርስ ጦርነት እንዳይሳተፉ ለመከልከል” መቻሉን ለፓርላማው አስረድተዋል፡፡ አል አረቢያ ሚኒስትሩን ጠቅሶ እንደዘገበው የቱኒዚያን ድንበር በማቋረጥ ወደ ሶሪያ ለመዝመት የሚፈልጉ ወጣቶችን ለመከላከል በቱኒዚያ የድንበር ቁጥጥር መጠናከሩን ገልጾዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ድንበር በማሻገር ተግባር ላይ የተሰማሩ 86 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አል አረቢያ ጨምሮ ዘግቧል፡፡

አቡ ኢያድ አል-ቱኒዚ (ፎቶ: አል-ማስዳር)
ጂሃድ አል-ኒቃ ስም ከጋብቻ ውጪ ከበርካታ ሰዎች ጋር ለወሲብ መተኛት በአንዳንድ አክራሪ የሱኒ ሙስሊም ሳላፊስቶች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቅዱስ ጦርነት (ጂሃድ) ነው፡፡ ይህ በሶሪያ ተከስቷል ተብሎ መነገሩ የሙጃሂዲኑን ቅስም ለመስበር የተደረገ የአሳድ ሴራ ነው በማለት የሚኮንኑት አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ወሲባዊ ጂሃድ” በሶሪያ እንዲካሄድ የሚመሩት አንሳር አል-ሻሪያ የተባለው በቱኒዚያ የዋንኛው ሳላፊስት እንቅስቃሴ መሪ የሆኑት አቡ ኢያድ አል-ቱኒዚ ናቸው በማለት የሚወነጅሏቸውም በርካታዎች ናቸው፡፡
በአረቡ ዓለም ጉዳይ ላይ የሚዘግቡ የዜና ምንጮች እንደሚሉት ግን “ወሲባዊ ጂሃድ” እንዲካሄድ የተደረገው “በፋትዋ” (እስላማዊ ትዕዛዝ) ነው ይላሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ፋትዋውን ያወጡት በሳውዲ አረቢያ ወግአጥባቂ የሳላፊ (ዋሃቢ) መሪ ሼክ ሞሃመድ አል-አሪፊ እንደሆኑ በተለይ ፕሬስ ቲቪ ምንጮቹ ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ “የአጭር ጊዜ ጋብቻ ወይም ጊዜያዊ ጋብቻ” በሶሪያ ለሚፋለሙት አማጺያን እንደሚያስፈልግና ይህ እንደ ሼክ ሞሃመድ አባባል “የወሲብ ጋብቻ” የአማጺያኑን ቁርጠኝነት የሚያደፋፍር በመሆኑ እስከ 14ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣት ልጃገረዶችና ሴቶች ሊሳተፉ እንደሚገባና በዚህ ተግባር የሚሳተፉ ሴቶች ሁሉ “ጀነት (ገነት)” የእነርሱ እንደምትሆን ሼኩ ቃል መግባታቸው ፕሬስ ቲቪ አክሎ ገልጾዋል፡፡

ሼክ ሞሃመድ አል-አሪፊ (ፎቶ: Press TV)
ይህ ከተሰማ በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ፍጹም የተከለከለ (ሃራም) መሆኑን የቀድሞው የቱኒዚያው ታላቁ ሙፍቲ ሼክ ዖትማን ባታኪ በይፋ መቃወማቸውን አል-አላም የዜና አገልግሎት ዘግቦ ነበር፡፡ ወደ ሶሪያ “ለወሲባዊ ጂሃድ” የሚሄዱት ሴቶች “የተታለሉና አእምሯቸው የደነዘዘ” ናቸው በማለት ሼክ ባታኪ ይገልጹዋቸዋል፡፡ ሲቀጥሉም “እንዲያውም በሶሪያ ሊታወጅ የሚገባው ጂሃድ-አክባር (በራስ ላይ የሚታወጅ) ጦርነት” መሆን እንዳለበትና ይህም ራስን ለመቆጣጠር የሚደረግ ጂሃድ በጦርነት ለመፋለም ከመሰለፍ የሚበልጥ “ታላቁ ጂሃድ” እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረገው “ጂሃድ አል-ኒቃ (ወሲባዊ ጂሃድ)” ሴተኛአዳሪነት ወይም ዝሙት እንደሆነ መግለጻቸውን አል-አላም ጨምሮ ዘግቧል፡፡

ታላቁ ሙፍቲ ሼክ ዖትማን ባታኪ (ፎቶ: አለአላም)
ይህንን ገለጻ ከሰጡ በኋላ ታላቁ ሙፍቲ ሼክ ዖትማን ባታኪ በሥልጣናቸው አልዘለቁም፡፡ ከሥልጣን የመነሳታቸውን ጉዳይ ከተናገሩት የተቃውሞ ንግግር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ግን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
በተያያዘ ዜና በዚሁ እጅግ ደም አፋሳሽ በሆነው የሶሪያ ጦርነት ሳዉዲ አረቢያ ከ1,200 በላይ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን እስረኞች አማጺያኑን በመደገፍ የአሳድን አገዛዝ እንዲዋጉ በምስጢር መላኳ ተረጋገጠ፡፡ የሳውዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር ይህንን ስጦታ ማቅረቡን አሜሪካ አገር የሚታተመው USA Today የአሶሪያን ዜና አገልግሎት ጠቅሶ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ “እጅግ ከፍተኛ ምስጢር” በሚል ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር የተጻፈው ማስታወሻ 1,239 የሞት ቅጣት የተበየነባቸው እስረኞች ወደ ሶሪያ ሄደው በምስጢር አማጺያኑን በመደገፍ እንዲዋጉ፤ ለዚህም ይቅርታ እንዲደረግላቸውና በልዋጭ ለቤተሰቦቻቸው ወርሃዊ የገንዘብ ክፍያ እንዲደረግላቸው በዚሁ ማስታወሻ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በሰይፍ እንዲገደሉ” የተወሰነባቸው እነዚህ እስረኞች ነፍስ በማጥፋት፣ አስገድዶ በመድፈር እና አደንዛዥ ዕጽ በማዘዋወር የተወነጀሉ ናቸው፡፡ የሳውዲ ተወላጆች ከሆኑት ወንጀለኞች በተጨማሪ የአፍጋኒስታን፣ የግብጽ፣ የኢራቅ፣ የዮርዳኖስ፣ የኩዌት፣ የፓኪስታን፣ የፍልስጤም፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የሶሪያ እና የየመን ተወላጆች እንደሚገኙበት ተገልጾዋል፡፡
ምስጢራዊውን መረጃው ሳውዲ አረቢያ አስቀድማ የካደች ቢሆንም የዜና ምንጩ የአረቢኛውን ቅጂ ይፋ በማድረጉና የተላኩት እስረኞች በይፋ ከሰጡት ምስክርነት ጋር ተዳምሮ የሳውዲ መንግሥት ጉዳዩን እንዲያምን አድርጎታል፡፡ በወቅቱ ሳውዲ አረቢያ በተመሳሳይ ተግባር ወደፊት እንደማትቀጥል ለሶሪያም ችግር የፖለቲካ መፍትሔ እንደምትፈልግ የሰጠች ቢሆንም ሰሞኑን የወጡ አንዳንድ መረጃዎች የምስጢራዊውን ሰነድ ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ ከተላኩት እስረኞች መካከል 23 የኢራቅ ተወላጆች እና ቁጥራቸው ያልታወቀ የየመን ተወላጆች ግዳጃቸውን ጨርሰውና ከሞት አምልጠው ወደየአገሮቻቸው ተመልሰዋል፡፡ የተቀሩት ያሉበት ሁኔታ እስካሁን አልተገለጸም፡፡
የሜሶፖታሚያ ሥልጣኔ መስራች የሆኑት አሶሪያውያን የሴም ዝርያ ያላቸውና ከአረቦችና አይሁዶች በዘር ፍጹም የተለዩ ናቸው፡፡ አሶሪያውያን ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጀመሪው ሺህ ዓመታት የመካከለኛውን ምስራቅ በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ (ሽፋን ፎቶ: አለ-አላም)

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Thursday, September 26, 2013

ወታደራዊ መኮንኖች የደሞዝ ይጨመርልን ጥያቄ አቀረቡ

ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ካለፉት 8 ቀናት ጀምሮ ስብሰባ ላይ ሲሆኑ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ዋነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ታውቋል።
ከመቶ አለቃ በላይ ማእረግ ያላቸው ወታደራዊ መኮንኖች ስብሰባዎችን እያካሄዱ ያሉት የጄኔራሎች ስብሰባ ከወር በፊት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው። በጄኔራሎቹ ስብሰባ ላይ ለሰራዊቱ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፣ “ሰራዊቱ አሁን የሚያገኘው ደሞዝ ለኑሮው በቂ ነው” የሚል መልስ ከሰራዊቱ ዋና አዛዦች ተሰጥቷል።  በተሰጠው መልስ የተበሳጩት  ጄኔራል ሰአረ መኮንን ስብሰባ ረግጠው ወጥተው እንደነበር ታውቋል። ጄኔራሉን ለማረጋጋት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ እንደነበርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ጄኔራል ሰአረ ለሰራዊቱ ደሞዝ እንዲጨመር አቋም ከያዙት ከፍተኛ መኮንኖች መካከል አንዱ ናቸው።
ሰሞኑን በመካሄድ ላይ ባለው ከጄኔራል በታች ማእረግ ባላቸው መኮንኖች ስብሰባም   የደሞዝ ጭማሪና የኑሮ ውድነት ዋና አጅንዳ ሆኖ ቀርቧል።
በምስራቅ አካባቢ ባለው እዝ አንዳንድ መኮንኖች ” እኛ ቤተሰቦቻችንን ምግብ አብልተን ለማኖር አልቻልንም፣ እናንተ በሙስና በዘረፋችሁት ገንዘብ ልጆቻችሁን ውጭ አገር ልካችሁ ታስተምራላችሁ” በሚል አለቆቻቸውን በድፍረት መተቸታቸውን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።   መኮንኖች ያቀረቡትን ጥያቄ የመደረክ መሪዎች ለመመለስ ሲቸገሩ ታይቷል።
መኮንኖቹ ስብሰባቸውን ሲጨርሱ ከተራ ወታደሮች ጋር የሚደረገው ስብሰባ ይቀጥላል ተብሎአል።
ከፍተኛ ቅሬታ እየተስተናገደበት ባለው ስብሰባ፣ ወታደሮቹ እንደ መኮንኖቹ ሁሉ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ወታደራዊ ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ሻምበል የወለደውን ልጅ በእሳት ማቃጠሉ ታውቋል። በምስራቅ እዝ የሚገኘው ሻምበል ፈቃዱ በዳዳ ከሳምንታት በፊት በልጁ ላይ ቤንዜን በማርከፍከፍ ያቃጠለው ሲሆን፣ ልጁም ወዲያውኑ ህይወቱ ሲያልፍ አባቱ ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል ተኝቷል። ሻምበል ፈቃዱ በልጁ ላይ ይህን አሰቃቂ እርምጃ ለምን እንደወሰደ አልታወቀም።

https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/09/25/36/

Wednesday, September 25, 2013

ጤናማ አጥንትና ጥርሶች፤ ቆዳችን ለስላሳ፣በቀላሉ መተጣጠፍ የሚያስችል፤ ለዓይን ማራኪም፤ በኋለኛው የዕድሜ ዘመን ከሚከሰት የአጥንት መሳሳት ችግር ሊታደገን ይችላል።


Milkሰውነትን ይገነባሉ በእዚያውም ያጠነክራሉ ከሚባሉ የምግብ ዓይነቶች ይመደባል-ወተት። በተለይ ለሕፃናት ዕድገትና ለአጥንት ጥንካሬ የጎላ ጠቀሜታ አለው የሚለው እሳቤ ሳይንሳዊ ድጋፍ ስላለው ሕፃናት ወደእዚህች ዓለም ከመጡባት ቅጽበት የጀምሮ የሚሰጣቸው ወተት ነው።
ምንም እንኳ ወተት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም ዕድሜያችን እያደገ በመጣ ቁጥር አጠቃቀማችንን እየቀነስን እንመጣለን። በተለይም በሀገራችን በዕለት ተዕለት ምግባችን ውስጥ አካትተን የመጠቀም ሁኔታ የተለ መደ አይደለም። ይህ የሆነበት የተለያዩ ምክን ያቶች አሉት።
የመጀመሪያው ጉዳይ አስተሳሰባችን ነው። አብ ዛኛው ሰው ወተትን የል ጅነት ጊዜ ምግብ አድርጎ ስለሚቆጥረው ትኩረት አይሰጠ ውም። አንዳንዶች ወተትን አብዝተን በመውሰ ዳችን በሰውነታችን ውስጥ ከተገቢው በላይ የቅባት ክምችት ይፈጥራል በሚል ስጋት የወተት አጠቃ ቀማቸውን ይቀንሳሉ። የዋጋው በየጊዜው እየጨ መረ በመምጣትም እንዲሁ አዘውትረን እንዳን ጠቀም ከሚያደርጉን ምክን ያቶች አንዱ ነው። ንጹህ ወተት በገበያው ላይ እንደልብ አለ ማግኘት እንዲሁ።
ይሁን እንጂ ወተት ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ ቫይታሚኖችና አልሚ ምግቦች ከመያዙ በተጨማሪ የሰውነታችንን ጤንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው አዘውትረን እንድ ንወስደው ይመከራል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ወተት ለሰውነታችን ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች አንዱ ለስላሳና የተፍታታ ቆዳ እንዲኖረን ማድረግ ነው። በዕለት ተዕለት ምግባችን ውስጥ ወተት የምንወስድ ከሆነ ቆዳችን ለስላሳ፣ ልልና በቀላሉ መተጣጠፍ የሚችል ይሆናል። ለዓይን ማራኪም ይሆናል።
በወተት ውስጥ የሚገኘው ላክቲክ አሲድ ቆዳን ለማለስለስ በዋናነት ይጠቅማል። ቆዳ ደረቅ እንዳይሆንና እርጥበቱን እንደጠበቀ እንዲቆይ የሚያደርገው ደግሞ በወተት ውስጥ የሚገኘው አሚኖ አሲድ ነው። ወተት ፀረ መርዛማ ነገሮችን በውስጡ በመያዙም በአካባቢ በሚገኙ መርዛማ ነገሮች አማካኝነት በሰውነት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ያስችላል።

ጤናማ አጥንትና ጥርሶች እንዲኖሩን በማድረግ ረገድም ወተት የላቀ ሚና አለው። አጥንታችን ጤናማና ጠንካራ እንዲሆን ከሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች መካከል ካልሲየም አንዱና ቀዳሚው ነው። ይህ ንጥረ ነገር ደግሞ በወተት ውስጥ በከፍተኛ መጠን ይገኛል።
በወተት ውስጥ የሚኖረው ካልሲየም ለታዳጊ ሕፃናት ለአጥንታቸው ዕድገትና ልምላሜ የጎላ ፋይዳ አለው። በሂደት ዕድሜ እየገፋ ሲመጣ ደግሞ አጥንትን ሊያሳሳና ሊያዛባ የሚችለው «ኦስቲዮፖሮሲስ» የተባለ በሽታን በመከላከል በኩልም ጠቀሜታ አለው። ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች ከካልሲየም በተጨማሪ ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆኑ እንደ ፎስፈረስ፣ ማግኒዚየምና ፕሮቲን ያሉ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ። እነዚህ ለጤናማ የአጥንት ዕድገትና ጥንካሬ ጠቀሜታ አላቸው። ወተትን ከልጅነት ጀምረን በሕይወት ዘመናችን አዘውትረን መውሰድ በኋለኛው የዕድሜ ዘመን (ቆይቶ ከሚከሰት የአጥንት መሳሳት ችግር) ሊታደገን ይችላል።
በወተት ውስጥ የሚገኙት ካልሲየምና ፎስፈረስ የተባሉ ነጥረ ነገሮች ጠንካራ ጥርሶች እንዲኖሩን ከማድረግ በተጨማሪ የጥርስ መበላሸትና መቦርቦርን ይከላከላሉ። ሰውነታችን የቫይታሚን «ዲ» እጥረት በሚገጥመው ጊዜም በየዕለቱ በምንወስደው ወተት ውስጥ የሚኖረው ካልሲየም ሰውነታችን ቫይታሚን «ዲ»ን በአማራጭነት እንዲያገኝ ይረዳዋል።
የሰውነት የተለያዩ ጡንቻዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ በኩልም ወተት የራሱ ጠቀሜታ እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ። ወተት ውስጥ የሚገኝ ፕሮቲን የተባለው ንጥረ ነገር የሰውነት ጡንቻዎችን በመገንባት ረገድ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል። ይህም በመሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከተደረገ በኋላ ጡንቻ በሚደክምበት ወቅት ወተትን መውሰድ ይመከራል። ምክንያቱም ወተት በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወቅት የዛለውን ጡንቻ ወደነበረበት ለመመለስ ያስችላልና። በእንቅስቃሴ ወቅት በትነት የወጣውን ፈሳሽ በመተካት ረገድም ወተት ጠቀሜታ ስላለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከተደረገ በኋላ ቢወሰድ መልካም ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ።
ውፍረትን በተለይ በሆድ አካባቢ የሚከሰት ውፍረትን ለመቀነስ ወተት ጠቀሜታ እንዳለውም ይነገራል። በወተት ጠቀሜታ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ አነስተኛ የቅባት መጠን ያለው ወተት ወይም ቅባቱ የወጣለትን ወተት የሚጠቀሙ ሴቶች ምንም ወተት ከማይወስዱት ሴቶች ኪሎአቸውን በተሻለ ሁኔታ ሊቀንሱ ይችላሉ።
ወተት የምግብ ፍላጎትን ከማሻሻሉ በላይ እንደ ቁርስ ማቆያ ተደርጎ ስለሚታይ ባለሙያዎች ከምግብ ገበታ ላይ እንዳይጠፋ ይመክራሉ። አትክልት በሚመገቡበት ወቅት አብረው ሊወስዱት እንደሚችሉም ይገልጻሉ። ቀኑን ሙሉ ሥራ ላይ የዋለ ሰው ወደ ማታ ላይ የፈላ ወተት ፉት ቢል በሥራ ምክንያት ተዳክሞ የነበረውን ሰውነቱን ዘና ለማድረግም ይረዳል።
ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳይከሰትና ለስትሮክ ሕመም የመጋለጥ ዕድልንም ይቀንሳል። በሰውነት ውስጥ ጉበት የሚያመርተውን የኮሊስትሮል መጠን በመቀነስ ረገድም የጎላ ፋይዳ አለው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በወተት ውስጥ የሚገኙት ቫይታሚን ኤ እና ቢ ጥሩና ጤናማ የዓይን እይታ እንዲኖረን በማድረግ ረገድም ጠቀሜታ አላቸው። ለተለያዩ የካንሰር ሕመሞች የመጋለጥ ዕድልን ለመቀነስም እንዲሁ።
የተለያዩ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት በዕለት ተዕለት ምግባችን ሦስት እጅ ወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ አምስት እጁን አትከልትና ፍራፍሬ ማድረግ እንዲሁም የጨው መጠንን መቀነስ በአዋቂነትም ሆነ በሕፃንነት ዕድሜ ሊከሰት የሚችልን ከፍተኛ የደም ግፊት ሊቀንስ ይችላል።
እነዚህ ጥናቶች አክለው እንደሚያመለክቱት ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች ለልብና ልብ ነክ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ይቀንሳሉ። በቅርቡ በእንግሊዝ ዌልስሜን የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ወተትን አዘውትረው የሚወስዱ ሰዎች ምንም ከማይወስዱትና አልፎ አልፎ ከሚወስዱት ጋር ሲነጻጸሩ ለልብ ድካም በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው በእጅጉ ይቀንሳል።
እንደጥናቶቹ ከሆነ ከፍተኛ የካልሲየም ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ መኖር በደም ውስጥ ጥሩ የማይባሉ ቅባቶች (ለሕመም የሚዳርጉ ቅባቶች ወይም የኮሌስትሮል ዓይነቶች) እንዲቀንሱ ሊያደርግ ይችላል። በአንጻሩ ጥሩ የሚባሉትን የኮሌስትሮል ዓይነቶች መጠን ሊያሳድግ ይችላል። ይህ ተግባሩ ነው ለልብ ሕመም የመጋለጥ ዕድልን ሊቀንስ ያስችላል የሚያስብለው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አነስተኛ የቅባት መጠን ያላቸውን የወተት ተዋጽኦዎች አዘውትሮ መመገብ ታይፕ «ቱ» በመባል የሚታወቀውን የስኳር ሕመምን ለመከላከል ያስችላል። ሕመሙ በሕፃንነትና በጎልማሳነት ዕድሜ የሚከሰት ሲሆን ፤ብዙጊዜም ሕክምናው የዕድሜ ልክ ነው። በቅርብ ጊዜ በመካከለኛ የዕድሜ ክልል በሚገኙ 37 ሺ ሴቶች ላይ በተካሄደ ጥናት ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን የወሰዱ ሴቶች ለታይፕ «ቱ» የስኳር ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው ቀንሶ ታይቷል። እ.ኤ.አ በ2005 በወንዶች ላይ ተካሂዶ የነበረ ተመሳሳይ ጥናትም አነስተኛ የቅባት መጠን ያላቸው የወተት ተዋጽኦዎችን መውሰድ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል ሲቀንስ መታየቱ ተረጋግጧል።
በገበያ ላይ በተለያየ መልክ የተቀነባበሩ የወተት ዓይነቶች አሉና ከላይ የተዘረዘሩትን የወተት ጠቀሜታዎች ለማግኘት የትኛው ይሻላል? የሚለውን መመለስና መምረጥ የግለሰቡ ጉዳይ ቢሆንም ባለሙያዎች ግን የቅባት መጠን ያልበዛበት ተፈጥሮአዊ የሆነውን እንዲሁም ከተጠቃሚው ምግብ ጋር የሚስማማውን ወተት እንዲጠቀሙ ይመክ ራሉ።
 http://selamlehulum.blogspot.com/2013/09/blog-post_9911.html?spref=fb

አምፖልና ኩራዝ


ኩራዝ ከጓሮ ማድቤት ተወሽቃ ትኖር ነበር፡፡ ለብዙ ዘመናት፡፡ ድንገት ሳሎን የምግብ ጠረጲዛ ላይ ታየች፡፡ ይህ ነገር ኮርኒስ ላይ የተንጠለጠለችውን አምፖል በእጅጉ አስገረማት፡፡
‹‹ኩራዝ፣ ዛሬ ከየት ከየት ተገኘሽ፡፡ እኔኮ እንደ ዳይኖሰር ዝርያሽ የጠፋ መስሎኝ ነበር›› አለች አምፖል እየተወዛወዘች፡፡
‹‹እናንተ የተጋደመ አታስተኙ፣ የተቀበረ አታስሞቱ›› አለቻት ኩራዝ ብል ብል እያለች፡፡ በዙሪያዋ የቤቱ ባለቤቶች ከብበው እራት ይበላሉ፡፡ ከተመጋቢዎቹ አንዱ ጭል ጭል በምትለው የኩራዟ ብርሃን በእንጀራው መሐል ያለውን ወጥ ፍለጋ ጠጋ ብሎ እያየ እንዲህ አለ፡-
‹‹ዛሬ ፌስ ቡክ ላይ ያየሁትን ግጥም ልንገራችሁ››
‹‹ምን ተባለ ደግሞ፡፡ ድሮ እረኛ ምን አለ? ነበር የሚባለው፡፡ ዛሬማ ፌስ ቡክ ምን አለ ሆነኮ፡፡›› አለችው የአባ ወራው ሚስት ወጡን ያገኘው ዘንድ ኩራዙን እያስጠጋችለት፡፡

‹‹እራትና መብራት ይባል ነበር ድሮ
እራቱም መብራቱም የት አለ ዘንድሮ›› አጨበጨበችለት፡፡ አምፖሏም ግርምቷን ይበልጥ በመወዛወዝ ገለጠችው፡፡ ኩራዝም ለመጎረር አስባ ትንሽ ኃይል ጨመረች፡፡ የሰውየውን ግጥም አጣጥማ ስትመለስም አምፖሏ ‹‹የጀመርሽውንኮ አልጨረስሽልኝም፡፡ የተጋደመ አታስተኙ፣ የተቀበረ አታስሞቱ ለምን አልሽን ›› አለቻት፡፡
‹‹እንዴ አዲስ አበባ ከተማ ላይ መብራት ከገባኮ መቶ ዓመት አለፈው፡፡ እኔ፣ ጧፍና ሻማ በቃን ብለን ጡረታ ወጥተን ነበር፡፡ ሻማና ጧፍም እንግዲህ ሲያረጁ ወደበተስኪያን ነው ብለው መንኩሰው በተስኪያን ገብተው ነበር፡፡ እኔም ባይሆን ስሜ እንኳን ለታሪክ ይቀመጥ ብል ስሜን ቀየራችሁት፡፡ ስሜ ከጠፋ እኔም ተረስቻለሁ ብዬ ሞቼ ነበር፡፡ እድሜ ለመብራት ኃይል እኔን ከተቀበርኩበት መቃብር፣ ሻማና ጧፍን ከመነኮሱበት ገዳም አመጣን፡፡ መቼም እናንተ ያለውን ከማክበር ይልቅ የሞተውን መቀስቀስ ትወዳላችሁ፡፡ ቆይ ግን አንቺና ፍሬቻ ልዩነታችሁ ምንድን ነው?››
‹‹ምን ልዩነት አለን፡፡ እርሱ መኪና ላይ እኔ ኮርኒስ ላይ ከመሆናችን በቀር፡፡ ያው ሁለታችንም ቦግ እልም ነው የምንለው፡፡ ሳንጠፋ ማብራት አይሆንልንም፡፡ ድሮ እኔ ሳቀው ቦግ እልም ብልጭ ድርግም የሚሉ ሦስት ነገሮች ብቻ ነበሩ››
‹‹ምን ምን ናቸው?››
‹‹አንድ መብረቅና፤ ከነ ድምጡ ብልጭ ብሎ ድርግም ይላል፡፡ ሁለት የገና መብራት፣ የገና ዛፍ ላይ ተጠብልሎ ቦግ እልም ይላል፡፡ ሦስት የዳንስ ቤት መብራት፣ ከሙዚቃ ጋር ተዋሕዶ በሙዚቃው ድምጥ ቦግ እልም ይላል፡፡ አሁን አሁንማ ወይ እንደ መብረቅ ነጎድጓድ የለኝ፣ ወይ እንደ ገና መብራት ዛፍ ላይ አልተንጠለጠልኩ፣ ወይ እንደ ዳንስ ቤት ሙዚቃ የለኝ እንዴው ብቻዬን ቦግ እልም ስል አመሻለሁ፡፡ አገልግሎቴኮ የሰዓት መቁጠሪያ ሆነ፡፡ መጀመሪያ መብራት የጠፋ ጊዜ፣ ሁለተኛ የጠፋ ጊዜ እየተባለ ሰዓት ይቆጠርብኛል፡፡ እንዴው ግን በናንተ ዘመን ሄደ መጣየሚባል ነገር ነበር እንዴ?››
‹‹ነበረ እንጂ›› አለች ኩራዝ፡፡ ‹‹ነጋዴ ሄደ መጣ፣ ወታደር ሄደ መጣ፣ እድሜ ሄደ፣ መሬት ሄደ መጣ፡፡ ስንት የሄደና የመጣ ነገር አለ፡፡››
‹‹መብራትስ ይሄድ ነበር››
‹‹መብራት መጣ፣ መብራት ሄደ አሁን እናንተ ስትሉ ነው የምሰማው፡፡ የመሠረተ ትምህርት ማስተማሪያ ላይ እንኳን አበበ ሄደ፣ ከበደ መጣ የሚል እንጂ መብራት ሄደ መብራት መጣ የሚል አላየሁም፡፡ እኛኮ በቅብዐ ኑግም ብትይ፣ በጥጥ ዘይትም ብትይ፣ በጉሎ ዘይትም ብትይ እንሠራ ነበር፡፡ ከባሰ ደግሞ ጤፍ የምታስለቅም ጨረቃ ትወጣለች፡፡ ያለበለዚያ ምድጃ ከብበሽ እሳት ዳር መብላት መጠጣት ነው፡፡ የእናንተኮ የሚገርም ነው፡፡ ዘይት መሥራቱን ኋላ ቀርነት ብላችሁ ተዋችሁት፡፡ ምድጃ ዳር እንዳትቀመጡ ሳሎናችን ለቴሌቭዥንና ለሶፋ ብቻ ነው አላችሁ፡፡ ከሁለቱም ያጣችሁ ሆናችሁኮ፡፡ እንደ ዘንድሮ ነጋዴኮ መከራ ያየ የለም፡፡ ገቢዎች፣ ጉምሩክ፣ ንግድ ቢሮ፣ ቀበሌ፣ ክፍለ ከተማ ማስታወቂያ ያወጣሉ፡፡ በቴሌቭዥንና በሬዲዮ ያስነግራሉ፡፡ ገና ማስታወቂያው ሲጀምር መብራቱ እልም፡፡ ተመዝገቡ ይባል፣ ክፈሉ ይባል፣ ተሰለፉ ይባል፣ ወረፋ ያዙ ይባል፣ ጥፉ ይባል፣ ሽሹ ይባል በምን ይታወቃል፡፡ ከዚያ ትቀጫለሽ ትባያለሽ›› ‹‹ምነው›› ያልሽ እንደሆነ ማስታወቂያ በቴሌቭዥንና በሬዲዮ ነግረን ነበር ይሉሻል፡፡ እነርሱ መናገራቸውን እንጂ እኛ አለመስማታችንን አያዩ፡፡ ቴሌቭዥንና ሬዲዮኮ ለራሳቸው እንጂ ለሁላችን የሚሆን ጀነሬተር የላቸውም፡፡ የስንቱ ሞያ ተበላሸ በእናንተ ምክንያት፡፡ ግማሽ በስሎ ግማሽ ሳይበስል የሚወጣ እንጀራ ምን እንደሚባል ታውቂያለሽ?››
አምፖል መልሱን ለመስማት ጓጉታ ‹‹አላውቅም›› አለች
‹‹የመብራት ኃይል እንጀራ›› ይባላል፡፡
አምፖል በሳቅ ስትፈርስ በውስጧ የነበሩት ቀጫጭን ሽቦዎች ረገፉ፡፡ ደነገጠች፡፡
‹‹አንቺ ሳልቃጠል አልቀርም›› አለቻት ኩራዝን፡፡
‹‹ምን የተቃጠለውም ያልተቃጠለውም አምፖል አንድ ነው፡፡ ሁለታችሁም አትበሩም፡፡ አይዞሽ ማንም አያውቅሽም፡፡ እዚህ ሀገር እንደሆነ የሚሠራው ከማይሠራው ጋር አብሮ ነው የሚኖረው››
‹‹እንዴት እንዴት››
‹‹ለምሳሌ መብራት ኃይል ሲባል ሰምተሻል? ኃይል አለ መብራት የለም፡፡ ኔት ወርክ ሲባል ሰምተሻል? ‹ኔት› አለ ‹ወርክ› ግን የለም፡፡ ቴሌ ኮሙኒኬሽን ሲባል ሰምተሻል? ‹ቴሌ› አለ ‹ኮሙኒኬሽን› ግን የለም፡፡ የሃይማኖት ተቋም ሲባል ሰምተሻል? ‹ሃይማኖት› አለ ‹ተቋም› ግን የለም፡፡ ስፖርት ፌዴሬሽኖችን አልሰማሽም? ‹ስፖርት› የለም ‹ፌዴሬሽን› ግን አለ፡፡ የደንበኛ አገልግሎት ሲባልስ? ‹ደንበኛ› አለ፤ ‹አገልግሎት› ግን የለም፡፡ ነጻ ፕሬስ ሲባልስ? ‹ፕሬስ› አለ ‹ነጻ› ግን የለም፡፡ የርዳታ ድርጅት ሲባልስ? ‹ድርጅት› አለ ‹ርዳታ› ግን የለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲባሉስ አልሰማሽም? ‹ፓርቲ› አለ ‹ፖለቲካ› ግን የለም፡፡ ነጻ ገበያስ አታውቂም? ‹ገበያ› አለ ‹ነጻ› ግን የለም፡፡ ዴሞክራሲ ሲባልስ አልሰማሽም? ‹ዴሞ(ሕዝብ)› አለ፣‹ክራሲ(አስተዳደር)› ግን የለም፡፡ በየቢሮው በኮምፒውተር ሲስተም መሥራት ጀምረናል ሲሉ አትሰሚም አዎ ኮምፒውተር በየቢሮው አለ ‹ሲስተም›› ግን የለም፡፡ እንዲህ እያልሽ መቀጠል ነው፡፡››
‹‹ መቃጠሌን ያወቁብኝ እንደሆነ ግን ከዚህ ቦታ መውረዴ ነው››
‹‹ተይ እባክሽ እዚህ ሀገር አንቺ ብቻ ነሽ እንዴ ስትቃጠይ የምትወርጅው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየፓርቲው፣ በየእምነት ተቋሙ፣ በየግል ድርጅቱ ስንት የተቃጠለ አምፖል አለ አይደለም እንዴ፡፡ ማን አወረደው፡፡ መብራት ስለሌለ ማንም ሳይለየው የሚሠራ  አምፖል መስሎ ይኖራል፡፡ አየሽ ጨለማ ለአጭበርባሪ ይመቻል፡፡ በብርሃን ግን ሁሉ ይገለጣል፡፡ እንዲህ ጨለማ የምንሆነው ኤሌክትሪክ በሀገር ጠፍቶ መሰለሽ?››
‹‹ታድያ ለምንድን ነው?››
‹‹ብርሃን ለማጭበርበር ስለማያመች ነው፡፡ ብርሃን ከመጣ የሚወልቁ ብዙ የተቃጠሉ አምፖሎች አሉ፡፡ ተቃጥሎ ቦታን ላለመልቀቅ ዋናው መፍትሔ ጨለማ ነው፡፡›› ኩራዝ ይህንን ስትል የቤቱ አባወራ መጣና ‹እፍ› ብሎ አጠፋት፡፡
‹‹በይ ደኅ እደሪ፣ እፍ ብለው ያበሩናል እፍ ብለው ያጠፉናል›› አለችና ቆርቆሮዋ ውስጥ ገብታ ተኛች፡፡  
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው
 http://www.danielkibret.com/