-ከጋና ወይም ከካሜሮን ጋር ለአቋም መለኪያ ይጫወታሉ
ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ የሚወከሉትን አምስት ቡድኖች ለመለየት አሥሩ ቡድኖች የሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
የናይጄሪያ አቻውን የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንት መስከረም 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ተሰባስቦ ዝግጅት ጀምሯል፡፡
አራቱን ፕሮፌሽናሎች ጨምሮ በአጠቃላይ 28 ተጫዋቾችን ለዝግጅት
የጠራው ብሔራዊ ቡድን፣ ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ናይጄሪያን ከመግጠሙ አስቀድሞ
መስከረም 19 ወይም 26 ቀን ከጋና ወይም ከካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ፌዴሬሽኑና
ዋናው አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡
የብሔራዊ ቡድን ምክትል አሠልጣኝ አቶ ዳኜ አሰፋ ዋናው አሠልጣኝ
ያገኟቸው የጋናና የካሜሮን አሠልጣኞች የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ግን ዋሊያዎቹ ከናይጄሪያ ጋር የሚያደርጉት ዋናው ጨዋታ ከቀረው ጊዜ አኳያ ከሁለቱ ቡድኖች ከአንዳቸው ጋር
መስከረም 19 አልያም 26 ቀን ቀድሞ እሺ ካለው ጋር አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ አሠልጣኙና ፌዴሬሽኑ
ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል አሠልጣኙ ማብራሪያ፣ በውጭ በተለያዩ አገሮች ከሚገኙትና
ከቅዱስ ጊዮርጊስ በስተቀር ቀሪዎቹ ተጫዋቾች በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ተሰባስበው ዝግጅት ጀምረዋል፡፡
ፕሮፌሽናሎቹ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በቅርቡ መጥተው ከብሔራዊ ቡድኑ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል፡፡
ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተመረጡትን በተመለከተ ደግሞ፣ ቡድኑ ለአፍሪካ
ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከቱኒዚያው ኤትዋል ዴ ሳህል ጋር በአዲሰ አበባ ስታዲየም መስከረም 12 ቀን 2006
ዓ.ም. ጨዋታውን ካጠናቀቀ በኋላ ተጫዋቾቹ ማታውኑ ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግም ምክትል አሠልጣኙ
ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ለአፍሪካ ኮንፌዴሽን ዋንጫ ከስምንቱ ቡድኖች አንዱ
የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ሳምንት በፊት ከሜዳው ውጪ ከማሊው ስታደ ማሊ ጋር ባደረገው ጨዋታ 1ለ0 ተሸንፎ
በመመለሱ ምክንያት ከፉክክሩ ውጪ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ በአዲሰ አበባ ስታዲየም ከኤትዋል ዴ ሳህል ጋር
የሚያደርገው ግጥሚያ ክብሩን ከማስጠበቅ በዘለለ አሸነፈም፤ ተሸነፈም በውጤቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለም
ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ክለቡ በኮንፌዴሬሽኑ ዋንጫ ከስምንቱ ውስጥ በመግባቱ 150 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር የሚያገኝ
ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑም አሥር ሺሕ ዶላር እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡
No comments:
Post a Comment