ኩራዝ ከጓሮ ማድቤት ተወሽቃ
ትኖር ነበር፡፡ ለብዙ ዘመናት፡፡ ድንገት ሳሎን የምግብ ጠረጲዛ ላይ ታየች፡፡ ይህ ነገር ኮርኒስ ላይ የተንጠለጠለችውን አምፖል
በእጅጉ አስገረማት፡፡
‹‹ኩራዝ፣ ዛሬ ከየት ከየት
ተገኘሽ፡፡ እኔኮ እንደ ዳይኖሰር ዝርያሽ የጠፋ መስሎኝ ነበር›› አለች አምፖል እየተወዛወዘች፡፡
‹‹እናንተ የተጋደመ አታስተኙ፣
የተቀበረ አታስሞቱ›› አለቻት ኩራዝ ብል ብል እያለች፡፡ በዙሪያዋ የቤቱ ባለቤቶች ከብበው እራት ይበላሉ፡፡ ከተመጋቢዎቹ አንዱ
ጭል ጭል በምትለው የኩራዟ ብርሃን በእንጀራው መሐል ያለውን ወጥ ፍለጋ ጠጋ ብሎ እያየ እንዲህ አለ፡-
‹‹ዛሬ ፌስ ቡክ ላይ ያየሁትን
ግጥም ልንገራችሁ››
‹‹ምን ተባለ ደግሞ፡፡ ድሮ
እረኛ ምን አለ? ነበር የሚባለው፡፡ ዛሬማ ፌስ ቡክ ምን አለ ሆነኮ፡፡›› አለችው የአባ ወራው ሚስት ወጡን ያገኘው ዘንድ
ኩራዙን እያስጠጋችለት፡፡
‹‹እራትና መብራት ይባል ነበር
ድሮ
እራቱም መብራቱም የት አለ
ዘንድሮ›› አጨበጨበችለት፡፡ አምፖሏም ግርምቷን ይበልጥ በመወዛወዝ ገለጠችው፡፡ ኩራዝም ለመጎረር አስባ ትንሽ ኃይል ጨመረች፡፡
የሰውየውን ግጥም አጣጥማ ስትመለስም አምፖሏ ‹‹የጀመርሽውንኮ አልጨረስሽልኝም፡፡ የተጋደመ አታስተኙ፣ የተቀበረ አታስሞቱ ለምን
አልሽን ›› አለቻት፡፡
‹‹እንዴ አዲስ አበባ ከተማ
ላይ መብራት ከገባኮ መቶ ዓመት አለፈው፡፡ እኔ፣ ጧፍና ሻማ በቃን ብለን ጡረታ ወጥተን ነበር፡፡ ሻማና ጧፍም እንግዲህ ሲያረጁ
ወደበተስኪያን ነው ብለው መንኩሰው በተስኪያን ገብተው ነበር፡፡ እኔም ባይሆን ስሜ እንኳን ለታሪክ ይቀመጥ ብል ስሜን
ቀየራችሁት፡፡ ስሜ ከጠፋ እኔም ተረስቻለሁ ብዬ ሞቼ ነበር፡፡ እድሜ ለመብራት ኃይል እኔን ከተቀበርኩበት መቃብር፣ ሻማና ጧፍን
ከመነኮሱበት ገዳም አመጣን፡፡ መቼም እናንተ ያለውን ከማክበር ይልቅ የሞተውን መቀስቀስ ትወዳላችሁ፡፡ ቆይ ግን አንቺና ፍሬቻ
ልዩነታችሁ ምንድን ነው?››
‹‹ምን ልዩነት አለን፡፡ እርሱ
መኪና ላይ እኔ ኮርኒስ ላይ ከመሆናችን በቀር፡፡ ያው ሁለታችንም ቦግ እልም ነው የምንለው፡፡ ሳንጠፋ ማብራት አይሆንልንም፡፡
ድሮ እኔ ሳቀው ቦግ እልም ብልጭ ድርግም የሚሉ ሦስት ነገሮች ብቻ ነበሩ››
‹‹ምን ምን ናቸው?››
‹‹አንድ መብረቅና፤ ከነ ድምጡ
ብልጭ ብሎ ድርግም ይላል፡፡ ሁለት የገና መብራት፣ የገና ዛፍ ላይ ተጠብልሎ ቦግ እልም ይላል፡፡ ሦስት የዳንስ ቤት መብራት፣
ከሙዚቃ ጋር ተዋሕዶ በሙዚቃው ድምጥ ቦግ እልም ይላል፡፡ አሁን አሁንማ ወይ እንደ መብረቅ ነጎድጓድ የለኝ፣ ወይ እንደ ገና
መብራት ዛፍ ላይ አልተንጠለጠልኩ፣ ወይ እንደ ዳንስ ቤት ሙዚቃ የለኝ እንዴው ብቻዬን ቦግ እልም ስል አመሻለሁ፡፡ አገልግሎቴኮ
የሰዓት መቁጠሪያ ሆነ፡፡ መጀመሪያ መብራት የጠፋ ጊዜ፣ ሁለተኛ የጠፋ ጊዜ እየተባለ ሰዓት ይቆጠርብኛል፡፡ እንዴው ግን በናንተ
ዘመን ሄደ መጣየሚባል ነገር ነበር እንዴ?››
‹‹ነበረ እንጂ›› አለች
ኩራዝ፡፡ ‹‹ነጋዴ ሄደ መጣ፣ ወታደር ሄደ መጣ፣ እድሜ ሄደ፣ መሬት ሄደ መጣ፡፡ ስንት የሄደና የመጣ ነገር አለ፡፡››
‹‹መብራትስ ይሄድ ነበር››
‹‹መብራት መጣ፣ መብራት ሄደ
አሁን እናንተ ስትሉ ነው የምሰማው፡፡ የመሠረተ ትምህርት ማስተማሪያ ላይ እንኳን አበበ ሄደ፣ ከበደ መጣ የሚል እንጂ መብራት
ሄደ መብራት መጣ የሚል አላየሁም፡፡ እኛኮ በቅብዐ ኑግም ብትይ፣ በጥጥ ዘይትም ብትይ፣ በጉሎ ዘይትም ብትይ እንሠራ ነበር፡፡
ከባሰ ደግሞ ጤፍ የምታስለቅም ጨረቃ ትወጣለች፡፡ ያለበለዚያ ምድጃ ከብበሽ እሳት ዳር መብላት መጠጣት ነው፡፡ የእናንተኮ
የሚገርም ነው፡፡ ዘይት መሥራቱን ኋላ ቀርነት ብላችሁ ተዋችሁት፡፡ ምድጃ ዳር እንዳትቀመጡ ሳሎናችን ለቴሌቭዥንና ለሶፋ ብቻ
ነው አላችሁ፡፡ ከሁለቱም ያጣችሁ ሆናችሁኮ፡፡ እንደ ዘንድሮ ነጋዴኮ መከራ ያየ የለም፡፡ ገቢዎች፣ ጉምሩክ፣ ንግድ ቢሮ፣
ቀበሌ፣ ክፍለ ከተማ ማስታወቂያ ያወጣሉ፡፡ በቴሌቭዥንና በሬዲዮ ያስነግራሉ፡፡ ገና ማስታወቂያው ሲጀምር መብራቱ እልም፡፡
ተመዝገቡ ይባል፣ ክፈሉ ይባል፣ ተሰለፉ ይባል፣ ወረፋ ያዙ ይባል፣ ጥፉ ይባል፣ ሽሹ ይባል በምን ይታወቃል፡፡ ከዚያ ትቀጫለሽ
ትባያለሽ›› ‹‹ምነው›› ያልሽ እንደሆነ ማስታወቂያ በቴሌቭዥንና በሬዲዮ ነግረን ነበር ይሉሻል፡፡ እነርሱ መናገራቸውን እንጂ
እኛ አለመስማታችንን አያዩ፡፡ ቴሌቭዥንና ሬዲዮኮ ለራሳቸው እንጂ ለሁላችን የሚሆን ጀነሬተር የላቸውም፡፡ የስንቱ ሞያ ተበላሸ
በእናንተ ምክንያት፡፡ ግማሽ በስሎ ግማሽ ሳይበስል የሚወጣ እንጀራ ምን እንደሚባል ታውቂያለሽ?››
አምፖል መልሱን ለመስማት ጓጉታ
‹‹አላውቅም›› አለች
‹‹የመብራት ኃይል እንጀራ››
ይባላል፡፡
አምፖል በሳቅ ስትፈርስ በውስጧ
የነበሩት ቀጫጭን ሽቦዎች ረገፉ፡፡ ደነገጠች፡፡
‹‹አንቺ ሳልቃጠል አልቀርም››
አለቻት ኩራዝን፡፡
‹‹ምን የተቃጠለውም
ያልተቃጠለውም አምፖል አንድ ነው፡፡ ሁለታችሁም አትበሩም፡፡ አይዞሽ ማንም አያውቅሽም፡፡ እዚህ ሀገር እንደሆነ የሚሠራው
ከማይሠራው ጋር አብሮ ነው የሚኖረው››
‹‹እንዴት እንዴት››
‹‹ለምሳሌ መብራት ኃይል ሲባል
ሰምተሻል? ኃይል አለ መብራት የለም፡፡ ኔት ወርክ ሲባል ሰምተሻል? ‹ኔት› አለ ‹ወርክ› ግን የለም፡፡ ቴሌ ኮሙኒኬሽን ሲባል
ሰምተሻል? ‹ቴሌ› አለ ‹ኮሙኒኬሽን› ግን የለም፡፡ የሃይማኖት ተቋም ሲባል ሰምተሻል? ‹ሃይማኖት› አለ ‹ተቋም› ግን
የለም፡፡ ስፖርት ፌዴሬሽኖችን አልሰማሽም? ‹ስፖርት› የለም ‹ፌዴሬሽን› ግን አለ፡፡ የደንበኛ አገልግሎት ሲባልስ? ‹ደንበኛ›
አለ፤ ‹አገልግሎት› ግን የለም፡፡ ነጻ ፕሬስ ሲባልስ? ‹ፕሬስ› አለ ‹ነጻ› ግን የለም፡፡ የርዳታ ድርጅት ሲባልስ? ‹ድርጅት›
አለ ‹ርዳታ› ግን የለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲባሉስ አልሰማሽም? ‹ፓርቲ› አለ ‹ፖለቲካ› ግን የለም፡፡ ነጻ ገበያስ
አታውቂም? ‹ገበያ› አለ ‹ነጻ› ግን የለም፡፡ ዴሞክራሲ ሲባልስ አልሰማሽም? ‹ዴሞ(ሕዝብ)› አለ፣‹ክራሲ(አስተዳደር)› ግን
የለም፡፡ በየቢሮው በኮምፒውተር ሲስተም መሥራት ጀምረናል ሲሉ አትሰሚም አዎ ኮምፒውተር በየቢሮው አለ ‹ሲስተም›› ግን የለም፡፡
እንዲህ እያልሽ መቀጠል ነው፡፡››
‹‹ መቃጠሌን ያወቁብኝ
እንደሆነ ግን ከዚህ ቦታ መውረዴ ነው››
‹‹ተይ እባክሽ እዚህ ሀገር
አንቺ ብቻ ነሽ እንዴ ስትቃጠይ የምትወርጅው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየፓርቲው፣ በየእምነት ተቋሙ፣ በየግል ድርጅቱ ስንት
የተቃጠለ አምፖል አለ አይደለም እንዴ፡፡ ማን አወረደው፡፡ መብራት ስለሌለ ማንም ሳይለየው የሚሠራ አምፖል መስሎ ይኖራል፡፡ አየሽ ጨለማ ለአጭበርባሪ ይመቻል፡፡ በብርሃን
ግን ሁሉ ይገለጣል፡፡ እንዲህ ጨለማ የምንሆነው ኤሌክትሪክ በሀገር ጠፍቶ መሰለሽ?››
‹‹ታድያ ለምንድን ነው?››
‹‹ብርሃን ለማጭበርበር
ስለማያመች ነው፡፡ ብርሃን ከመጣ የሚወልቁ ብዙ የተቃጠሉ አምፖሎች አሉ፡፡ ተቃጥሎ ቦታን ላለመልቀቅ ዋናው መፍትሔ ጨለማ
ነው፡፡›› ኩራዝ ይህንን ስትል የቤቱ አባወራ መጣና ‹እፍ› ብሎ አጠፋት፡፡
‹‹በይ ደኅ እደሪ፣ እፍ ብለው
ያበሩናል እፍ ብለው ያጠፉናል›› አለችና ቆርቆሮዋ ውስጥ ገብታ ተኛች፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው
http://www.danielkibret.com/
No comments:
Post a Comment