Tuesday, November 5, 2013

Appendix: የትርፍ አንጀት ነገር!

appendix-4ትርፍ አንጀት በብዙዎች ዘንድ የማያስፈልግ የሰውነት ክፍል ተደርጎ ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ በሰውነታችን ውስጥ ምንም አይነት አስፈላጊ አይደለም የሚባል የአካል ክፍል እንደሌለ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡ ትርፍ አንጀትም እንደ ስሟ ትርፍ ሳትሆን በሰውነት ውስጥ ጠቃሚ ተግባር አላት፡፡ ይሄ ነው የሚባል የሰነድ ማስረጃ ባይገኝም በቃላት ደረጃ ግን ድሮ ድሮ ትርፍ አንጀት እንደ ጨጓራ ሁሉ ትልቅ ተግባር ነበራት ይባላል፡፡ ዛሬም ቢሆን /Appendix/ የአንጀታችን ፖሊስማን በመሆን እንደሚያገለግል ይታወቃል፡፡ እንደ ጣፊያና በአንገታችን አካባቢ እንዳሉ እጢዎች የሚያመነጨው የበሽታ መከላከያ ኬሚካል አለው፡፡ ስለሆነም ይህን የአካል ክፍል እንደ ትርፍ ነገር መቁጠር ችግር አለው፡፡
ትርፍ አንጀት በትንሹና በትልቁ አንጀታች መገናኛ በቀኝ ጎናችን በኩል ትገኛለች፡፡ በመጠኗም ቢሆን ትንሿን ጣታችንን የምታክል ሲሆን በውስጧ የጀርም መከላከያ እጢዎች /Payers patches/ ይገኙበታል ያሉት ዶ/ር ሃይማኖት ናቸው፡፡ ዶ/ር ሃይማኖት በቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሐኪም ሲሆኑ ከእኚህ የዘርፉ ሙያተኛ ጋር በትርፍ አንጀትና በአንጀት መታጠፍ በሽታዎች ዙሪያ ተወያይተናል፡፡
የትርፍ አንጀት በመቆጣቱ ሳቢያ የሚከሰት ቁስለትን ነው የትርፍ አንጀት በሽት የምንለው፡፡ የሚከሰተውም በትርፍ አንጀት ቱቦ መዘጋት ሳቢያ ነው፡፡ ትቦውን እንዲዘጋ የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ የሚናገሩት ዶ/ር ሃይማኖት ምክንያቶቹን እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡
‹‹የትርፍ አንጀት ቱቦን የሚዘጉ ምክንያቶች ውስጥ ጠጠር፣ ድንጋይ መሰል ነገሮች፣ ወስፋትና ትናንሽ የአንጀት ትሎች በቶሎ ሊዘጉት ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎ በሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችን የቁስለት ምንጭ ካለ በደም አማካኝነት ጎጂ ህዋሳት ይሰራጫሉ፡፡
በዚህ ምክንያትም በትርፍ አንጀት አካባቢ ያለው የደም ዝውውር ሂደት የመቋረጥ ዕድል ይገጥመዋል፡፡ እንዲህ ያለው ክስተት በሚፈጠርበት ወቅት ትርፍ አንጀት እየበሰበሰበ ይሄዳል››
እንደ ሙያተኛው ማብራሪያ ትርፍ አንጀት በሽታ ከ132 እስከ 30 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል በስፋት የሚከሰት ቢሆንም በታዳጊ ወጣቶች 10 በመቶ የመከሰት እድል ሲኖረው ስርጭቱ በአዋቂዎች ላይ ከ2 እስከ 3 በመቶ እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡
በትርፍ አንጀት በሽታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች መካከል እንደሆኑ ‹‹ሰፋ ባለ ጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም አመጋገብ እና የዕድሜ መርዘም ይጠቀሳሉ፡፡ ችግሩን ከፆታ አንፃር ካየነው ደግሞ የበሽታውን የመከሰት ዕድል ከሚያሰፉት ተጠቃሾች ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በበለጠ ሁኔታ የተጋለጡ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በተጨባጭ አይታወቅም›› ብለዋል፡፡
በአብዛኛው የበሽታው ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት ህመምተኛው ከእንቅልፉ እንደነቃ መሆኑን የገለፁት ሙያተኛው ዋና ዋና ምልክቶችንም ዘርዝረዋል፡፡
- የሆድ ህመም
- በእንብርት ዙሪያ ቁርጠትና ጭብጥ አድርጎ የመያዝ
- በደረት አካባቢ የሚሰነጥቅ አይነት ህመም
- በሽተኛው ቀና ብሎ ለመጓዝ አይችልም
እነዚህ የህመም ስሜቶች ከታዩ ከአንድ እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ከእንብርት በስተቀኝ ወዳለው የሆድ ክፍል በመሰራጨት በሰውነት ክፍል ቋሚ ህመምን ያስከትላል፡፡ እንዲህ ያለው የህመም ስሜት እንደ ትርፍ አንጀት አቀማመጥ ሊለዋወጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የትርፍ አንጀቱ አቀማመጥ ከትልቁ አንጀት በስተጀርባ ከሆነ የህመም ስሜቱ በቀኝ በኩል በጎን ሊሰማ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቁልቁል ወደ ታች ወደ ሽንት ፊኛ አቅጣቻ የተንጠለጠለ ከሆነ የሽንት ፊኛ በሽታ ሊያስመስል ይችላል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ጥቂት በሆኑ ሰዎች ዘንድ የተፈጥሮ የሆድ እቃ አቀማመጥ ተቃራኒ አቅጣጫን ስለሚይዝ የተጠቀሰው ህመም በቀኝ በኩል በመሰማት ፈንታ ከእንብርት በስተግራ በኩል ሊሰማ ይችላል፡፡ ሆኖም የትርፍ አንጀት በሽታ በወቅቱ ህክምና ተደርጎ ካልታከመና ከፈነዳ ህመሙ ሁሉንም የሆድ ዕቃ አካባቢ ሊያዳርስ ይችላል፡፡ ከላይ ከተገለፁት ምልክቶች በተጨማሪ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ እነዚህም፡-
- አልፎ አልፎ ወይም በተደጋጋሚ የማስመለስ ሁኔታ ይከሰታል
- መለስተኛ የሆነ ትኩሳት
- የምግብ ፍላጎት መቀነስ
- የዓይነ ምድር መድረቅ ወይም በተቃራኒው የተቅማጥ መከሰት
- በህፃናት ዘንድ ከሆነ ምግብ መውሰድ ማቆም፣ መነጫነጭ፣ ተቅማጥና የመሳሰሉ ምልክቶች ይታያሉ፡፡
- በትርፍ አንጀት አካባቢ እብጠት መኖር (Appendicle mass) ይህ እብጠት የሚከሰተው በትልቁ አንጀት ዘርፍ ላይ የሚበቅለው ሞራ ችግር ውስጥ ያለውን ትርፍ አንጀት አካባቢውን በመሸፈን በሽታው ወደ ሌላ እንዳይሰራጭ ያደርገዋል፡፡
በምልክታቸው ከትርፍ አንጀት በሽታ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች በሽታዎች መኖራቸውን በማብራሪያቸው የገለፁት ዶ/ር ሃይማኖት ዋና ዋና የሚባሉትን ለጥንቃቄ እንደሚከተለው ጠቁመዋል፡፡
- የሴት የዘር ፍሬ አመንጪና የመተላለፊያ ቧንቧ ቁስለት
- የሽንት መውረጃ ቱቦ ቁስለት
- የቀኝ ኩላሊት መቁሰል እና
- የአንጀት መታወክ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
በተለምዶ አንዳንድ ሰዎች የትርፍ አንጀት በሽታን ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ከእርግዝና የጤና ችግር ጋር በማያያዝ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ የህክምናው ሳይንስ ምን ይላል? ‹‹ይህ በሽታ ከኤች.አይ.ቪ ህመም ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ባይኖረውም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የሰውነት መከላከያ አቅም በማዳከም ለተለያዩ ደዌዎች እንደሚያጋልጥ ሁሉ የትርፍ አንጀት በሽታንም በተፋጠነ መልኩ የተወሳሰበ ደረጃ ሊያደርሰው ስለሚችል በተለይም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ህሙማን ትርፍ አንጀት በሽታ ምልክት እንደታየባቸው ጊዜ ሳይወስዱ ወደ ጤና ተቋማት መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የትርፍ አንጀት በሽታና እርግዝና በቀጥታ የሚያገናኛቸው ጉዳይ የለም፡፡ ሆኖም ግን በሽታው ሲከሰት የሆድ ህመም የሚመስሉ ምልክቶች መሰማት ከሚገባቸው ስፍራ ውጭ ስለሚሆኑ ሊያሳስቱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ነፍሰጡሮች አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ የማስወረድና ህይወታቸውን የማጣት አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡
በሽታው መኖሩን ለማረጋገጥ ከሚደረጉ ምርመራዎች ሁሉ ጠቃሚ መረጃ የሚሰጠው ህመምተኛው ስለበሽታው ምልክቶችም ሆነ አጠቃላይ ሁኔታ ከሚሰጠው ታሪክ ነው የሚሉት ዶ/ር ሃይማኖት በውጫዊ አካሉ ላይ የተወሰኑ ምርመራዎችን በማድረግ እንዲሁም በላብራቶሪ የነጭ ደም ህዋስ የሚያሳየውን ለውጥ ከመመርመር ባሻገር በአልትራ ሳውንድና በራጅ የህመምተኛው የጤናው ችግር ትርፍ አንጀት መሆን አለመሆኑ ማረጋገጥ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ እንደ ሙያተኛው ትንታኔ የህምምተኛው የጤና ችግር ባሉት አማራጭ የምርመራ ዘዴዎች የትርፍ አንጀት በሽታ ሆኖ ከተገኘ ብቸኛውና አማራጭ የለሹ የህክምና መፍትሄ ቀዶ ህክምና ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ከቀዶ ህክምናው በፊትም ሆነ በኋላም የሚሰጠውን ህክምና አስተማማኝ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ አንቲ ባዮቲክስ መድሃኒቶች በደም ስር የሚሰጡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ አንዳንዴም በቁስለት ምክንያት በትርፍ አንጀት አካባቢ ከመግል ነፃ የሆነ እብጠት ካለ በመድሃኒት ህክምና ቁስለቱ እንዲረጋጋ ከተደረገ በኋላ ለ6 ሳምንታት በመጠበቅ የቀዶ ህክምናው ሊደረግ እንደሚችል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሐኪሙ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ጊዜ ህመምተኞቹ ወደ ጤና ተቋማት በጊዜው ሳይመጡ ሲቀሩ ወይም የቁስለቱ ደረጃ ዝቅተኛ ሲሆን ምንም አይነት ህክም ሳይደረግላቸው የመሻል ሁኔታ ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሽታው ተመልሶ የመከሰት ዕድል የለውም ማለት ግን አይደለም፡፡ እንዲያውም ችግሩ በጥሞና ሳይታወቅ በመቅረቱ የመፈንዳት እድል ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታም በሽታው ከባድና ለህይወት አስጊ ወደ መሆን ያሸጋግረዋል›› የሚሉት ሙያተኛው ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ምንም እንኳን ከቀዶ ህክምና ውጭ አማራጭ የህክምና መፍትሄ የለውም ብልም በአንዳንድ ሀገሮች ትርፍ አንጀት ምንም አይነት ህመም ሆነ ቁስለት ሳያመጣ እንደ ግርዛት ቆርጠው የሚያስወግዱበት ሁኔታ አለ፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ጥቅምም ጉዳትም ይኖረዋል፡፡ ጥቅሙ በትርፍ አንጀት ቁስለት ሳቢያ የሚደርሰውን የሞትና የስቃይ አደጋ ይቀንሳል፡፡ በሌላ በኩል ትርፍ አንጀት ተቆርጦ በመውጣቱ የሚደርሰው ጉዳትን በተመለከተም የሰውነት የመከላከያ አቅም ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ይገመታል›› ብለዋል፡፡
በትርፍ አንጀት በሽታ የተጠቃ አንድ ሰው ችግሩ በቀዶ ህክምና ከተወገደለት በኋላ የሚያደርገው የተለየ ጥንቃቄ እንዳለ የጠየቅናቸው ዶ/ር ሃይማኖት ‹‹በተወሰነ ጊዜ ከባድ ዕቃ ከማንሳት ከመቆጠብ ባሻገር የተለየ ተብሎ የሚገለፅ ጥንቃቄ የሌለ በመሆኑ እንደ ማንኛውም ጤናማ ሰው የዕለት ተዕለት ተግባሩ ሳይስተጓጎል መቀጠል ቢችል ምንም ስጋት እንደማይኖርበት›› መክረዋል፡፡
የትርፍ አንጀት በሽታ ከአጣዳፊ በሽታዎች አንዱ በመሆኑ አፋጣኝ የሆነ የህክምና እርዳታ ካልተሰጠው በስተቀር ውጤቱ አስከፊ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ሰው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት ሙያተኛው አሳስበዋል፡፡
ከአንጀት ጋር በተያያዘ ሌላው የሚነሳው አጣዳፊ ህመም የትንሹና የትልቁ አንጀታችን መታጠፍ ነው፡፡ ይሄም ችግር በተለያዩ ሁኔታዎች እንደሚከሰት ዶ/ር ሃይማኖት ይናገራሉ፡፡ የትንሹም ሆነ የትልቁ አንጀት መርዘም አንዱ በአንዱ ላይ የመጠምለል ሁኔታን ያመጣል፡፡ በዚህም ምክንያት የአንጀት መታጠፍ ይፈጠራል፡፡ በሌላ በኩልም የአንጀት በተለያዩ ምክንያቶች መቁሰል፣ አንዱ አንጀት ከሌላኛው ጋር ሲጣበቅ፣ በሰገራም ሆነ በምግብ ቱቦዎች ሲዘጉ፣ በሆድም ሆነ በአንጀት ውስጥ እጢዎች ሲፈጠሩ፣ የአፈጣጠር ችግርንና እድሜ እየጨመረ ሲሄድ አንጀት እየረዘመ መሄዱ ለአንጀት መታጠፍም ሆነ መዘጋት ከሚያጋልጡ መንስኤዎች ዋነኛዎቹ እንደሆኑ ዶ/ር ሃይማኖት አጫውተውናል፡፡
እንደ ሙያተኛው ማብራሪያ ይህ የጤና ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ ቢሆንም በወጣቶችና ህፃናት ላይ የመታየት እድልም ይኖረዋል፡፡ ለመሆኑ የአንጀት መታጠፍ ያጋጠመው ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች የትኞቹ ናቸው ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ዶ/ር ሃይማኖት ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
- በእንብርት አካባቢ ቁርጠት
- ማስታወክ
- በተወሰኑ ደቂቃዎች እየሄደ የሚመጣ ቁርጠት
- ሰገራ አልወጣም ማለት
- ውሃ ጥም
- የሆድ መነፋት
- ራስን መሳት
- ኢንፌክሽን እና የመሳሰሉት ምልክቶች የትንሹም ሆነ የትልቁ አንጀት ሲታጠፍ ከሚያሳየን ምልክት ዋና ዋና የሚባሉት ናቸው፡፡
የትኛውም የአንጀት ክፍል ላይ መዘጋቱም ሆነ መታጠፉ እንደተከሰተ ኤክስሬይና አልትራሳውንድን ጨምሮ ልዩ ልዩ ምርመራዎች ይካሄዳሉ፡፡ በእነዚህ ምርመራዎች ችግር ከተገኘ ህክምናው በሁለት አቅጣጫ የሚካሄድ ነው፡፡ ችግሩ የተከሰተው በትልቁ አንጀት ላይ ከሆነ ሬክታል ቲዩብ ወደ ሆድ ዕቃ በማስገባት የተጠመለለውን የአንጀት ክፍል እንዲላቀቅ እናደርገዋለን፡፡ ይህ ሆነ ማለት ግን ጠቅላላ ህክምናው ተከናወነ ማለት አይደለም፡፡ ችግሩን ያመጣው የትልቁ አንጀት ከሚገባው በላይ መርዘም ስለሆነ በቀዶ ህክምና በመክፈት ትልቁን አንጀት ቆርጠን በማሳጠር አንዱን ከአንዱ ጋር እንሰፋዋለን፡፡
በተጨማሪ ትንሹ አንጀት ከሆነ በቀዶ ህክምና በመክፈት የተጠመለለውንም ሆነ የተጣበቀውን የአንጀት ክፍል የማስተካከል ስራ እንሰራለን፡፡ ነገር ግን ከፍተን በምናይበት ጊዜ ትንሹ አንጀት ያልበሰበሰና ያልተቀደደ ከሆነ በቀላሉ የማስተካከል ስራ በመስራት እናክመዋለን፡፡ ህክምናውን በተመለከተም ህሙማኑ ሳይዘገዩ ወደ ህክምና ተቋማት ከመጡ ለትርፍ አንጀትም ሆነ ለአንጀት መታጠፍ በሀገራችን የሚሰጠው ህክምና ውጤታማ መሆኑን ሙያተኛው ይናገራሉ፡፡
እንደ ሙያተኛው ማብራሪያ ከሆነ የትርፍ አንጀት በሽታንም ሆነ የአንጀት መታጠፍ በሽታን በእኛ አቅም ለመከላከል የማንችል በመሆኑ ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች የሉም፡፡ ዋናው ጉዳይ የችግሩ ስሜት እንደታየ በፍጥነት ወደ ህክምና መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በትርፍ አንጀትም ሆነ የአንጀት መታጠፍ በሚከሰትበት ጊዜ በመፈንዳትና መግል በመያዝ አጠቃላይ የሆድ ዕቃን በመበከልና በመመረዝ ለከፋ የሞት አደጋ የሚያጋልጡ ችግሮች በመሆናቸው ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ዶ/ር ሃይማኖት በውይይታችን መቋጫ ላይ መክረዋል፡፡
አንጀቴን አንጀቴን የሚያሰኙ ህመሞቻችን
በአንጀት ላይ ከሚከሰቱ ህመሞች መካከል የትርፍ አንጀት ህመም ነው፡፡ በሳይንሳዊ አጠራሩ አፔንዴክስ ወይም ኢፒይታይፊላተስ (Appendix or epityphlifis) ይባላል፡፡ ህመሙ የሚከሰተው በትርፍ አንጀት ማበጥ የተነሳ ነው፡፡
- በትርፍ አንጀት ህመም ወቅት የሚታዩ ምልክቶች
- የሆድ ህመም
- አልፎ አልፎ ራስ ምታት ይኖራል
- የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም መቀነስ
- ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ
- አልፎ አልፎ ቅፅበታዊ የሆነ የማስቀመጥ ሁኔታ
- በሆድ አካባቢ የትልቁ አንጀት መጀመሪያ አካባቢ የእብጠትና የመርገብገብ አይነት የምት ስሜት መኖር እንደዚሁም በጣም የመጫጫን ስሜት መኖር
- ጎንበስ ብለን ቀና በምንልበት ጊዜ ቅፅበታዊ የሆነ የመውጋትና የቁርጠት ስሜት መኖር አብዛኛው ምልክቶች ከአንጀት መታጠፍ ህመም ጋር የሚያመሳስለው በመሆኑ ህመሞቹን በደንብ መለየት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ተጠቃሹ የአንጀት ህመም የአንጀት መታጠፍ ሲሆን ቅፅበታዊ በሆነ መልኩ ሳናስበው በምንሽከረከርበት ጊዜ፣ ከባድ ነገሮችን ከአቅማችን በላይ ሆነውም ስንሸከማቸው፣ ለመዋጥ ያልተለመደ ጠጣር ነገሮችን ወይም ዕቃዎችን በምንውጥበት ጊዜ፣ አንጀታችን ላይ ገብተው የሚጣበቁ ነገሮችን ስንመገብ፣ እንደ ቆሎ አይነት ምግቦችን ብቻ ለረዥም ጊዜ እየበላን ውሃ ብቻ ቀኑን ሙሉ እየጠጣን የምንቆይ ከሆነ (ይህ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የችግሩ መንስኤ ነው) በመሳሰሉት የአንጀት መታጠፍ የመከሰት እድል ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን በቀጥታ ህመሙን ሊያስከትል የሚችል ምክንያት በግልፅ አይታወቅም፡፡ ትርፍ አንጀት በአብዛኛው አንጀት ምግብን ተቀብሎ በደንብ መጠቅለልና ወደ ክብ አይነት ቅርፅ እያስያዘ በሚያንቀሳቅስበት የአንጀት ክፍል በብዛት ይከሰታል፡፡ በተለይም በታዳጊዎችና በህፃናት ላይ ሲግሞይድ በምንለው የአንጀታችን ክፍል ላይ በብዛት ሲከሰት ከጨጓራ ወደ አንጀት የሚሄደውን ክፍል ይዞ የሚፈጠረው እንደዚሁም በትልቁ አንጀት መጀመሪያ አካባቢ የሚከሰትም ይገኛል፡፡ በትልቁ አንጀት ዓለም የተባለውን ቦታም የሚያጠቃው የትርፍ አንጀት በብዛት የቃጫነት ፀባይ ያላቸውን ምግቦች ተመግበው መፍጨት የማይችሉ ህመምተኞችን በብዛት ያጠቃቸዋል፡፡
ለአንጀት መታጠፍ ተጠቃሽ ምክንያቶች
- ለትክክለኛ የምግብ ውህድ የሚያገለግሉ ለምሳሌ የወተት ተዋፅኦ እጥረት፣ የቃጫነት ፀባይ ያላቸው ምግቦችን አለመውሰድ ለምሳሌ ጎመን፣ ሙዝ፣… ፈሳሽ በደንብ አለመውሰድና በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡
- ለረጅም ጊዜ ከባድ ዕቃዎችን ማንሳት
- ለረጅም ጊዜ ሰገራ ለማስወጣት መቸገርና ብዙ ሰዓት ማማጥ ይህም ከድርቀት የመጣ ሊሆን ይችላል
- ለብዙ ጊዜ የዓይነ ምድር መውጫን በሳሙና መታጠብ ይህም የሰገራ መውጫ አካባቢ ሰገራ መኖሩን የመጠቆም ወይም ሴንስ አድርጎ የማሳወቅ ሁኔታውን ስለሚቀንሰው ነው
- የተለያዩ ምግቦች በምንመገብበት ወቅት አንጀት ላይ ሄደው የመጣበቅ ፀባይ የሚያሳዩ ከሆነ ይህ በብዛት በሴቶች ላይ በእርግዝና ወቅት ሊከሰት ይችላል፡፡
- በጣም መተጣጠፍ የሚበዛባቸው እንቅስቃሴዎችን በማብዛት
የአንጀት መታጠፍ ህመም ምልክቶች

- ሲጀምር አካባቢ የተወሰኑ የሆድ ክፍሎች ላይ እየከፋፈሉ በመቀያየር የሚሰማ የህመም ስሜት በመቀጠልም መላ ሆድን የሚሰማ ስቃይ
- ቦውል የምንለው የምግብ ክልላዊ ቅርፁን ጠብቆ የመሄድ እንቅስቃሴ በመካከል ሲታገድ ወይም በተወሰነ ቦታ ሄዶ መቆም ማቅለሽለሽና ማስታወክ
- ደም የተቀላቀለበት ሰገራ መውጣት
- የድርቀት መከሰት
- የሰውነት መዛልና ራስን ድንገት መሳት
- ቶሎ ህክምና ካልተወሰደም የአንጀት በከፍተኛ ሁኔታ መታጠፍና የሆድ አካባቢ መጠጠርና መነፋፋት እንደዚሁም ሰንጥቆ በአንጀት ላይ እስከማሳየት የሚያደርስ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡
ለሁለቱም ለትርፍ አንጀትም ሆነ ለአንጀት መታጠፍ ሲቲ ስካን ከአልትራሳውድን በበለጠ (94 ፐርሰንት በበለጠ ሴንስቲቭ እና ስፔስፊክ ስለሆነ) እብጠቱንም ሆነ መተጣጠፉን በግልፅ ማሳየት ይቻላል፡፡ በዚህም ወደ ቀጣዩ ህክምና ወደ ቀዶ ህክምናም ሆነ ወደ ሌላ ህክምና ለመሄድ ሁለቱንም በደንብ መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህም በሲቲ ስካን በቀላሉ ለይተን ማወቅ እንችላለን፡፡ 


tenadam

No comments:

Post a Comment