Tuesday, November 26, 2013

የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጠበት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናታዊ ውይይት በጥብቅ ሥነ ሥርዐታዊ ኹኔታ ውስጥ ይካሄዳል፤ ለካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤት አመራሮች እና የምእመናን ተወካዮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል


A.A Diosces Head Office
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት (ፎቶ: ሀገረ ስብከት)
  • ጥናቱ – እያንዳንዳቸው ከ50 – 122 ገጾች ያሏቸውን 15 የፖሊሲና ማኑዋል አርእስተ ጉዳዮን ያካተተ መኾኑ ተገልጦአል፡፡
  • ከእነርሱም መካከል፡- የሰው ሀብት አስተዳደር፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የፋይናንስ፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን፤ የዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማ፤ የግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር፤ የኢንቨስትመንትና ምግባረ ሠናይ፤ የቅርስና ቱሪዝም፤ የመንፈሳዊ ፍትሕ፣ የአስተዳደር እና የሥራ ክርክር ጉዳዮች ችሎቶችን የተመለከቱ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ዝርዝር አሠራሮች ይገኙበታል፡፡
  • ዛሬ፣ ኅዳር ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በሀ/ስብከቱ አዳራሽ እንደሚጀመር የሚጠበቀው ጥናታዊ ውይይቱ በሦስት ዙሮች የሚካሄድ ሲኾን ከብር 160,000 በላይ የማስፈጸሚያ በጀት ተመድቦለታል፡፡
  • በጥናታዊ ውይይቱ ላይ በተጋባዥነት ከሚሳተፉት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ዋና ሓላፊዎች ጋራ የሀ/ስብከቱ የዋና ክፍል እና የክፍል ሓላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጆችና የክፍል ሓላፊዎች እንዲሁም የ167 አድባራትና ገዳማት ሠራተኞች ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ በተሳታፊዎች ውክልና ረገድ የለውጥ አመራሩ ማኅበራዊ መሠረቶችና ዋነኛ ፈጻሚዎች ለኾኑት ካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የሰንበት ት/ቤት አመራሮችና የምእመናን ተወካዮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
  • ጥናታዊ ውይይቱ የለውጥ አመራር ፖሊሲዎቹንና ማኑዋሎቹን በማስተዋወቅ (ኦሬንቴሽን)፣ በማሥረጽ እና በተሳታፊዎች ውይይት በማዳበር ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡
  • ለሦስት ወራት የቆየውና የማይናቅ የለውጥ ዜናና ተነሣሽነት በሓላፊው፣ ሠራተኛውና አገልጋዩ ላይ እንዳሰማና እንደፈጠረ የሚታመነው የሽግግር ወቅት በተፈጸመበት ማግሥት የሚጀመረው የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናታዊ ውይይት÷ ሠልጣኞች ያላቸው ተጨባጭ አቅምና ለለውጡ ያላቸው ዝግጁነት በግልጽ መድረክ የሚፈተንበት፣ ጥቅመኛ አሉባልተኛውና የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ቅጥረኛው ከሐቀኛ ሠራተኛውና ቀናዒ ኦርቶዶክሳዊው የሚለይበት ኹነኛ ወቅት እንደሚኾን ተመልክቷል፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ ሠልጣኝ ለጥናታዊ ውይይቱ ያለውን የተሳትፎ አግባብነት በጥብቅ ሥነ ሥርዓታዊ ቁጥጥር ከማረጋገጥ ጀምሮ በጥናታዊ ውይይት ተሳትፎውና ተሳትፎውን ተከትሎ በሚካሄደው ምደባ እንደሚገለጽ ተጠቁሟል፡፡
  • ከምንም ዐይነት ክፍያ ነጻ በኾነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና ሥርዐት በማገናዘብ የተሠራው ይኸው የለውጥ አመራር ጥናት ቤተ ክርስቲያናችንን ከብር ሦስት ሚልዮን ያላነሰ ወጪ እንደሚያድን ተገምቷል፡፡
  • ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በገዳማውያን ጸሎት ጭምር እየታገዘ ጥናቱን በታታሪነት ሲያካሂድ የቆየው የባለሞያ ቡድኑ ከሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት የተውጣጡትን ጨምሮ ዘጠኝ ከፍተኛ ኤክፐርቶች በአባልነት የሚገኙበት ነው፡፡ የባለሞያ ቡድኑን በሰብሳቢነት ያስተባበሩበት ከፍተኛ የሥራ አመራር አማካሪና የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ አባል የኾኑት አቶ ታደሰ አሰፋ ናቸው፡፡
የጥናቱንና የጥናታዊ ውይይቱን ተጨማሪ መረጃዎች ይከታተሉ

 http://haratewahido.wordpress.com

No comments:

Post a Comment