Wednesday, October 30, 2013

የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቋመ፤ የዕጩዎችን ዝርዝር ለርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ያቀርባል


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው፣ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ዘጠነኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ የሚያስፈጽም አስመራጭ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ስድስት ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ሲኾን የትግራይ፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋና ኦሮሚያ አህጉረ ስብከትን በመወከል የተመረጡ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት÷ ከትግራይ ብፁዕ አቡነ፣ ከወሎ የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ከጎንደር የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ከጎጃም የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ከኦሮሚያ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት ተሠይመዋል፡፡
ዕጩዎች በሕገ ቤተ ክርስቲያን ለኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በወጣው መስፈርት ብቻና ብቻ ለይቶ እንዲያቀርብ በምልአተ ጉባኤው ከባድ አደራ የተጣለበት አስመራጭ ኮሚቴው÷ ከመስፈርቱ ውጭ ጎጠኝነትን ጨምሮ በተለያዩ መደለያዎች ሢመተ ኤጲስ ቆጶስነትን ለማግኘት ካሰፈሰፉ ቆሞሳት እንዲጠበቅ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው በመምረጫ መስፈርቱ መሠረት የዕጩዎችን ማንነት ከመለየት ባሻገር ከበጀት፣ ከመንበረ ጵጵስና እና ከጽ/ቤቶች መማሏት አኳያ ኤጲስ ቆጶሳቱ ሊመደቡባቸው የሚገቡ አህጉረ ስብከትን በቅደም ተከተል በመለየት ብዛታቸውን የመወሰን ሥራም እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን ጨርሶ ሪፖርቱን የሚያቀርበው ለመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሲኾን ሥርዐተ ሢመቱም የምልአተ ጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ እንደሚፈጸም ተመልክቷል፡፡
የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሌሎች መረጃዎችን ወደፊት እንደምናቀርብ ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡

haratewahido

No comments:

Post a Comment