Thursday, October 24, 2013

ራስን ማጥፋት ለምን ?

ካቻምና ነሐሴ መጨረሻ ላይ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ቅጥር ግቢ ውስጥ አራት ሰዓት ተኩል ገደማ ይሆናል፡፡
በዕለቱ ምንም እንኳ ሰዓቱ በርካታ ነገሮችን ለማከናወን የወጠኑ ሠራተኞች፣ በቅጥሩ ለተለያዩ የሥራ ጉዳዮች የተገኙ ሌሎች ሰዎችም ወዲያ ወዲህ ቢሉ፤ ያለምንም ዕረፍት ሊፍቶች ቢከፈቱና ቢዘጉ እንዲሁም የእግር ዳናዎች በብዛት ቢሰሙም ሁሉም ነገር እንደተለመደው መስመር የያዘና ሰላማዊ ነበር፡፡
በቅፅበት ግን ሰዎች ይሯሯጡና ይጯጯሁ ጀመር፡፡ መናገር አቅቷቸው በድንጋጤ በቆሙበት የቀሩ፣ የሚርበተበቱና አንዲት እንኳ ቃል ማውጣት ተስኗቸው እንዲሁ እምባቸውን የሚያፈሱም ነበሩ፡፡ ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ ተቀየረ፡፡ ለዚህ ምክንያት የነበረው ደግሞ በኮሚሽኑ ረዳት የሒሳብ ሠራተኛ የነበሩት ወይዘሪት አልማዝ ልዑልሰገድ ከፎቅ ላይ በመወርወር ራሳቸውን ማጥፋታቸው ነበር፡፡ የሒሳብ ሠራተኛዋ ጥሩ ክፍያ፤ ጥሩ ሊባል የሚችል ኑሮ ያላቸው ስለነበሩ ራሷቸውን የማጥፋታቸው ዜና በማኅበራዊ ድረገጾች እንዲሁም በጋዜጣ ሲታይ ብዙዎች ምን ሆነው ራሳቸውን ሊያጠፉ በቁ? ብለው እንዲጠይቁ ተገደዋል፡፡
ከደቂቃዎች በፊት በሙሉ ጤንነት የነበረ ምናልባትም ከደቂቃዎች በፊት አብረው ሻይ ቡና ያሉት ወይም ሥራን በሚመለከት ያነጋገሩት ሰው በቅፅበት ሕይወቱ አለፈ ሲባል እውነቱ ከምንም በላይ ሊቀበሉት ይከብዳል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ያ ሰው ሕይወቱን ያጠፋው በራሱ እጅ መሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ስሜት ይረብሻል፡፡ ቀደም ሲል ፈፅሞ አንስተው ምናልባትም ስለ ሕይወት የማያውቁትን ጥያቄ በተደጋጋሚ ለራስዎ እንዲያነሱ የግድ ይላል፡፡ በዚህ ምክንያት ራስን ማጥፋት ለማኅበረሰቡ ሁሌም አስደንጋጭና በቀላሉ ለመቀበል የሚቸግር የሕይወት እውነት ነው፡፡ ከመሥሪያ ቤቱ የሥራ ባልደረቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው የሒሳብ ሠራተኛዋ በዕለቱ ‹‹መኖር አልፈልግም›› ሲሉ ያደመጡ ጓደኞቻቸው የሆኑትን እንዲነግሯቸው ቢጠይቋቸውም ለመግለጽ አልፈለጉም ነበር፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች በብዛት በአዕምሮ ጭንቀትና መረበሽ ውስጥ የሚያልፉ ናቸው፡፡ ጥናቶቹ እንደሚያመለክቱት ከእነዚህ ሰዎች ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት በዲፕሬሽን (ድብርት) የሚጠቁ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በቅፅበታዊ ብስጭት አልያም ጭንቀት በሚፈጠር የአእምሮ መናወጥ (ሳይኮሲስ) ራስን ወደ ማጥፋት የሚያመሩ ናቸው፡፡
ፈተና ላይ ከተቀመጡ በኋላ የፈተናውን መክበድና በገመቱት አልያም በጠበቁት መጠን ጥያቄዎችን መመለስ አለመቻላቸውን በማሰብና የፈለግነውን ውጤት አጥተናል ብለው በመደምደም ራሳቸውን ያጠፉ ተማሪዎችም አሉ፡፡ እንደጭንቀታቸውና እንዳመኑት ሳይሆን በመጨረሻ ውጤታቸው ከብዙዎች በላይና ጥሩ ሊባል የሚችል ሆኖ የታየባቸው አጋጣሚዎችም በተለያየ ጊዜያት ተስተውለዋል፡፡
በድንገተኛ የአእምሮ መናወጥ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚያስቡ ብሎም በተደጋጋሚ የሞከሩ እንደሚያጋጥሙ የኢትዮጵያ ሥነ ልቦና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሮግራም ረዳት የሆነችው ወይዘሪት ቃልኪዳን ብርሃኑ ትናገራለች፡፡ በፍቅር ግንኙነት፣ ከሥራ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩና ያልተሳካላቸው ነገር ግን በመጨረሻ የምክር አገልግሎት ሽተው ወደ ቢሯቸው ጐራ የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡
በዚህ መልኩ ካጋጠሟት ሰዎች መካከል በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያነት የምትሠራው የ34 ዓመቷ ወጣት አንዷ ነበረች፡፡ ከዓመታት በፊት ወደ ውጭ አገር የሄደ ፍቅረኛዋ ምንም እንኳ ተለያይተው በቆዩባቸው ዓመታት ይደዋወሉ፤ በአካል ከመራራቃቸው በቀር ሁሉም ነገር እንደቀድሞ የነበረ ቢሆንም ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ትዳር ከመሠረተ ትንሽ መቆየቱን ይነግራታል፡፡ ይህን እውነት መቀበል እጅግ ስለከበዳት ነገሩን እንደሰማች ‹‹ከዚህ ሁሉ በኋላ ሕይወቴ ትርጉም አይኖረውም›› ብላ በማሰብ ራሷን ለማጥፋት ወሰነች፡፡ ሙከራዋ ሳይሳካ በመቅረቱ በመጨረሻ የሥነ ልቦና ባለሙያ ለማየት ፈቃደኛ ሆነች፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሳይካትሪ የትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ራስን የማጥፋት ሙከራ በሴቶች ቢበዛም ራሳቸውን በማጥፋት የሚሳካላቸው ግን ወንዶች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚቀመጠው ነገር ከሴቶቹ ጋር ሲነጻጸር ወንዶች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩት አደገኛ ጉዳይ ዘዴዎችን መሆኑ ነው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት በጥቅሉ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር ራስን ማጥፋት በአገራችን ከፍተኛ ነው ለማለት የሚያስችል መረጃ የለም፡፡ ይልቁንም መረጃዎች የሚያሳዩት ራስን የማጥፋት ነገር በተወሰነ መልኩ አነስ የሚል መሆኑን ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ከአደጉ አገሮች ጋር ሲነጻጸር በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ራስን የማጥፋት ነገር ይቀንሳል፡፡
‹‹ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ነገሮች ሰዎች ራሳቸውን እንዳያጠፉ ይገድቧቸዋል፡፡ ሃይማኖትን ብንመለከት ሁሉም ሃይማኖት ማለት ይቻላል ራስን ማጥፋትን ያወግዛል፡፡ ምንም እንኳ ሰዎች ከፍተኛ ራስን የማጥፋት ግፊት ቢኖርባቸው ከሞት በኋላ ያለን ሕይወት አስበው ሐሳባቸውን እንደሚቀይሩ በሥራ አጋጣሚዬ ብዙ ተመልክቻለሁ፡፡››
ዲፕሬሽን በተባለው ከባድ የአእምሮ ሕመም የተያዙ ሰዎች 60 በመቶ ራሳቸውን  ማጥፋት ያስባሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 15 በመቶ ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የሆስፒታሎችና የፖሊስ ሪፖርትን መሠረት አድርጎ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው በከተማው ውስጥ በአማካይ በቀን አንድ ሰው ራሱን እንደሚያጠፋ መታወቁን ዶ/ር ሰለሞን ያስታውሳሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት በቅፅበታዊ ነገር የሚወሰደው ራስን  የማጥፋት ዕርምጃ ከአጠቃላዩ አምስት በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ብዙ የተለመደም አይደለም፡፡ ነገር ግን በሁለቱም መንገድ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት ሲያስቡ የሚያሳዩዋቸው ያልተለመዱ ባሕርያት ሲኖሩ ይህን እንደ ምልክት መውሰድ ይቻላል፡፡ እውነታው ግን በማኅበረሰቡ ዘንድ ራስን ማጥፋት እንደነውር ስለሚታይ ችግሩም የተደበቀ ስለሆነ ራስን ስለማጥፋት አይወራም፡፡ ሰዎችም በሌሎች ላይ ስለሚመለከቷቸው የተለዩ ነገሮች ቀርበው መጠየቅ አይደፍሩም፡፡ ይህ ሰዎች ራስን ስለማጥፋት ወይም ራስን ወደ ማጥፋት ስለሚያመሩ ለውጦች እንዳይወያዩና ወደ መፍትሔ እንዳይሄዱ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡
ኤልያስ ተክሌ ከአራት ዓመታት በፊት ራሱን ስላጠፋ ጓደኛው ስንጠይቀው ጓደኛው ራሱን ያጠፋበትን ወር ዕለትና ሰዓት በትክክል ለመናገር ለቅፅበት እንኳ ማሰብ አላስፈለገውም፡፡ ነገሩ ትናንት የተፈጠረ ያህል ሁሉም ነገር በአዕምሮ በጉልህ ተሥሏል፡፡ ትውስታው ከጥልቅ ሐዘን ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ስለ ሕይወት ብሩህ ምልከታ ያለው ለመኖር የሚጓጓና ነገን በተስፋ የሚናፍቅ የአብሮ አደግ ጓደኛው ራስን የማጥፋት ዜና የፈጠረበት ሐዘን ዓመታት የሚሽሩት ዓይነት አይመስልም፡፡ የጓደኛው ራሱን ማጥፋት ዛሬም ለእሱ እንቆቅልሽ ነው፡፡ እንቆቅልሹን ለመፍታት ሞክሮ ግን አያውቅም፡፡ ነገሩ ሀዘኑን ከመቀስቀስ በቀር ውጭ የሚወደው ጓደኛውን አይመልሰውምና፡፡ ኤልያስ ምንም እንኳ የጓደኛውን ሞት አምኖ ቢቀበልም ነገሩ በተለያየ መልኩ ሕይወቱን እንደቀየረው ይናገራል፡፡
ጓደኛው በብዙ መልኩ እሱ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው የሚናገረው ኤልያስ ወደኋላ መለስ ብሎ ነገሮችን በማየት ራሱን ከማጥፋቱ በፊት ጓደኛው ላይ የተለያዩ የባሕሪ ለውጦች ይታዩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከልጅነት ጀምሮ አድገው ወደ ሥራ ዓለም ከገቡ በኋላም የጠበቀው ጓደኝነታቸው ጓደኛው ራሱን ከማጥፋቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ሊቋረጥ የግድ ነበር፡፡ ‹‹በማይረባ ምክንያት ተጣላን›› በማለት በፀፀት ያስታውሳል ኤልያስ፡፡
‹‹መኖር ምን ያደርጋል? ሕይወት ምን ትርጉም አለው? የሚሻለው መሞት ነው የሚሉ ዓይነት ነገሮች በተደጋጋሚ ሲሰሙ ሰዎችን ቀርቦ ማነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ሞክሮ መትረፍ በራሱ አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው የተረፉ ሰዎች ደግመው የመሞከር ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ዙሪያ ያሉ ዘመድ ጓደኞች የግለሰቦቹን የወደፊት ዕቅድ የመጠየቅና የመከታተል ሁኔታቸውን የማጥናት እንዲሁም የጤና አልያም ሌላ ችግር ካለባቸው እንዲፈታ ማድረግ እንደሚገባቸው ይናገራሉ፡፡
ራስን ስለማጥፋት ሲወራ የመጨረሻው የነፍስ ህቅታ ደቂቃዎች ምን ይመስላሉ? በብዙዎች ጭንቅላት የሚመላለስ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ቤተሰቦቹ ላይ በነበረው ቅያሜ ከአሥር ዓመታት በፊት በአይጥ መርዝ ሕይወቱን በእጁ ለማሳለፍ የሞከረው ሽመልስ ከበደ በዕለቱ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ የተመረቀበት ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ በተለያየ መልኩ ለሱ ዝቅተኛ አመለካከት የነበራቸው ቢሆንም የምርቃቱ ዕለት ሰፊ ድግስ ደግሰው ደስታና ፌሽታ ማድረጋቸው ለሱ ማስመሰልና ለታይታ እንደሆነ ስለተሰማው ራሱን አጥፍቶ ደስታቸውን በሀዘን በመቀየር ሊቀጣቸው አስቦ ነበር፡፡
‹‹በመጨረሻው ሰዓት አእምሮዬም አካሌም ደክሞ ነበር፡፡ ሁለቱ እህቶቼ ፊቴ ላይ ድቅን አሉብኝ፡፡ እንደገና መኖር መትረፍ ፈለግኩኝ›› ሲል አስጨናቂዎቹን ደቂቃዎች ያስታውሳል፡፡
የተለያዩ ራስን የማጥፋት ታሪኮች ሲሰሙ የአንዳንዶቹ ምክንያት ሕይወትን ለማጥፋት በቂ አይደለም ሊያስብል ቢችልም በቂ ነው አይደለም ብሎ ለመደምደም ምናልባትም በጉዳዩ ባለቤቶች ቦታ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የወደዳት ልጅ የፍቅር ጥያቄውን ያልተቀበለችው አንድ የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ራሱን ሲያጠፋ ጥሎ ያለፈው መልዕክት ‹‹የምፈልገውን ነገር እያጣሁኝ ለምን እኖራለሁ?›› የሚል ነበር፡፡
በቅፅበታዊ ንዴት ወይም ጭንቀት ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ሰዎች ነገሮችን የሚያስተናግዱበት ሥነ ልቦናዊ አቅም ያልዳበረ ነው፡፡ ራስን የማጥፋት ዕርምጃውን ለመውሰድም በውስጣቸው ብዙ ትግል ይፈጠራል፡፡ ሙከራቸውም አብዛኛውን ጊዜ የተሳካ አይሆንም፡፡
ዶ/ር ሰለሞን የሚመለከቷቸው ሕመምተኞች ከሞላ ጎደል ሁሉም በከፍተኛ ዲፕሬሽን የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምንም ዓይነት የኑሮ ችግር የሌለባቸው ምናልባትም ሁሉ የተሟላላቸው ነገር ግን በከባድ የአዕምሮ ሕመም የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች እያንዳንዱ ቀን ሊሸከሙት የማከብድ፣ የእያንዳንዱ ቀን ብርሃን ሊቋቋሙት የማይቻል ይሆናል፡፡ በሰላም አሳድረኝ በማለት ፈንታ ወደ አልጋቸው ሲሄዱ ዕለቱ የመጨረሻ የሕይወት ቀናቸው እንዲሆን ፈጣሪያቸውን የሚለምኑና ነግቶ ራሳቸውን በሕይወት ሲያገኙ እጅግ የሚበሳጩ ሰዎች በተደጋጋሚ አጋጥመዋቸዋል፡፡
‹‹የተማረ፣ የተደራጀ ኑሮ ያለው በሁሉም መስፈርት ቢመዘን ጥሩ የሚባለ ኑሮ ያለው አንድ ሕመምተኛ ነበረኝ፡፡ እያንዳንዱን ቀን የሚያሳልፈው ያለምንም ስቃይ እንዴት በቀላሉ ራሱን ማጥፋት እንደሚችል ኢንተርኔት ላይ በመፈለግ ነበር፡፡›› በማለት አጋጣሚውን ያስታወሱት ዶ/ር ሰለሞን እንደዚህ ያሉት ሰዎች ራስን የማጥፋት ነገር በውጫዊ ሁኔታዎች ሳይሆን በውስጣዊ የአዕምሮ ሕመም የተጫነባቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡
ዶ/ር አብድልረሺድ አብዱላሒ በክሪ ራስን ማጥፋትን በሚመለከት የፖሊስና የሆስፒታሎችን ሪፖርት መሠረት በማድረግ አዲስ አበባ ላይ አትኩረው የሠሩት ጥናት እንደሚያሳየው በ15 ተከታታይ ዓመታት ውስጥ የሴት ራስን የማጥፋት ጥቅል ሬት 2.45 ሲሆን፣ የወንዶች ደግሞ 12.7 ነው፡፡ በብዛት የሚታየው ራስን የማጥፋት ዘዴ መታነቅ ሲሆን፣ ይህ 70.2 በመቶ ይሆናል፡፡
ሰዎች አፍረው እውነቱን ለመናገር ባይደፍሩም በርካታ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው በተለያየ አጋጣሚ ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረዋል ወይም አስበዋል፡፡ በ1974 ዓ.ም. ራስን የማጥፋት እንዲሁም ምክንያቱ ያልታወቀ ሞት 88 የነበረ ሲሆን፣ 1988 ይህ ቁጥር ወደ 269 አድጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ የወንዶችና የሴቶች ምጣኔ 5.19፡1 ነው፡፡ ጥናቱ በተደረገባቸው 15 ዓመታት የተወሰዱ ራስን የማጥፋት ዕርምጃዎች ራስን መስቀል (1502)፣ ውኃ ውስጥ መግባት (328)፣ መርዝ (161) እና ያልታወቁ መንገዶች (150) ነበሩ፡፡
በወቅቱ የተደረጉ ራስን የማጥፋት ሙከራዎች በመቶ ሺሕኛ ሲሰሉ 1974 ዓ.ም. 1092 ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በ1988 ወደ 3675 አድጓል፡፡
ጥናቱ እንደሚያሳየው ራስን የማጥፋት ሙከራዎች አብዛኛውን ጊዜ ለሆስፒታል ሪፖርት ስለማይደረጉ ከተደረጉም እንደ ድንገተኛ አደጋ ተደርገው ስለሚቀርቡ ቁጥሩ ትክክለኛውን ነገር ላያሳይ ይችላል፡፡ ጥናቱ በእሳት ቃጠሎ፣ በፈንጂ፣ በስለት፣ ከከፍታ በመዝለል የመሳሰሉ ራስን ማጥፋቶችን አይጨምርም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አጋጣሚዎች እንደ ድንገተኛ አደጋ ሊታዩ ይችላሉና፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩት ወጣቶች በመሆናቸው ራስን ማጥፋትን መከላከል ላይ ቢሠራ የዕርምጃው አንድምታ ትልቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጦች ቢኖሩም ሰዎች የአዕምሮ ሕመምን እንደ ማንኛውም አካላዊ ሕመም አይተው ወደ ባለሙያ ለመሄድ ያላቸው ተነሳሽነት ዛሬም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከሚመለከቷቸው ሕመምተኞች አብዛኞቹ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ መፍትሔዎችን ሞክረው በመጨረሻ ወደ ሕክምና ለመሄድ የወሰኑ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት በአማኑኤል ሆስፒታል በአንድ ሺሕ ሕመምተኞች ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ሌሎች አማራጮችን ሳያዩ ሕክምናን እንደ ቀዳሚ መፍትሔ ተመልክተው ወደ አዕምሮ ሐኪም የሄዱ ታካሚዎች ከግማሽ በመቶ በታች ናቸው፡፡
ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ራስን ማጥፋት ባደጉት አገሮች ሁለት ዓይነት ሥርጭት (Bi-polar Distribution) አለው፡፡ ይህ ሥርጭት ራስን ማጥፋት በብዛት የሚታየው በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ እንዲሁም ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ነው፡፡ ወጣትነት የሽግግር ጊዜ እንደመሆኑ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት የመፈተኛ ጊዜም ነው፡፡ በሌላ በኩል እርጅና ብቸኝነት የሚጫንበት ድካም የሚመጣበት ነው፡፡ ይህ የሚያሳድረው ጭንቀት ራስን ወደ ማጥፋት ሊያመራ ይችላል፡፡ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ግን ማኅበራዊ ትስስር ጠንካራ በመሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብቸኛ ስለማይሆኑ፣ በዕድሜያቸው ተከብረው ለሽምግልና የሚፈለጉ በመሆኑ፣ በብዛት ወደ ቤተ ክርስቲያን ፊታቸውን የሚመልሱበት ጊዜ በመሆኑ ራሳቸውን የሚያጠፉበት ሁኔታ አለመኖሩን ዶ/ር ሰለሞን ይገምታሉ፡፡ ይልቁንም የሚያውቋቸው ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች በወጣት አልያም በአዋቂነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሥርጭቱ ወጣቶችን በሚመለከት በአገራችንም የሚታይ እውነት ነው፡፡
የኢኮኖሚ ሽግግር፣ የውጭ ባሕል ተፅዕኖና የአኗኗር ዘዬ ለውጥ በአገራችን እውነታ በምን ያህል ደረጃ ራስን ለማጥፋት አስተዋጽኦ የደርጋሉ? የሚል ጥያቄ ለዶ/ር ሰለሞን አንስተን ነበር፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ ማኅበራዊ ሽግግር በራሱ ለአዕምሮ ጤና አደጋ ነው፡፡ በአገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ሽግግሮች እየታዩ ነው፡፡ ስለዚህ በተለይም ወጣቱ እነዚህ ሽግግሮች በሚፈጥሯቸው ግፊቶች የተወጠረ ነው፡፡ ግፊቶቹ የተወሰኑት ጠቃሚ ሌሎቹ ደግሞ ጐጂዎች ናቸው፡፡ ግላዊነት፣ ደስታን በማንኛውም መንገድ መሻት ራስን ወደማጥፋት ሊያመሩ ይችላሉ፡፡ በማንኛውም መንገድ ደስታን መሻት የተለያዩ አነቃቂ እፆችን ወደ መጠቀም ያመራል፡፡ እነዚህ አነቃቂ እፆች ደግሞ ለዲፕሬሽን ያጋልጣሉ፡፡
ሽግግሮቹ ኑሮ ላይ ጫና ይፈጥራሉ፡፡ ሁሉም ሰው ከእነዚህ ሽግግሮች ጋር ለመራመድ ይሮጣል፡፡ በዚህ ሩጫ ውስጥ የሚሳካላቸው አሉ፡፡ የማይሳካላቸው ደግሞ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ሊያድርባቸውና ለዲፕሬሽን ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ በአንድ ወቅት በከተማችን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን ያጠፉ ታዋቂ ባለሀብቶች ታሪክ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ሽግግሮች የሚፈጥሩት ጫና እንዴት ራስን ለማጥፋት ምክንያት እንደሚሆን ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ያምናሉ፡፡
‹‹ሰው ራሱን ወይም ሌላ ነገሩን ሲያመው ወደ ሐኪም እንደሚሄድ ሁሉ ራሱን የማጥፋት ፍላጎት በውስጡ ሲፈጠር ለምን መኖር ያስጠላኛል? ለምን ራስህን አጥፋ አጥፋ ይለኛል? ብሎ በመጠየቅ ወደ አዕምሮ ሐኪም በመሄድ የነገሩን መፍትሔ ለማግኘት መሻት አለበት፡፡ ምክንያቱም ችግሩ በምክር በሕክምና የሚፈታ ነውና››
ዶ/ር ሰለሞን ራስን አጥፋ የሚል ነገር ወደ አዕምሮ ስለመጣ ወይም ችግሮችን (የኑሮ) በአቋራጭ ለማምለጥ ራስን የማጥፋት ዕርምጃ ውጤቱ አስከፊ ይሆናል ይላሉ፡፡ ሕይወቱን ለሚያጣው ሰው ጉዳት ለቀሪ ቤተሰብ ዘመድም የልብ ስብራት ያስከትላል፡፡ ለሚቀርቡትና የመፍትሔ አቅጣጫ ሊያሳየኝ ይችላል ለሚሉት ቤተሰብ ጓደኛ ችግርን መንገርም መሸነፍ ደካማነትም እንዳልሆነ ማመን ያስፈልጋል፡፡
በአማኑኤል ሆስፒታል በጥናትና ሥልጠና ክፍል የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዘገየ ዮሐንስ እንዳሉት ራስን ማጥፋት የአዕምሮ ሕመም አንዱ ምልክት ነው፡፡ ምንም እንኳ በከፍተኛ ሁኔታ ራስን ለማጥፋት ምክንያት የሚሆነው ዲፕሬሽን ቢሆንም ስኪዞፍሬኒያ፣ አደጋን (አጋጣሚን) ተከትሎ የሚደርስ የአዕምሮ ሕመም፣ ጭንቀትና ሌሎችም የአዕምሮ ችግሮች በተለያየ ደረጃ ራስን ለማጥፋት ምክንያት ይሆናሉ፡፡
አቶ ዘገየ እንደሚሉት ራስን ማጥፋት ምክንያቱ ይሄ ነው ያ ለማለት በሚያስችል መልኩ የተጠና ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቶቹ ባዮሎጂካል፣ ሥነልቦናዊ አልያም ማኅራዊ ነገሮች ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ መፍትሔውም የተለያዩ ነገሮችን አቀናጅቶ የያዘ ነው፡፡ በፈተና ወቅት የሚፈጠር ጭንቀት፣ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነገርና ጦርነት የተወሰኑ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment