Tuesday, October 15, 2013

ጉዞ ዶላርና ሐሳር ወደ ምታፈልቀው ምድር

lottery-winner
እነሆ መረቡ ተጣለ፡፡ ሚሊየን አሶች አሰፍስፈው የሚጠብቁት የዲቪ መረብ፡፡ ዲቪ 2015፡፡ ቆይታው አንድ ወር ብቻ በመሆኑ ወደ ተስፋይቱ ምድር መዝለቅ ተስፋ ያደረጋችሁ ጊዜው ደርሶ መረቡ በአሶች ሳይሞላ ቶሎ ቶሎ  ሙሉ፡፡ የለም እንደ ዋልያ ካገር አንወጣም የምትሉም እሰየው! ሞባይላችሁን ሙሉ፡፡ ሆዳችሁን ሙሉ ያላልኩት ስለምንተዋወቅ ነው፡፡ :-(
አማሪካ ግታቸው ለነጠፋባቸው አገሮች ዲቪ ይሉት መረቧን እየጣለች በያመቱ አያሌ አሦችን ትይዛለች፡፡ አገር ባህር አንጡራ ሀብቷን አንጠፍጥፋ ያሳደገቻቸውን አሦች አማሪካ በዲቪ መረቧ ዋጥ ሰልቀጥ ስታደርግ ደስ ይላታል፣ ምድሯን የሚያለሙላት፤ አርግዛ ያላማጠቻቸው፣ ወልዳ ያላሳደገቻቸው ልጆች ስለምታገኝ፡፡ ኢትዮጵያም ደስ ይላታል፤ ሰው አገር ሄደው የሚጦሩ ልጆች (የተቦለደው ቃል ሲነበብ ይላል፡፡) ስላፈራች፡፡ አሶቹም እዚያ ሄደው ባንድ ደንጊያ ሁለት ወፍ ይገላሉ፡፡ አንድም አማሪካንን ያለማሉ፤ ደሞም እናት ምድራቸውን ይጦራሉ፡፡
ከመላው ዓለም ለዲቪ 2014 መርሓግብር ከተመዘገቡት 14.633.764 (አስራ አራት ሚሊየን ስድስት መቶ ሰላሳ ሶስት ሺ ሰባት መቶ ሰላሳ አራት) ሰዎች መካከል 9.374.191 (ዘጠኝ ሚሊየን ሶስት መቶ ሰባ አራት ሺ አንድ መቶ ዘጠና አንድ) ሰዎች ፎርሙን በትክክል ሞልተው ልከዋል፡፡
ኬንተኪ የተባለው አማካሪ ማዕከልም እንደተለመደው ለ2014 ዓ.ም.  ዕድሉ ቀንቷቸው ወደ መረቡ ለገቡለት 50.000 አሶች ቪዛ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህም ከመላው ዓለም ወደ 140.000 የሚጠጉ አሶች ዶላርና ሐሳር ወደ ምታፈልቀው ምድር የመዝለቂያውን ቪዛ ይሉት መታወቂያ እየጠበቁ ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ ሁሉ ወፈ ሰማይ ተመዝጋቢ መካከል “የተስፋይቱን ምድር” እስከናካቴው ይኖሩ ዘንድ የሚፈቀድላቸው የመጀመሪያዎቹ 50.000 ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
እነሆ እናንተ በለስ ቀንቷችሁ በመረቡ ውስጥ ገብታችሁ፣ ደግሞም ከዚያ ሁሉ ግሪሳ ተመርጣችሁ፣ ቪዛ የመጣላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩኝ ቪዛው ከመጣላችሁ በኋላ አማሪካ አምባሲ ለቃለ መጠይቅ ስትቀርቡ በቃለ መጠይቁ ወቅት በዋናነት ማሟላት ከሚገባችሁ ነገር መካከል ሕጋዊ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ የምስክር ወረቀት (አሁን ምን እንደሚባል ባላውቅም በኔ ጊዜ ESLCE ይባል ነበር) ካልሆነም ለዚያ አቻ ይሆን ዘንድ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሆነ ሞያ አልያም ሥልጠና የሁለት ዓመት የሥራ ልምድ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ይሆናልና ቸል አትበሉ፡፡
አንዴ ለመጀመሪያዎቹ ሃምሳ ሺዎቹ ሰዎች የተዘጋጀው ቪዛ ካለቀ በኋላ ያልደረሳቸው ሰዎች በዕድላቸው ከማዘን ውጪ አንዳችም መፈየድ አይችሉም፡፡ ቢሆንም የእግዚሐር ነገር አይታወቅምና እስከ ሴፕተምበር 30/2014 ድረስ ቪዛቸውን በተስፋ መጠባበቅ አለባቸው፡፡
እነሆ  5718 (አምስት ሺ ሰባት መቶ አስራ ስምንት)ኢትዮጵያውያን  ለዲቪ 2014 ዓ.ም  በመመዝገብ ከአፍሪካ አገሮች ናይጄሪያን፣ ኮንጎንና፣ ግብጽን ተከትለን አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠናል፡፡ (5718 ብቻ? . . . የፒያሳዎቹ ኢንተርኔት ቤቶች ብቻ በቀን አስር ሺ ሰው አይሆንም እንዴ የሚመዘግቡት? . . . ነው ወይንስ እኔ ያልገባኝ ነገር አለ? . . . )
ኢትዮጵያ ዲቪ እስክትጀምር ድረስ ዶላርና ሃሳር ወደምታፈስሰው ምድር የሚፈሰው ወንዝ ይቀጥላል፡፡
ዳዊት ወርቁ
መስከረም 2006 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

 https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/10/15/3422/

No comments:

Post a Comment