“ዘርሽ! ዘርሽ!” አሉኝ
በዘማሪት ፍቅርተ ፈለቀ
ዘርሽ ዘርሽ አሉኝ…
የተከለኝ ሳለ በቅጡ የሚያውቀኝ
የሚነቅለኝ እርሱ ቢያሻው የሚያጸድቀኝ
እኒያ ምን ገዷቸው ይዘረዝራሉ!
በሳምራዊቷ እርሾ ድንበር ይጠራሉ
ስለ ጥሪኝ ውሃ አጥንት ይቆጥራሉ
እነ ዘረ ብርቁ…
ከፋፍለው ከፋፍለው እርስትን በገመድ
መቅደሱን በዘመድ
ይመስላቸው ያለ ጽድቅ እንኳን በነገድ
ዘርሽ ዘርሽ አሉኝ…
ብመሳሰላቸው ቀያቸው ሊያኖሩኝ
ብለይ ባልመስል ከጓሮ ሊቀብሩኝ
አሜኬላ አስይዘው በአበባው ሊስቀሩኝ
ዘርሽ ዘርሽ አሉኝ…
ሳይጠሩ ሚያጠሩ
ሳይጥሩ የሚያጥሩ
አጥንት ሚቆጥሩ ስጋን የሚያልሙ
ዘርን እየለዩ ሊከፍቱ ሊዘጉ ሊያስገቡ ሊያስወጡ በር ላይ የቆሙ
ጭንጫ ላይ ተዘርተው ጭንጫ ላይ ያደጉ
እነ ዘረ ዝርው እነ ዘር ማዕረጉ
“ዘሩ እንዴት ነው?” እንጂ “እንደምን ይጸድቃል?
” “ከምን ላይ ይወድቃል?”
ከቶ ማይገዳቸው ቁብ የማይሰጣቸው
እነ አርም ባይ ነቃይ አዘምር ባይ አጥፊ
ላልማ ባይ አክሳሚ ልብላ ባይ ቀጣፊ
ዘርሽ ዘርሽ አሉኝ…
እንኪያስ ልንገራቸው
በኩራት በድፍረት ልመስክርላቸው
እኔስ የንጉስ ነኝ ንጉስ የወለደኝ ንጉስ ያሳደገኝ
በቅምጥል ያለሁ በብዙ ማዕረግ ከፍ ከፍ ያረገኝ
ለፍቅር የታረደ ፍሪዳ የምበላ
ለእውነት የተቀዳ ወይንን እጠጣሁ የምኖር በተድላ
በእጅ ያልተፈተለ በፍታን የደረብኩኝ
ንጉስ ያተመበት አክሊል ያጠለቅኩኝ
እኔስ የንጉስ ነኝ ገዢው ነው አባቴ
ማደሪያው ቦታዬ ቤቱ ደግሞ ቤቴ
ቋንቋዬ ቅኔው ነው ልሳኔ ውዳሴ
መግባቢያዬ ፍቅሩ ምታደምጠው ነፍሴ
አዎ ከንጉስ ነኝ ሞትን ከማይሞተው
የመቃብርን ደጅ በእጁ ከሚከፍተው
ጎሳዬ ወገኔ ከእርሱ ብቻ ከአንዱ
እኔ ከኢየሱስ ነኝ ሊያውም ከወይን ግንዱ
መሰረቴ ኢየሱስ ነገዴም ከኢየሱስ ደሜ ከኢየሱስ አጥንቴም ከኢየሱስ
በቃ እርሱ ነው ዘሬ
ቅዱስ የተከለኝ አባቱ ገበሬ
ሄዶ ያዘጋጀልኝ ሃገሩም ሃገሬ፡፡
No comments:
Post a Comment